‹‹የተሳካ ትዳር የሚገኘው ትክክለኛውን አጋር በማግኘት ብቻ ሳይሆን ትክክለኛውን አጋር ሆኖ በመገኘት ነው፡፡››  ባርነት አር.ብርክነር

በትዳር ውስጥ ትክክለኛውን አጋር ሆኖ ለመገኘት ይረዳዎ ዘንድ እነዚህን 8 ወሳኝ ነገሮች እንሆ፡-

1. ፍቅር /ፅናት

ፍቅር ማለት በአጋር ላይ የመፅናት ውሳኔ ነው ፡፡ ከቴሌቪዥን ድራማዎች እንዲሁም ከፍቅር ልብወለዶች ላይ እንደምናየው ወጣ ወይም ጎላ ያለ ስሜት የራቀ ነው፡፡ ይህ ጎላ ያለ ስሜት ሊመጣም ሊሄድም ይችላል ነገር ግን ትክክለኛ ጽናት ማብቂያ ነጥብ አይኖረውም ፡፡ ይህ በእውነት ሲተገበር ግን እውነተኛ ፍቅር ሊገለጽ ይችላል ፡፡ ፍቅር ማለት ውጣ ውረዶችን ፤ መጥፎ እና ጥሩዎችን እስከ መጨረሻው አብሮ የመጋፈጥ ቃልኪዳን ሲሆን የነገሮች ሂደት በጥሩ ሁኔታ እየቀጠለ ከሆነ ይህን ፅናት ለመተግበር ቀላል ሊሆን ይችላል ፡፡ ይህ እውነተኛ ፍቅር ወይም ፅናት በደንብ የሚታየው በህይወት ውጣ ውረዶች እና ፈተናዎች አብሮ ሆኖ በመጽናት ነው፡፡

2. ወሲባዊ ታማኝነት

ወሲባዊ ታማኝነት ሲባል በትዳር ውስጥ ከአካላዊ ያለፈ ምናባዊ ሀሳቦችንም ይጨምራል፡፡ ይህ ሀሳብ አእምሮ ልባችን እንዲሁም መንፈሳችንን ጭምር ያካትታል፡፡ አእምሮአችን ሌላ ሰውን በምናብ ማሰብ ከጀመረ እለት ጀምሮ ከትዳር አጋራችን ጋር የነበረንን ወሲባዊ ታማኝነት መስዋዕት አድርገናል ማለት ነው፡፡ ወሲባዊ ፍላጎትዎን ሁልጊዜም በመቆጣጠር ከትዳር አጋርዎ ጋር ይጋሩት፡፡

ወሲባዊ ታማኝነት ከሚያስፈልጋቸው ነገሮች የራስ ስነስርአት እንዲሁም ወደፊት ሰለሚያስከትለው ችግር ቀድሞ ማሰብ ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ ምንም አይነት የእርሶን ታማኝነት ጥያቄ ውስጥ ሊከቱ የሚችሉ ነገሮች ሲያጋጥምዎ አይንዎን፤ ሰውነት እንዲሁም ልብዎተን በደንብ በመቆጣጠር እምቢ ወይንም  አይሆንም ከማለት ወደ ኋላ አይበሉ፡

3. ትህትና

ሁላችንም ትህትናን የማጣት መጥፎ ጎን ይኖረናል በትዳር ግንኙነት ውስጥ ስንሆን ደግሞ ይህ ችግራችን ወጥቶ ለመታየት ይፈጥናል፡፡ ስኬታማ ትዳርን ለመገንባት በጣም ወሳኝ ከሚባሉ ነገሮች አንዱ ፍጹም አለመሆንን መቀበል ነው፡፡ ሰው በመሆናችን ጥፋት እንሰራለን ፤ትልቁና ዋናው ነገር ግን ለጥፋታችን ይቅርታ ለመጠየቅ ወደ ኋላ አለማለታችን ነው፡፡ ከትዳር አጋርዎ ጋር ባለዎት ግንኙነት የበላይነት የሚስማዎት ወይም ይህ የሚያንፀባርቁ ከሆነ ግንኙነታችሁ በጥሩ ሁኔታ ወደፊት ሊገፋ እንደማይችል ከወዲሁ ይወቁት፡፡ በዚህ ሁኔታ ከራሰዎጋር  ትግል ውስጥ ገብተው ከሆነ እስቲ ይህችን ቀላል ልምምድ ይሞክሯት፡- እርሳስ ያንሱና የትዳር አጋርዎ ከእርስዎ በላይ እና ጥሩ አድርጎ ሊሰራቸው ወይም ልትሰራቸው የሚችሉ 3 ነገሮችን ይፃፉ፡፡ ይህ ቀላል ልምምድ ዘላቂ መፍትሄ ሊሰጥዎት ይችላል እና አሁኑኑ ይሞክሩት፡፡  እንደ አስፈላጊነቱም ይደጋግሙት፡፡

4. ትእግስት / ይቅር ባይነት

በተራ ቁጥር 3 ማንም ፍፁም አይደለም እንዳልነው ሁሉ ጥፋት በሚያጋጥም ጊዜ ትዕግስትና ይቅር ባይነት ሁሌም በትዳር ግንኙነት ውስጥ ያስፈልጋሉ፡፡ ውጤታማ ትዳር ውስጥ ያሉ ሰዎች ማለቂያ የሌለው ትእግስት እና ይቅር ባይነትን መተግበር ይማራሉ፡፡ ያለፈን ስህተት እያነሱ የትዳር አጋራቸውን በቆየ ጥፋት እነዲሰቃዩ ወይም እንዲታገቱ አያደርጉም፡፡

ለጥፋቱም ምንም አይነት ካሳም ሆነ በቂም በቀል ተነሳስተው የሚያደርጉት አንዳችም መጥፎ ነገር አይኖርም።በትዳር አጋርዎ የተስራብዎን ጥፋት እስካሁን ቂም ይዘው ከሆነ አሁኑኑ ይቅር

ይበሏቸው፡፡ ይህም ልብዎን እና የትዳር ግንኙነትዎን ከማናቸውም አላስፈላጊ ነገሮች የፀዳ እና መልካም ያደርግልዎታል፡፡

5. ጊዜ

በግንኙነት ወቅት ውድ የሚባል ጊዜያችንን የማንሰዋ ከሆነ አንዳሰብነው ግንኙታችን ሊጓዝልን አይችልም፡፡ ውጤታማ ትዳር የታሰበበት ጥሩ የሚባል የአብሮነት ጊዜን ይፈልጋል፡፡ ከትዳር አጋርዎ ጋር የሚኖርዎት ግንኙነት ከማናቸውም የላቀ እና ጥልቅ ሊሆን ይገባዋል፡፡ ይህ ደግሞ የሚሳካው ከሌሎች ማህበራዊ ግንኙነቶች የላቀ ጊዜዎን ከፍቅር አጋርዎ ጋር ሲያሳልፉ ነው፡፡ ከተቻለ ከፍቅር አቻዎ ጋር ሊኖርዎት የሚገባ ጊዜን በፕሮግራም ይምሩ አንዳንዴም ለየት ያለ ቀጠሮ (date) ቢኖርዎት ይመረጣል፡፡

6. ሀቀኝነት /ታማኝነት

ሀቀኝነት እና ታማኝነት ለውጤታማ ትዳር መሰረት መሆናቸው የማያሻማ እውነት ነው፡፡ ነገር ግን ከሌሎቹ ለትዳር አስፈላጊ ነገሮች በላቀ መልኩ መተማመን ጊዜን ሊወስድ ይቻላል፡፡ ለጊዜው የማይቀና እና የታመነ እንዲሁም ትዕግስተኛ ሊሆኑ ይችላሉ ነገር ግን ዘላቂ መተማመንን መገንባት ሳምንታት፣ ወራት ወይም አመታት ያህል ጊዜ ሊወስድብዎ ይችላል፡፡ ይህ መተማመን የሚለካውም እንሆናለን ብለን በተናገርነው እና የእውነት ሆነን በተገኘንበት መጠን ነው፡፡ እውነተኛ መተማመንን በግንኙነትዎ ውስጥ መገንባት ፈልገው ከሆነ ተደጋጋሚ ልምምድ እንዲሆም ጠንከር ያለ ሙከራ ይጠበቅብዎታል፡፡

7. መነጋገር

የውጤታማ ትዳር አጋሮች በተቻለ መጠን መነጋገርን እና መረጃ መለዋወጥን ይመርጣሉ፡፡ ስለ ልጆቻቸው ፕሮግራም፣ ስለሚገዙ እቃዎች እንዲሁም ስለሚከፈሉ ሂሳቦች ሊነጋገሩ ይችላሉ ፡፡ ግን እዛ ላይ ብቻ አያበቁም ተስፋቸውን፣ የወደፊት እቅዳቸውን፣ የሚያስጨንቃቸውን ነገር እና የውስጣቸውንም ስሜት ጭምር ይለዋወጣሉ፡፡ ስለ ልጆቻቸው ላይ ወደፊት ለውጥ ሊያመጣ ስለሚችል ነገር ብቻ ሳይሆን በራሳቸው ልብ እና መንፈስ ውስጥ ለውጥ ስለሚያመጣ ነገርም ያወራሉ፡፡ ይህ በጣም አስፈላጊ የትዳር ቁልፍ በቀላሉ ሊታለፍ አይገባም ምክንያቱም ታማኝነት እና ግልጽነት የተሞላበት ንግግር ከላይ ለተገለጹት ነገሮች ሁሉ (ለጽናት፣ትዕግስት ፣ ተማኝነት ወዘተ) ዋናው መሰረት ነው፡፡

8. ሌሎችን ማስቀደም

ምንም እንኳን በጥናቶች ባይገለፅም ብዙ ትዳሮች  የሚፈርሱት በራስ ወዳድነት ወይም ራስን ከሌላ ሰው (ከትዳር አጋር) አብልጦ በማየት ነው፡፡ አንዳንድ ጥናቶች ገንዘብን፣ግልፅ አለመሆንን እንዲሁም አለመተማመንን ለዚህ ለትዳር መፍረስ እንደ ዋና ምክንያት ይወሰዱታል ነገር ግን የዚህ ችግር ስር መሰረት ሆኖ የሚገኘው ራስን ከምንም በላይ መውደድ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ራስ  ወዳድ ሰው ሊያምነው የሚችለው እራሱን ብቻ ከመሆኑም አልፎ ትዕግስትም የነሳውና ጥሩ የትዳር አጋር ለመሆን ካለው ተሞክሮ ትምህርት ለመውስድ የሚቸገር ነው፡፡ ራዕይዎትን ፣ህልምዎን እንዲሁም መላው ህይወትዎን ለትዳር አጋርዎ አሳልፈው ይሰጡ፡፡ በተቻልዎት መጠንም ከትዳር አጋርዎ ጋር ህይወት ለማጣጣም ይሞክሩ፡፡

ይህች ማስታወሻ ለትዳርዎ ዋጋ ይሰጡ ዘንድ ትረዳዎ ይሆናል፡፡ የትዳር አጋርዎን ይንከባከቡ፣ በደንብም ይያዙ እናም ያለዎትን ነገር ሁሉ ለማካፈል ወደ ኋላ አይበሉ፡፡ እነዚህ የተጠቀሱትን ነገሮች ሁሉ በአንዴ ማሟላት ሊከብድዎት ይችል ይሆናል ነገር ግን ይሞክሩት፡፡ ውጤታማ ትዳር በህይወታችን ውስጥ ከምንፈልጋቸው ነገሮች ሁሉ የላቀ ነው፡፡ የሁልጊዜ ዘላቂነትም አለው፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.