የሃሞት ጠጠር ለስረዓተ ምግብ መፈጨት የሚያገለግሉት ፈሳሾች በመጠጠር/በመጠንከር በሃሞት ከረጢት ዉስጥ በሚጠራቀሙበት ወቅት የሚከሰት ነዉ፡፡ የሃሞት ከረጢት ሾጠጥ ያለች በቀኝ ጎናችን ከጉበታችን ስር የምትገኝ አካል ናት፡፡

የህመሙ ምልክቶች
የሃሞት ጠጠር ምንም የህመም ምልክት ላይኖረዉ/ላያሳይ ይችላል፡፡ የሃሞት ጠጠሩ በሃሞት መተላለፊያ ቱቦ ዉስጥ ከተሰካ/ከተወተፈና ቱቦዉን ከዘጋዉ የሃሞት ጠጠር ህመም ምልክቶች መታየት ይጀምራሉ፡፡ እነርሱም
• ድንገታዊ የሆነና እየጨመረ የሚመጣ በቀኝ የላይኛዉ ሆድዎ አካባቢ ህመም መሰማት
• ድንገታዊ የሆነና እየጨመረ የሚመጣ ጨጓራዎ ባለበት አካበቢ በጡትና ጡት መካከል ባለዉ አጥንትዎ መጨረሻ ህመም መሰማት
• በሁለቱ ትከሻዎ መሃል በጀርባዎ ላይ ህመም መሰማት
• በቀኝ ትከሻዎ ላይ ህመም መሰማት

የሃሞት ጠጠር ህመም ከደቂቃዎች እስከ ተወሰነ ሰዓታት ድረስ ሊቆይ ይችላል፡፡

የህክምና ባለሙያዎን ማማከር የሚገባዎ መቼ ነዉ?
ከሃሞት ጠጠር ጉዳት/መወሳሰብ( complication) ጋር ተያያዥነት ያላቸዉ የህመም ምልክቶች ካለዎ ባስቸኳይ የህክምና ባለሙያዎን ያማክሩ
• ከፍተኛ የሆነ የሆድ ህመም ካለዎና ህመሙ አላስቀምጥ ወይም አልሻሻል ካለዎ
• አይንዎ ወይም ቆዳዎ ወደቢጫነት ከተለወጠ
• ትኩሳትና ብርድ ብርድ የማለት ስሜት ካለዎ

ለሃሞት ጠጠር መከሰት ምክንያቶች
ለሃሞት ጠጠር መፈጠር ምክንያቶቹ በትክክል ምን እንደሆነ አይታወቅም፡፡ ነገር ግን የህክምና ባለሙያዎች የሚከተሉት ለጠጠር መፈጠር ምክንት ሊሆኑ ይችላሉ ይላሉ፡፡
• ሃሞትዎ በጣም ብዙ ኮሌስትሮል ካለዉ፡- ኮሌስትሮሉ ከመጠን ካለፈ በመጀመሪያ ወደ ክሪስታልነት ከተለወጠ በኃለ የሃሞት ጠጠር እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡
• በሃሞትዎ ዉስጥ በጣም ብዙ ቢሊሩቢን/ bilirubin/ የሚባለዉ ኬሚካል ካለ፡- የቢሊሩቢን ኬሚካል በብዛት መገኘት የሃሞት ጠጠር እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡
• ሃሞት በአግባቡ ከሃሞት ከረጢትዎ ዉስጥ የማይወገድ ከሆነ፡- የሃሞት ከረጢትዎ ሃሞትን በአግባቡ የማታስወግድ ከሆነ ሃሞት ከመጠን በላይ ስለሚወፍር/concentrated / ስለሚሆንለሃሞት ጠጠር መፈጠር ምክንያት ይሆናል፡፡

ለሃሞት ጠጠር መፈጠር ተጋላጭነትዎን የሚጨምሩ ነገሮች
• ሴት መሆን
• ወፍራም/ከመጠን ያለፈ ክብደት መኖር
• ነፍሰጡር ሴቶች
• ስብነት የበዛባቸዉን ምግቦች ማዘዉተር/ high-fat diet
• ኮሌስትሮል የበዛባቸዉን ምግቦች ማብዛት
• የፋይበር ይዘት የሌላቸዉ ወይም አነስተኛ የፋይበር ይዘት ያላቸዉን ምግቦች ማዘዉተር
• በቤተሰብ ዉስጥ የሃሞት ጠጠር ያለባቸዉ መኖር
• የስኳር ህመም
• ዕድሜዎ 40 አመትና ከዚያን በላይ መሆን
• ክብደት በፍጥነት የሚቀንሱ ሰዎች
• ኮሌስትሮልን ለማዉረድና ሆርሞን ያለባቸዉ መድሃኒቶችን የሚወስዱ ሰዎች

የሃሞት ጠጠር ህክምና
ጠጠሩን ለማስወገድ የሚደረግ ቀዶ ጥገና፡- የሃሞት ጠጠር ህመም በተደጋጋሚ ሊከሰት ስለሚችል የህክምና ባለሙያዎ የሃሞት ከረጢትዎ በቀዶ ጥገና እንዲወጣ ሊያደርግልዎ ይችላል፡፡

የሃሞት ጠጠርን እንዴት ልንከላከለዉ እንችላለን?
የሃሞት ጠጠር ተጋላጭነትዎን የሚከተሉትን መንገዶች በመተግበር ለመቀነስ ይሞክሩ
• የአመጋገብ መርሃግብርዎን ያለመዝለል፡- በየቀኑ የአመጋገብ መርሃግብርዎን መተግበር፡፡ መርሃግብርዎን መዝለል ወይም ለብዙ ሰዓታት ሳይመገቡ መቆየት ለሃሞት ጠጠር የመጋለጥ ዕድልዎን ይጨምራል።
• ክብደትን ቀስ በቀስ መቀነስ፡- ክብትን ሲቀንሱ ቀስ በቀስ መሆን አለበት፡፡ ክብደትን በፍጥነት መቀነስ ለሃሞት ጠጠር መፈጠር ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ (በሳምንት 1 ኪግ ለመቀነስ ማቀድ)
• ጤናማ ክብደትን መጠበቅ፡- ከመጠን በላይ ዉፍረትና ክብደት መኖር ለሃሞት ጠጠር መከሰት ምክንያት ናቸዉ፡፡ የሚመገቡትን የካሎሪ መጠን በመቀነስና የሚሰሩትን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በመጨመር ክብደትዎን አመጣጥኖ መጠበቅ ያሻል፡፡ አንዴ ጤናማ ክብደት ላይ ከደረሱ በኃላ ጤናማ አመጋገብ በመከተልና መደበኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በማድረግ ክብደትዎን መጠበቅ ያስፈልጋል፡፡

11048653_494343177396574_2541591818774611963_n

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.