ግላኮማ / Glaucoma

0

ግላኮማ የተለያዩ የአይን ችግሮች አንድ ላይ ሆነዉ ለእይታ የሚያገለግሉ ነርቮች/ optic nerve/ ላይ ጉዳት በማስከተል አይነስዉርነት እንዲመጣ/እንዲከሰት ሊያደርጉ ከሚችሉ የአይን ችግሮች ዉስጥ የሚጠቀስ ሲሆን ከነዚህ ዉስጥ በአብዛኛዉ ጊዚ የአይን ግፊት መጨመር / high intraocular pressure/ ለጉዳቱ መከሰት ዋነኛ መንስኤ ነዉ፡፡
ግላኮማ እርስዎ የአይን እይታዎ መቀነሱ በደንብ ሳይታወቅዎ ቀስ በቀስ እየቀነሰ እንዲሄድ በማድረግ የእይታዎ መጠን መቀነስ ከፍተኛ ደረጃ እንዲደርስ ያደርጋል፡፡ በጣም ብዙ ጊዜ/በተደጋጋሚ ከሚከሰቱ የግላኮማ አይነቶች ዉስጥ ኦፕን አንግል ግላኮማ/ open-angle glaucoma የሚባለዉ ሲሆን ይህ እይታን ቀስ በቀስ እየቀነሰ እንዲሄድ ከማድረግ በስተቀር ሌላ በቀላሉ የሚለይ ምንም አይነት የህመም ምልክት የለዉም፡፡ ስለሆነም ግላኮማን በጊዜዉ መመርመርና አስፈላጊዉን ህክምና ማድረግ በእይታ ነርቭዎ ላይ የሚከሰተዉን ጉዳት ከመቀነሱም/ከመከላከሉም በላይ ከግላኮማ ጋር ተያይዞ የሚመጣዉን እይታ መቀነስና አይነስዉርነት መከላከል ይቻላል፡፡ ስለዚህ መደበኛ የሆነ የአይን ምርመራ ማድረግና የአይን ግፊትዎን መጠን መለካት አስፈላጊ ነገር ነዉ፡፡
ኦፕን አንግል ግላዩኮማና ክሎዝድ አንግል ግላኮማ የሚባሉት ሁለቱ የግላዩኮማ አይነቶች ሲሆኑ የተለያዩ የህመም ምልክቶች አሉዋቸዉ ፡፡
ፕራይመሪ ኦፕን አንግል ግላኮማ ያለ ምንም የህመም ምልክት ቀስ በቀስ እይታ እየቀነሰ እንዲሄድ የሚደርግ ሲሆን አክዩት ክሎዝድ አንግል ገላኮማ/ angle-closure glaucoma/ በበኩሉ ደግሞ የሚከተሉትን ምልክቶችን ያሳያል፡፡ እነርሱም፡-
• የአይን ህመም
• የአይን ህመሙን ተከትሎ የማቅለሽለሽና የማስታወክ መኖር
• ድንገታዊ የሆነ የአይን እይታ ችግሮች( በተለይ ደብዘዝ ባለ ብርሃን ዉስጥ)
• ብዥታ
• የአይን መቅላትና የመሳሰሉት ናቸዉ፡፡
ለግላኮማ ተጋለጭነትዎን የሚጨምሩ ነገሮች
• የአይን ግፊት መጨመር፡- ምንም እንኳ ሁሉም የአይን ግፊት መጨመር ያላቸዉ ሰዎች ግላኮማ ያጋጥማቸዋል ባይባልም የአይንዎ ግፊት ከኖርማሉ በላይ ከጨመረ በግላዩኮማ የመያዝ ተጋላጭነትዎ ይጨምራል፡፡
• እድሜ፡- እድሜዎ ከ60 ዓመት በላይ እየሆነ ሲመጣ በግላኮማ የመያስ እድልዎ እየጨመረ ይመጣል፡፡ እድሜዎ ከ40 ዓመታት በላይ እየጨመረ ሲመጣ የአንግል ክሎዠር ግላኮማ ተጋላጭነትዎ እየጨመረ ይመጣል፡፡
• በቤተሰብ ዉስጥ ግላኮማ ካለዎ፡- በቤተሰብዎ ዉስጥ ግላኮማ ያለዉ ሰዉ ካለ እርስዎም ለግላኮማ ተጋላጭነትዎ እየጨመረ ይመጣል፡፡ ግላኮማ ከዘር ጋር የሚያያዝ ነዉ፡፡
• የዉስጥ ደዌ ችግሮች፡- ለግላኮማ ተጋላጭነትዎን ሊጨምሩ የሚችሉ ብዙ ሁኔታዎች ያሉ ሲሆን ከእነዚህም ዉስጥ የስኳር ህመም፣ የልብ ህመሞች፣ የደም ግፊትና የታይሮይድ ሆርሞን መቀነስ (ሃይፖታይሮይድዝም) ይጠቀሳሉ፡፡
• ሌሎች የአይን ችግሮች፡- የግላኮማን ህመም ሊያስከትሉ ከሚችሉ ሌሎች የአይን ችግሮች ዉስጥ የአይን አደጋ/eye injuries/፣ አይን ዉስጥ የሚወጡ ዕጢዎች፣ የሌንስ ችግር፣ የአይን መቆጣትና የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ፡፡
• ለረጅም ጊዜ ኮርቲኮስቴሮይድ የሚጠቀሙ ሰዎች፡- ኮርቲኮስቴሮይድ ያለበት የአይን ጠብታን ጨምሮ ሌሎችን የስቴሮይድ አይነቶች ለረጅም ጊዜ የሚጠቀሙ ሰዎች ለችግሩ ተጋላጭ ይሆናሉ፡፡
የህክምና ባለሙያዎን ማማከር የሚገባዎ መቼ ነዉ?
የህክምና ባለሙያዎን ለማማከር የግድ አይንዎ ላይ የተለየ ለዉጥ እስኪመጣ /እስኪታይ መጠበቅ አያስፈልግም፡፡ ፕራይመሪ ኦፕን አንግል ግላዩኮማ ምንም የማስጠንቀቂ ምልክት ሳይኖረዉ የማይቀለበስ ችግር የአይን እይታዎ ላይ ሊያመጣ ስለሚችል መደበኛ የአይን ምርመራ በማድረግ ሊመጣ ከሚችል ጉዳት እራስን አስቀድሞ መከላከል ይቻላል፡፡
በተጨማሪም ማወቅ የሚስፈልገዉ ነገር ቢኖር ከፍተኛ የራስ ምታት፣ የአይን ህመምና ብዥታ ካለዎ የክሎዝድ አንግል ግላዩኮማ ምልክት ሊሆን ስለሚችል የተወሰኑትን ወይም ሁሉንም ምልክቶች ካለዎ የህክምና ባለሙያዎን ማማከር ያስፈልጋል፡፡

11071616_471900766307482_3054811719872324250_n

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.