አር ኤች ፋክተር በዘር የሚወረስ በቀይ የደም ህወሶች/ሴሎች የዉጨኛዉ መሸፈኛ/ሴል መንብሬን ላይ የሚገኝ የፕሮቲን አይነት ነዉ፡፡ ቀይ የደም ሴልዎ ላይ ፕሮቲኑ ካለዎ እርስዎ አር ኤች ፖዚቲቭ ነዎት ማለት ነዉ፡፡ በቀይ የደም ሴሉ ላይ ይህ የፕሮቲን አይነት ከሌለ ግን አር ኤች ኔጋቲቭ ይሆናሉ፡፡ ምንም እንኳ እርስዎ አር ኤች ኔጋቲቭ ቢሆኑ በጤናዎ ላይ የሚያስከትለዉ ምንም አይነት ጉዳት ባይኖርም በእርግዝና ወቅት ግን ችግር ሊፈጥር ይችላል፡፡ እርስዎ አር ኤች ኔጋቲቭ ከሆኑና ባለቤትዎ አር ኤች ፖዘቲቭ ከሆነ ነፍሰጡር በሚሆኑበት ወቅት እርግዝናዎ የተለየ ክትትል ይፈልጋል፡፡
ምክንያቱም ይህ ነው። በእርግዝና ወቅት በማህፀን ካለዉ ልጅዎ ቀይ የደም ሴሎች/ህዋሶች የእንግዴ ልጁን አልፈዉ ወደ እርስዎ ደም ዉስጥ ሊቀላቀሉ ይችላሉ። እርስዎ አር ኤች ኔጋቲቭ ከሆኑ (ሾተላይ ካለዎ) የእርስዎ የበሽታ መከላከያ ህዋሳት (ሴሎች) የልጁን የደም ህዋሳት እንደ ባዕድ ስለሚቆጥሯቸው እነዚህን የልጁን የቀይ ደም ሴሎች/ ህዋሳት ሊያጠፉ የሚችሉ መከላከያ አንቲቦዲዎችን/ ንጥረነገሮችን ሰዉነትዎ እንዲያዘጋጅ ያደርጋሉ፡፡ እነዚህ ሰዉነትዎ ያዘጋጃቸዉ የልጁን የደም ህዋሳት የሚፃረሩ አንቲቦዲዎች የእንግዴ ልጁን በማለፍ/በማቋረጥ በማህፀንዎ እያደገ ባለዉ ፅንስ ቀይ የደም ሴሎች ላይ ጉዳት ያደርሳሉ፡፡
እናትየዋ ከዚህ በፊት አቅዳም ይሁን ሳታቅድ ዉርጃ ኖሯት የበሽታ መከላከል ህዋሶቿን ካለነቃቃች በስተቀር፤ አንቲቦዲዎቹን ለማዘጋጀት ጊዜ ስለሚያስፈልጋት የመጀመሪያ ልጇን ብዙዉን ጊዜ ያለ ምንም ችግር ልትወልድ ትችላለች፡፡ በሚቀጥሉት እርግዝናዎቿ ላይ ግን በተለይ የተረገዘዉ ልጅ አር ኤች ፖዘቲቭ ከሆነ ችግር የሚፈጠር ስለሆነ በቂ ክትትል ማድረግ ይኖርባታል፡፡

ሾተላይን እንዴት መከላከል ይቻላል?
ሾተላይን ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ መከላከል ይቻላል፡፡ በእርግዝና ወቅት አር ኤች ኔጋቲቭ የሆኑ እናቶች ጥብቅ የእርግዝና ክትትል ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ አር ኤች ኔጋቲቭ የሆኑ እናቶች የተለየ/ልዩ የሆነ ሮሆጋም/ አንታይ ዲ የሚባል ክትባት ይሰጣቸዋል፡፡ ይህ የሚሆነዉ የፅንሱ አባት ደም አር ኤች ፖዘቲቭ ከሆነ አሊያም የማይታወቅ ከሆነ ሲሆን መድሃኒቱ የሚሰጠዉ በሁለተኛዉ የእርግዝና ክፍለ ጊዜ (second trimester) ነዉ፡፡ የተወለደዉ ልጅ ደም ለአር ኤች ሲመረመር አር ኤች ፖዘቲቭ ከሆነ እናትየዋ ድጋሚ ልጁ በተወለደ በጥቂት ቀናት ዉስጥ( በ72 ሰዓታት ዉስጥ) ለሁለተኛ ጊዜ የክትባቱን መርፌዉን ትወጋለች፡፡
እናትየዋ መድሃኒቱን የምትወጋዉ/ይህን መድሃኒት መዉሰድ የሚያስፈልግበት ዋና ምክንያት ልጇን ሊጎዳ የሚችለዉ አንቲቦዲ ሰዉነቷ እንዳያመርት ለመከላከል ሲሆን አር ኤች ኔጋቲቭ የሆኑ እናቶች መድሃኒቱን የግድ መወጋት ያለባቸዉ በሚከተሉት በአንዱ ወቅት ነዉ፡፡
• በእያንዳንዱ እርግዝና ወቅት
• ፈልገዉትም ይሁን ሳይፈልጉት ዉርጃ ካላቸዉ
• በእርግዝና ወቅት ሆዳቸዉ ላይ አደጋ ከተከሰተና
• በእረግዝና ክትትል ወቅት ከእንግዴ ልጅ ወይም ከሽርት ዉሃ ናሙና ከተወሰደ በኃላ ናቸዉ፡፡

10968374_464752870355605_4777351185179811640_n

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.