ቫሪኮስ ቬይን/ varicose veins

ቫሪኮስ ቬይን የተጣጠፉና ያባበጡ የደም መልስ/veins ሲሆኑ በየትኛዉም የደም መልሶች ላይ ሊከሰት የሚችል ነዉ፡፡ ቫሪኮስ ቬይን አብዛኛዉን ጊዜ የሚከሰተዉ ግን እግር ላይ ባሉ የደም መልሶች ላይ ነዉ፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት በሚቆሙበት ወይም ቀጥ ብለዉ በሚሄዱበት ወቅት በታችኛዉ የሰዉነት ክፍል ላይ ባሉ የደም መልሶች ላይ ከፍተኛ ጫና/ግፊት ስለሚፈጠር ነዉ፡፡

የህመሙ ምልክቶች
አብዛኛዉን ጊዜ ቫሪኮስ ቬይን ብዙም የህመም ምልክት የለዉም፡፡ የህመም ምልክት ካለ ግን የሚከተለዉን ሊያሳይ ይችላል፡፡
• ሰማያዊ ወይም ጠቆር ያሉ የደም መልሶች
• በእግርዎ ላይ እንደ ገመድ የተወጣጠሩና የተጠማዘዙ የደም መልሶች መታየት
• በእግርዎ ላይ የህመም ወይም የመክበድ ስሜት መፈጠር
• የማቃጠል፣ የመምታት፣ የጡንቻ ላይ ህመምና የእግር ላይ እብጠት መከሰት
• ለረጅም ጊዜ ሲቀመጡ ወይም ሲቆሙ የህመም መባባስ መከሰት
• የማሳከክ ስሜት በደም በልሱ ዙሪያ መከሰት
• በቁርጭምጭምትዎ አካባቢ ቁስለት መፈጠር የመሳሰሉት ናቸዉ፡፡
የህክምና ባለሙያዎን ማማከር የሚገባዎ መቼ ነዉ?
የህመሙን ስሜት ለመቀነስና እንዳይባባስ ለማድረግ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ፣ እግርዎን ከፍ አድርገዉ መቀመጥ/መተኛት እስቶኪንግ ማድረግ ይመከራል፡፡ ይኸንን አድርገዉ የህመምዎ ስሜት ካልቀነሰ ወይም ሌሎች ነገሮች ካሳሰብዎ የጤና ባለሙያዎን ማየት ያስፈልጋል፡፡

ለቫሪኮስ ቬይን የሚያጋልጡ ነገሮች
• እድሜ፡- እድሜዎ እየጨመረ ሲመጣ በቫሪኮስ የመያዝ እድልዎ ይጨምራል፡፡
• ፆታ፡- ቫሪኮስ ቬይን ከወንዶች ይልቅ ሴቶች ላይ በብዛት ይታያል፡፡
• በቤተሰብ ዉስጥ መሰል ችግር ካለ፡- በቤተሰብዎ ዉስጥ መሰል ችግር ካል በቫሪኮስ ቬይን የማያዝ እድልዎ ይጨምራል፡፡
• ዉፍረት፡- ከመጠን ያለፈ ክብደት በደም መልስ ላይ ጫና ስለሚፈጥር ለቫሪኮስ ያጋልጥዎታል፡፡
ለረጅም ጊዜ መቀመጥ/መቆም፡- በአንድ ቦታ ለረጅም ጊዜ መቆየት የደም ዝዉዉሩን ስለሚከለክል ለችግሩ መከሰት መንስኤ ይሆናል፡፡
ሊደረጉ የሚችሉ ህክምናዎች
• ለራስዎ የሚያደርጉት እንክብካቤ፡- የአካል ብቃት እንቅስቃሴ፣ ክብደት መቀነስ፣ በጣም ጥብቅ ያሉ አልባሳትን ያለማድረግ/ያለመልበስ፣ ሲቀመጡም ይሁን ሲተኙ እግርዎን ከፍ ማድረግ፣ ለረጅም ጊዜ መቀመጥን/መቆምን ማስወገድ የቫሪኮስን ህመም ከመቀነሱም በላይ እንዳይባባስ ያደርጋል፡፡
• ኮምፕረሽን እስቶኪንግ መጠቀም፡- ወደሌላ ህክምና ከመሄድዎ በፊት እስቶኪንግ በማጥለቅ መሞከር፡፡ ይህ በየቀኑ የሚደረግ ሲሆንየእግርዎን ጡንቻዎች ስለሚጨምቁ የደም ዝዉዉሩ ጥሩ እንዲሆን ያደርጋሉ፡፡ ኮምፕሬሽን ስቶኪንግ ሲገዙ በትክክል እንደሚሆንዎ ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡
• ከበድ ላሉ ቫሪኮስ ቬይን የሚደረጉ ህክምናዎች፡- ከላይ ባሉት ዘዴዎች ችግሩ ካልተቃለለ ወይም እየተባባሰ ከመጣ እንደ ስክሌሮቴራፒ፣ ሌዘር ሰርጀሪ፣ ቬይን ስትሪፕይንግ፣ አምቡላቶሪ ፍሌቤክቶሚ የሚባሉ ፕሮሲጀሮች ስላሉ የህክምና ባለሙያዎን ማማከር ያስፈልጋል፡፡

ቫሪኮስን እንዴት ልንከላከለዉ እንችላልን?
ቫሪኮስ ቬይንን ሙሉ በሙሉ እንዳይከሰት የሚያደርግ መንገድ ባይኖርም የደም ዝዉዉሩን በማሻሻልና የእግር ጡንቻዎችን በመወጠር ቫሪኮስ እንዳይከሰት ለማድረግና ተከስቶም ከሆነ ተጨማሪ እንዳይመጣ ለመከላከል ይረዳል፡፡ በተጨማሪም የቫሪኮስ ቬይንን ህመም ለመቀነስ የሚረዱት መንገዶች/ዘዴዎች ህመሙ እንዳይከሰት ለመከላከል የሚረዱ ሲሆን እነርሱም
• የአካል ብቃት እንቅስቃሴ
• ክብደትዎን መከታተል
• የፋይበር/ቃጫ ይዘታቸዉ ከፍ ያሉ ምግቦችንና የጨዉ ይዘታቸዉ መጠነኛ የሆኑ ምግቦችን ማዘዉተር
• ተረከዛቸዉ ከፍተኛ የሆኑ ጫማዎችን ያለማዘዉተር
• ሲቀመጡ/ሲተኙ እግርዎን ከፍ ማድረግ
• ብዙ ሰዓት የሚቆሙ/የሚቀመጡ ከሆነ ቶሎ ቶሎ አቋምዎን/አቅጣጫዎን መቀያየር ናቸዉ፡፡

10563187_490614284436130_421777425278790294_n

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.