የወሊድ መከላከያ ዘዴዎች፡- የትኛዉ ዘዴ ነዉ ለኔ የሚመረጠዉ?

 

ዛሬ በወሊድ መከላከያ ዘዴዎች ላይ ምክሮች እንሰጥዎታለን፡፡ ስለወሊድ መከላከያ ዘዴዎችም ይሁን ስለሌላ የጤና ጉዳይ ተጨማሪ መረጃ ከፈለጉ 8896 ሃሎ ዶክተር ላይ በመደወል በቂ ልምድና ሙያ ያላቸዉን ሀኪሞቻችንን ያማክሩ፡፡ እርስዎን ለማማከር ሁሌም ዝግጁ ናቸዉ፡፡

በጣም ከሚታወቁት ኮንደምና የሚዋጡ እንክብሎችን ጨምሮ እርግዝናን ለመከላከል የሚችሉ ብዙ አይነት የወሊድ መከላከያ ዘዴዎች አሉ፡፡ ከመከላከያዎች ጋር ተያይዞ መታየት የሚገባቸዉ ብዙ ጉዳዮች ስላሉ የትኛዉ ዘዴ ለእርስዎ ተመራጭ እንደሆነ ለመወሰን አስቸጋሪ ሊሆንብዎ ይችላል፡፡ ስለሆነም ከግምት ዉስጥ ሊገቡ ከሚገባቸዉ ጉዳዮች የሚከተሉት ናቸዉ፡፡

• የመከላከያዉ ዘዴዉ ምን ያህል እርግዝናን ሊከላከል ይችላል?
• ተስማሚ ነዉ ወይ? ለመጠቀምስ አስታዉሳለሁ ወይ?
• በየቀኑ መዉሰድ/መጠቀም ይጠበቅብኛል ወይ?
• መከላከያዉን እንዳቆምኩ ወዲያዉ ማርገዝ እችላለሁ ወይ?
• ይህ ዘዴ ለብዙ ደም መፍሰስ ያጋልጠኛል ወይስ አያጋልጠኝም?
• በመከላከያዉ ምክንያት የሚከሰቱ የጎንዮሽ ጉዳት ወይም ችግር አለ ወይ?
• የመከላከያዉ ዘዴዉ የመግዛት አቅምዎን ያገናዘበ ነዉ ወይ?
• ይህ ዘዴ ከሌሎች የአባለዘር በሽታዎች መከላከል ይችላል ወይ? የሚሉት ናቸዉ፡፡

አብዛኛዎቹ የወሊድ መከላከያ ዘዴዎች በአግባቡ ከተጠቀሙባቸዉ እርግዝናን የመከላከል ብቃት አላቸዉ፡፡ የተወሰኑት እንደ በማህፀን ዉስጥ የሚገባዉ(IUDs)፣ በክርን ዉስጥ የሚቀበሩና የሚወጉ የወሊድ መከላከያ ዘዴዎች እርግዝናን የመከላከል ብቃታቸዉ ከፍተኛ ሲሆን ዘዴዉን ተጠቅመዉ የማርገዝ እድልዎ በጣም አነስተኛ ነዉ፡፡ በአጠቃላይ ሲታይ የግብረስጋ ግንኙነት ሊያደርጉ ሲሉ የሚጠቀሟቸዉ እንደ ኮንደምና ዲያፍራም ከሉፕ(IUCD)ና ከወሊድ መከላከያ እንክብሎች አንፃር ሲታይ የመከላከል ብቃታቸዉ አነስተኛ ነዉ፡፡
የወሊድ መከላከያዎን ለመዉሰድ ረስተዉ ከሆነ ወይም የወሰዱት የመከላከያ ዘዴ የመስራት ብቃት የሌለዉ ከሆነ፣ የግብረስጋ ግንኙነት ካደረጉ በ3 ቀናት ዉስጥ ቢወሰዱ የማርገዝ እድልዎን ሊቀንሱ የሚችሉ መድሃኒቶችም አሉ፡፡
መታወቅ ያለበት ነገር ቢኖር እርግዝናን መቶ በመቶ/ ሙሉ በሙሉ ለመከላከል የሚያስችል የወሊድ መከላከያ ዘዴ የለም፡፡ ስለሆነም ጥቅሙንና ጉዳቱን በማመዛዘን እርስዎ በትክክልና በተከታታይ ሊወስዱ የሚችሉትን የመከላከያ ዘዴ በመምረጥ ይጠቀሙ፡፡

ድንገተኛ የወሊድ መከላከያ ዘዴዎች
የወሊድ መከላከያ እንክብልዎ ሳይወስዱ ግንኙነት ካደረጉ፣ በግንኙነት ወቅት ኮንደም ቢቀደድብዎ፣ ወይም በሌላ ምክንያት ልቅ የሆነ የግብረስጋ ግንኙነት ካደረጉ ድንገተኛ የወሊድ መከላከያ ዘዴዎችን መጠቀም ይችላሉ፡፡ እነዚህ ዘዴዎች ሆርሞን ያላቸዉ ወይም የሌላቸዉ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ እነዚህም በአፍ የሚዋጡ እንክብል ወይም በማህፀን የሚገባ ሉፕ(IUCD) ሊሆን ይችላል፡፡

የወሊድ መከላከያ እንክብሎች
ብዙዎቹ የወሊድ መከላከያ እንክብሎች የሁለት ሆርሞኖች ድብልቅ ናቸዉ፡፡ ይህን ዘዴ በትክክል ከተጠቀሙት ዉጤታማ ነዉ፡፡ የመዉሰጃ ሰዓትዎን ካሳለፉ ባስታወሱበት ሰዓት ወዲያዉ እንዲወስዱ የሚመከር ሲሆን ሁለትና ከዚያ በላይ ቀናት እንክብሎችን ሳይወስዱ ቀርተዉ ከሆነ በየቀኑ የሚወሰደዉን እየወሰዱ በመቀጠል ተጨማሪ እንደ ኮንደም ያሉ የመከላከያ ዘዴን ለተከታታይ 7 ቀናት አብሮ መጠቀም ይመከራል (ወይም ድንገተኛ የወሊድ መከላከያ ዘዴዎችን መጠቀም ይቻላል)፡፡
የጎንዮሽ ጉዳት
• ማቅለሽለሽ፣ የጡት ህመም፣ ሆድ መንፋትና የባህሪ መለዋወጥ የመሳሰሉት ሲሆኑ በ2-3 ወራት ዉስጥ ሊሻሻሉ ይችላሉ፡፡
• የወር አባበ ዑደት መዛባት፡- የወር አበባዎ መዛባትና መጠን መቀነስ (አንዳንዴ ጠብታ ብቻ መታየት) በመጀመሪያ ወራት ላይ ይታያል፡፡ የወሊድ መከላከያ እንክብልዎን መርሳትም ይህን ችግር ሊያስከትል ይችላል፡፡
ፕሮጀስትሮን ኦንሊ ፒልስ (ፕሮጀስትሮን የተባለዉን ሆርሞን ብቻ የያዙ የወሊድ መከላከያ እንክብሎች) ኢስትሮጂን የተባለዉ ሆርሞን የሌለዉ ሲሆን ኢስትሮጂን ሆርሞን ያለበትን የመከላከያ እንክብል መዉሰድ ለማይችሉ የሚሰጥ/የሚያገለግል ነዉ፡፡

የሚወጉ የወሊድ መከላከያ ዘዴዎች
ይህ አይነቱ የመከላከያ ዘዴ ፕሮጀስትሮን የተባለዉን ሆርሞን የያዘ ሲሆን በየሶስት ወሩ በክርን የሚወጋ ነዉ፡፡ ይህ እርግዝናን በመከላከል ረገድ በጣም ዉጤታማ ከሚባሉት ዘዴዎች የሚመደብ ነዉ፡፡
የጎንዮሽ ጉዳት፡- የወር አበባን ማዛባትና ማብዛት/ጠብታ ብቻ መታየት፡፡ ይህ ችግር በተለይ በመጀመሪያዎቹ ሶስት እና ስድስት ወራት የሚታይ ሲሆን እስከ 50 ፐርሰንት የሚደርሱ ሴቶች ደግሞ ይህን ዘዴ ለአንድ አመት ከተጠቀሙ የወር አበባ ዑደት ጭራሹኑ ላያዩ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን መከላከያዉን ካsረጡ የወር አበባ ዑደታቸዉ የመጨረሻዉን መርፌ ከተወጉ በ6 ወራት ዉስጥ ተመልሶ ሊመጣ ይችላል፡፡

ኢምፕላንት የወሊድ መከላከያ
ኢምፕላንት በቆዳ ስር የሚቀበር ፕሮጀስትሮን የሚባለዉን ሆርሞን ብቻ የያዘ የወሊድ መከላከያ ዘዴ ሲሆን እርግዝናን እስከ 3 ዓመታት የመከላከል ብቃት ያለዉና መድሃኒቱ በተቀበረ በ24 ሰዓታት ዉስጥ መስራት የሚችል ነዉ፡፡ በብዙ ሴቶች ላይ ከሚታዩ የጎንዮሽ ጉዳቶች ዉስጥ የወር አበባ ዑደት መዛባት ዋነኛዉ ነዉ፡፡ ብዙ ሴቶች መድሃኒቱ ከክንዳቸዉ ዉስጥ ከወጣ ወዲያዉኑ ሊያረግዙ ይችላሉ፡፡

ባርየር ሜትድ (የወንድና ሴት ዘር ፈሳሾች እንዳይገናኙ የሚያደርጉ)
ባርየር ሜትድ የሚባሉት የወንድ ዘር ፈሳሽ ወደ ሴት ማህፀን እንዳይገባ የሚከላከሉ ዘዴዎች ናቸዉ፡፡ እነዚህም ኮንደም፣ዲያፍራምና ሰርቫይካል ካፕ(ማህፀን አንገት ላይ የሚከደን) ናቸዉ፡፡
የወንድ ኮንደም፡- የወንድ ኮንደም በወንዶች ብልት ላይ የሚጠለቅ ሲሆን እረግዝናንም ይሁን ሌሎች የአባለዘር በሽታዎችን ለመከላከል የሚችል ሲሆን የኮንደምን የመከላከል ብቃት ለመጨመር የኮንደም አጠቃቀም መመሪያዎችን በትክክል መተግበር/መከተል ያስፈልጋል፡፡ ብዙ ሰዎች እንደ የወሊድ መከላከያ እንክብል ያሉ ሌሎች የወሊድ መከላከያ ዘዴዎችን እየወሰዱ ቢሆንም የአባለዘር በሽታዎችን ለመከላከል ኮንደምን መጠቀም ይመርጣሉ፡፡
የሴቶች ኮንደም፡- የሴቶች ኮንደም በሴት ብልት ዉስጥ የሚጠለቅና የወንዶች የዘር ፈሳሽ ወደ ሴት ብልት እንዳይገባ የሚከላከል ከፖሊዩሬቴን የተሳራ ላስቲክ ነዉ፡፡
ዳያፍራም/ሰርቫይካል ካፕ፡- ዲያፍራምና ሰርቫይካል ካፕ በማህፀን አንገት (cervix) ላይ የሚገጠምና የወንዶች የዘር ፈሳሽ ወደ ማህፀን እንዳይገባ የሚከላከል የወሊድ መከላከያ ዘዴ ነዉ፡፡ ይህ ዘዴ ስፐርሚሳይድ ከሚባለዉ የመከላከያ ዘዴ ጋር ቢሆን የተሻለ ዉጤት ያለዉ ሲሆን ከግብረስጋ ግንኙነት በኃላ ቢያንስ ከ6 እስከ 8 ሰዓታት በቦታዉ መቆየት አለበት፡፡ዲያፍራም ከ8 ሰዓት በኃላ መዉጣት የሚችል ሲሆን ሰርቫይካል ካፕ እስከ 24 ሰዓታት መቆየት ይችላል፡፡
ስፐርሚሳይድ፡- ስፐርሚሳይድ የወንዶችን የዘር ፈሳሽ(ስፐርም) ለመግደል የሚያገለግል የወሊድ መከላከያ ኬሚካል ነዉ፡፡ ስፐርሚሳይድ ከፋርማሲ ያለማዘዣ ሊያገኙ የሚችሉ ሲሆን በጄል፣ በፎም፣ በክሬም፣ ፊልም፣ ሰፖዚተሪና በእንክብል መልክ ሊገኝ ይችላል፡፡

ሉፕ( INTRAUTERINE DEVICES (IUD )- በማህፀን ዉስጥ የሚገባ
ሉፕ በጤና ባለሙያዎች በማህፀንዎ ዉስጥ የሚቀመጥ/የሚገባ የወሊድ መከላከያ ዘዴ ነዉ፡፡ እነዚህ የመከላከያ ዘዴዎች በጣም ጥሩና እርግዝናን በመከላከል ረገድ በጣም ዉጤታማ ሲሆኑ በሁለት አይነት ይገኛሉ፡፡
• ኮፐር ያለበት ሉፕና
• ሌቮኖርጄስትሮል ሆርሞን ያለበት ሉፕ ናቸዉ፡፡

10378925_435355516628674_8696318173098747505_n

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.