የተከበራችሁ ወዳጆቻችን፤ በፌስ ቡክ ገፃችን ላይ ብዙዎቻችሁ ስለሴቶች የወሲብ ችግር መረጃ እንድንሰጣችሁ አስተያየቶቻችሁን ኢንቦክስ ባደረጋችሁልን መሰረት በሴቶች የወሲብ ችግር ላይ የተወሰኑ መረጃዎች እነሆ:-

10653777_410604662437093_7966529809375767650_nቀጣይነት ያለዉ ተደጋጋሚ የሆነ የግብረስጋ ግንኙነት ፍላጎት ያለመኖር ችግር እርስዎን ወይም ግንኙነትዎን ካወከዎ በህክምናዉ የሴቶች የወሲብ ችግር አለ ልንል እንችላለን፡፡ ብዙ ሴቶች በህይወት ዘመናቸዉ በሆነ ጊዜ የወሲብ ችግር ሊገጥማቸዉ የሚችል ሲሆን ይህ ችግር በየትኛዉም የዕድሜ ክልል ሊከሰት ይችላል፡፡

የሴቶች የወሲብ ችግሮች የሚከተሉትን የሚያጠቃልል ሲሆን አንዲት ሴት አንድ ወይም ከአንድ በላይ ችግሮች ሊኖሩዋት ይችላል፡፡
• ዝቅተኛ የሆነ የግብረስጋ ግንኙነት ፍላጎት( Low sexual desire) ፡- የፍላጎት መቀነስ ወይም ጭራሹኑ ያለመኖር ችግር
• የግብረስጋ ፍላጎት የመነቃቃት ችግር( Sexual arousal disorder)፡- የግብረስጋ ፍላጎት ችግር ላይኖር ይችላል፡፡ ችግሩ ያለዉ ለግብረስጋ ግንኙነት የመነቃቃት ላይ ሲሆን ይህም ለመነቃቃት መቸገር ወይም ጭራሹኑ መነቃቃት ያለመኖር ችግር ሊሆን ይችላል፡፡
• የመርካት ችግር( Orgasmic disorder)፡- በቂ የሆነ የስሜት መነቃቃት ቢኖርም ለረጅም ጊዜ ወይም በተደጋጋሚ ያለ የመርካት ችግር ሲኖር
• በግብረስጋ ግንኙነት ጊዜ ህመም መኖር( Sexual pain disorder)

የሴቶች የወሲብ ችግር ምልክቶች
የሴቶች የወሲብ ችግር በየትኛዉም ዕድሜ ክልል የሚከሰት ሲሆን ይህ ችግር ብዙዉን ጊዜ የሚመጣዉ የሆርሞኖች መዛባት በሚኖርበት ወቅት ነዉ፡፡ ለምሳሌ ልጅ ከወለዱ በኃላ ወይም የወር አበባ ዑደት በሚቛረጥበት ወቅት(በሚያርጡበት ወቅት)፡፡ በተጨማሪ የወሲብ ችግር የተለያዩ እንደ የስኳር ህመም፣ የልብ ችግር፣ የደም ቧንቧ ችግርና ካንሰር የመሳሰሉ የጤና ችግሮች በሚኖርበት ወቅትም ሊከሰት ይችላል፡፡
ከሚተሉት አንዱ ወይም ከዚያ በላይ የሆነ ምልክቶች ካለዎት የወሲብ ችግር አለዎት ተብሎ ሊወሰድ ይችላል
• የግብረስጋ ግነኙነት የማድረግ ፍላጎትዎ ከቀነሰ ወይም ጭራሹኑ ከሌለ
• የግብረስጋ ግንኙነት ፍላጎት እያለዎ ለግንኙነት የስሜት መነቃቃት ችግር ካለዎ
• በግብረስጋ ግንኙነት ወቅት ምንም እርካታ ከሌለዎ
• በግብረስጋ ግንኙነት ወቅት ህመም ካለዎ

የህክምና ባለሙያ ማየት የሚገባዎ መቼ ነዉ?
የወሲብ ችግርዎ የአዕምሮ ሰላምዎን ከነሳዎ፣ የትዳር/ፍቅር ግንኙነትዎን ካወከዉ የህክምና ባለሙያ እንዲያማክሩ እንመክርዎታለን፡፡

ለሴቶች ወሲብ ችግር መንስዔዎች
ለወሲብ ችግር ሊያጋልጡ የሚችሉ የተለያዩ መንስዔዎች ያሉ ሲሆን እርስ በርሳቸዉ ግንኙነት ሊኖራቸዉ ይችላል፡፡
• አካላዊ ምክንያቶች፡- የመገጣጠሚያ ችግሮች( arthritis)፣ የዳሌ ዉስጥ ቀዶ ጥገና፣ ድካም፣ የራስምታት፣ የሽንትና የአንጀት ችግሮች፣ የነርቭ ችግሮችና ሌሎች የጤና ችግሮች፡፡ ለድብርት፣ ለደም ግፊት፣ ለአለርጂ ህክምና የሚሰጡ እንደ አንታይሂስታሚንና ለካንሰር ህክምና የሚወሰዱ መድሃኒቶች የወሲብን ችግር ሊያመጡ ይችላሉ፡፡
• ሆርሞኖች፡- የሆርሞኖች መለዋወጥ የተለያዩ የወሲብ ችግሮችን ሊያመጡ ይችላሉ (በእርግዝና፣ ጡት ማጥባትና የወር አበባ ዑደት በሚቛረጥበት ወቅት)
• ስነልቦናዊና ማህበራዊ ችግሮች፡- ህክምና ያላገኘ ጭንቀትና ድብርት ካለ፤ ለረጅም ጊዜ የቆየ በወሲብም ይሁን በሌላ ምክንያቶች ከትዳር/ፍቅር አጋረዎ ጋር ያለመስማማት ካለዎ፤ በእርግዝና ወቅትና አዲስ እናት ሊኮን ሲል ያሉ ጭንቀቶች፤ ባህላዊ፣ ሃይማኖታዊና የሰዉነት ቅርፅ ጉዳዮች

ለሴቶች የወሲብ ችግር ሊያጋልጡ የሚችሉ ነገሮች
• ጭንቀት ወይም ድብርት
• የልብና የደም ቧንቧ ችግሮች ካሉ
• የነርቭ ችግሮች ካሉ፡- ለምሳሌ በህብለ ሰረሰር ላይ ችግር/ጉዳት ሲደርስ
• የኩላሊት ወይም የጉበት ችግሮች ካሉ
• መድሃኒቶች፡- ለድብርትና ለደም ግፊት የሚሰጡ መድሃኒቶች
• ስነልቦናዊና ስሜታዊ ጭንቀቶች ካሉ፡- በተለይ ከትዳር/ፍቅር አጋርዎ ጋር ያለዎት ግንኙነት
• ከዚህ በፊት ወሲባዊ ጥቃት ደርሶቦት ከሆነ

ሊደረጉ የሚችሉ ምርመራዎች
• የህክምና ባለሙያዎ ስለእርስዎ ወሲባዊና የህክምና ታሪክዎን ይጠይቅዎታል፡- ስለግል ሚስጥርዎ ለህክምና ባለሙያዎ ማዉራት ሊከብድ ይችላል፡፡ ነገርግን ይህን ማድረግዎ ሊደረግለዎ ስለሚገባዉ ህክምና አጋዥና ዋነኛዉ ክፍል ስለሆነ ምንም ሳያፍሩ መነጋገር ያስፈልግዎታል፡፡
• የማህፀን ምርመራ፡- በዚህ የምርመራ ወቅት በብልትዎ አካባቢ ያለና ለችግሩ መንስኤ የሆነ ነገር እንዳለና እንደሌለ ለማረጋገጥ ምርመራ ሊደረግልዎ ይችላል፡፡
• የሆርሞን ምርመራ

ሊደረጉ የሚችሉ ህክምናዎች
ለወሲብ ችግር ሊደረጉ የሚችሉ ህክምናዎች የተለያዩ የዉስጥ ደዌ፣ ስነልቦናዊና ማኅበራዊ ችግሮችን ሊቀርፉ የሚችሉ የህክምና መንገዶችን በጋራ መጠቀም ሊያስፈልግ ይችላል፡፡

ከመድሃኒት ዉጪ ሊደረጉ የሚችሉ የወስብ ችግር ህክምናዎች
• መናገርና ማድመጥ፡- ከትዳር/ፍቅር አጋርዎ ጋር ግልፅና በእምነት ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ማድረግ በወሲብ እርካታዎ ላይ ትልቅ ለዉጥ ያመጣል፡፡ ከዚህ በፊት ስለሚወዱትና ስለማይወዱት ነገር የመወያየት ልምድ ባይኖርም ግንኙነትን በማያዉክ መልኩ ይህን ማድረግ መጀመርና ግብረመልስ መሰጣጣት ለቅርብርቦሽ ትልቅ ሚና አለዉ፡፡
• ጤናማ የአኗኗር ዘይቤን መለማመድ፡- አልኮል በብዛት ያለመጠጣት(በብዛት መጠጣት የወሲብ ህይወትዎን ስለሚጎዳ)፣አለማጨስ(ማጨስ ወደብልትዎ የሚሄደዉን የደም ዝዉዉር ስለሚቀንስ ለግብረስጋ ግንኙነት መነቃቃትን ይቀንሳል)፣የአካል እንቅስቃሴ ማድረግ(ስሜቶትን ለማነቃቃትይረዳል)፣ጭንቀትን ለመቀነስ መጣር
• የምክር አገልግሎት ማግኘት
• ማለስለሻዎችን መጠቀም፡- በግብረስጋ ግንኙነት ወቅት ህመም ካለዎት ወይም የብልት ፈሳሽ ከሌለዎ የብልት ማለስለሻዎችን መጠቀም ይችላሉ

በመድሃኒት የሚደረግ የወሲብ ችግር ህክምና
ለችግሩ እልባት ለመስጠት ለችግሩ መንስኤ የሆነዉን መሰረታዊ የውስጥ ደዌ ወይም የሆርሞን ችግር መታከም አለበት፡፡ መሰረታዊ የጤና ችግሮችን ለማከም የህክምና ባለሙያዎ
• ለወሲብ ችግር ሊዳርጉ የሚችሉና እየወሰዱት ያለ መድሃኒት ካለ እንዲለወጥ ወይም እንዲስተካከል ሊያደርግ ይችላል
• የታይሮይድ ወይም ሌሎች የሆርሞን ችግሮች ካሉ እንዲታከሙ ይደረጋል
• ድብርት ወይም ጭንቀት ካለዎ ተገቢዉን ህክምና እንዲገኙ ይደረጋሉ
• የዳሌ ዉስጥ ህመም ወይም ሌሎች ህመሞች ካለዎ ህክምና እንዲያገኙ ይደረጋሉ
ከሆርሞን መዛባት ጋር የተገኛኘ የወሲብ ችግር ካለዎ
• የኢስትሮጂን ሆረሞን ህክምና
• የአንድሮጂን ሆርሞን ህክምና ሊደረጉ ይችላሉ

የኑሮ ዘይቤ ለዉጥና የቤት ዉስጥ ህክምና
• ብዙ አልኮሆል ያለመዉሰድ
• ሲጋራ ያለማጨስ
• አካለዊ ንቃት እንዲኖሮት ማድረግ፡-ተከታታይነት ያለዉ የሰዉነት እንቅስቃሴ ማድረግ ስሜትዎን ከማነቃቃቱም በላይ የሰዉነት ቅርፅዎ እንዲስተካከል ያደርጋል
• ለመዝናናትና ለመፍታታት ጊዜ መያዝ፡-ይህን ሲያደርጉ ጭንቀትን ይቀንሳሉ፣ፈታ ስለሚሉ የቀን ተቀን የኑሮ ጭንቀትን ይቀንሳሉ፡፡ ዘና ማለት በወሲብ ልምድዎ ላይ ትከረት ለመስጠት ስለሚያግዝዎ ጥሩ የሆነ የወሲብ መነቃቃትንና እርካታን አንዲገኙ ይረዳዎታል፡፡

Source- 8896 Hello Doctor Ethiopia

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.