ልቦናዊ ክትባት

0

ጤና ይስጥልኝ….
ዛሬ ከአሃ የስነ-ልቦና አገልግሎት ባልደረባችን ሞገስ ገ/ማሪያም ስለ-ስነልቦናዊ ክትባት ያወራናል፡፡

10255608_403427846488108_8795889935482752239_n (1)ብዙዎቻችን ክትባትን የምናውቀው በቫይረስ ሊመጣ የሚችልን በሽታ ለመከላከል ነው፡፡ የአእምሮ ጤናን ለመጠበቅ ስነ ልቦናዊ ክትባት በእንግሊዘኛው ሳይኮፊላክሲስ /Psychophylaxis / ወይም ቫክሲን ፎር ሳይክ / Vaccine for psyche / በስነ-አእምሮ/psychiatry/ እና በስነልቦና/psychology/ መስክ የተለመደ ነው፡፡ ስነ-ልቦናዊ ክትባት/psychological vaccine/ ከተለመደው ክትባት በአይነቱ የተለየ ሲሆን የስሜት ወይም የአስተሳሰብ መመረዝ እንዳይነካን ብሎም የስነ-ልቦና እና የአእምሮ ቀውስ ደረጃ ላይ እንዳንደርስ የመከላከያ ስልት ነው፡፡ ይህ አይነት ክትባት ከተለመደው የክትባት አይነት የሚለየው፤ በተለመደው የክትባት አይነት የተዳከመ ቫይረስን /weakened virus/ ወደሰውነታችን በማስገባት የተፈጥሮ የበሽታ የመከላከል አቅማችንን በማንቃት በሽታ እንዲከላከል ማድረግ ሲሆን፤ ስነ-ልቦናዊ የክትባት ዘዴ ግን ስሜታችንን አስተሳሰባችንን ጤናማ በማድረግ እና መራዥ ስሜቶችና አመለካከቶች ወደ ውስጣችን እንዳይገቡ በመከላከል አእምሮአዊ ጤናችንንና ደህንነታችንን መጠበቅ ነው፡፡
በአጠቃላይ ስነ-ልቦናዊ ክትባት ማለት ጤናማ ስሜትን እና አስተሳሰብን የማዳበር ልማድ ማለት ነው፡፡ ይህም በጎ እና አወንታዊ አመለካከትን፣ አስተሳሰብን፣ ስሜትን እና ድርጊትን የሚያካትት ሲሆን ዋነኛ አላማውም የስነ-ልቦና ቀውስንና የአእምሮ ጤና መታዎክን መከላከል ነው፡፡ በአጭሩ ሰነ-ልቦናዊ ክትባት ስነ-ልቦናዊ ደህንነታችንና አእምሮአዊ ጤናችንን የምንጠብቅበትና የምንከባከብበት አእምሮኣዊ ንፅኅና/Mental Hygiene/ ወይም የአእምሮ ምግብ ልንለው እንችላለን፡፡
ይህ ፅንሰ ሃሳብ በህክምና የመጀመሪያ የጤና ክብካቤ/ Primary health care/ መርህ ውስጥ ተካቶ ብናገኘውም እንደ የግልና አካባቢን ንፅህና መጠበቅ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ ባለመሰራቱ ማህበረሰባችን ትኩረት ሲያደርግበት አይስተዋልም፡፡ በዚህም ምክንያት በአጭሩ መቀጨት የሚችል ችግር ግለሰብን፣ ትዳርን፣ ቤተሰብን፣ ማህበረሰብንና ሀገርን ማፍርስ ደረጃ ላይ ደርሶ እናገኘዋለን፡፡ ማንኛችንም ይህን የመፍረስ አደጋ እና ውድቀት አንፈልግም፡፡ የዚህ ጽሑፍ መነሻም በስሜት እና በሃሳብ መርዝ እነዚህ መዋቅሮች እንዳይፈርሱ ግንዛቤ ለማስጨበጥና ለመጠንቀቅ ይሆናል፡፡

ክትባቱን እንዴት መውሰድ ይቻላል?
የስነ-ልቦናዊ ክትባት የሚከተሉትን ተግባራት ያካትታል፡-
1. አዎንታዊ አስተሳሰብን/Positive thinking/ ማዳበር፡- በጎና አዎንታዊ አስተሳሰብን ማዳበር ጥሩ ስሜት እንዲሰማን፣ ምክንያታዊ አስተሳሰባችን እንዲጨምር እና ወደ በጎ ተግባር እንድንገባ የሚረዳ መሳሪያ ነው፡፡ የአዎንታዊ አስተሳሰብ ጠንቆች ደግሞ ሁል ጊዜ ጎደሎ ጎደሎዉን ማየት፣ አእምሮአዊ ግነትን መፍጠር፣ አልችልም ብሎ ማሰብ፣ ይህቺ አለም ኢ-ፍትሃዊ እና አድሏዊ አለም ነች ብሎ መደምደምና መብተክተክ የተወሰኑት ናቸው፡፡
2. ጥሩ ስነ-ምግባርን መከተል/ Cultivating good conduct /፡ ጥሩ-ስነ-ምግባር እንደ ጥሩ የአእምሮ ምግብ ይቆጠራል፡፡ ስራችንን፣ ማህበራዊ ግንኙነታችንንና አካላችንን በጥሩ ስነ-ምግባር የተቃኘ ማድረግ እንደ አንድ ስነ-ልቦናዊ ክትባት ይቆጠራል፡፡
3. ግብረ ገብነትን እና ጥሩ መንፈሳዊ ባህሪን መላበስ/ Having morale and good spiritual life/፡ ህይዎታችን እና ኑሯችን የእኛ ብቻ አይደለም፡፡ ከዚያ ይልቅ የማህበረስብ መስተጋብርና እሴቶች ዉጤት እንደሆንን አንዘንጋ፡፡ እነዚህ ማህበረሰባዊ እና መንፈሳዊ እሴቶች ሌላኛዎቹ የስነ-ልቦና ክትባት ምንጮች ናቸው፡፡ ከነዚህ ምንጮች አለመራቅ እንዲያውም ከምንጩ ቀድተን መጠጣት ይኖርብናል፡፡ ይህን ስናደርግ ከግጭት ነፃ የሆነ ህይዎት ይኖረናል፡፡
4. አእምሮን ማሰልጠን/ Training the mind/፡- ከላይ የተጠቀሱትን ተግባራት በየእለት ተእለት ህይዎታችን ለመተግበር አእምሮአችንን ማለማመድ እና ማሰልጠን ተገቢ ነው፡፡ የዚህ ልምምድ የመጀመሪያ መርህ ‘አለምን መቀየር አትችልም ነገር ግን አለምን የምትመለከትበትን መነፅር ቀይር’ ከሚለው አባባል መጀመር ይኖርበታል፡፡ ማለትም የራሳችንን ስሜት እና አስተሳሰብ ብቻ ነው መቆጣጠር የምንችለው፤ የሌላውን ሰው ስሜት እና አስተሳሰብ ለመቆጣጠር ስንሞክር ሚዛናችንን እንስታለን፡፡ አስተሳሰባችንንም እንመርዛለን፡፡

ስነ-ልቦናዊ ክትባትን የት ማግኘት ይቻላል?
ስነ-ልቦናዊ ክትባት ከሌላው የክትባት አይነት የሚለየው ክትባቱ ሁል ጊዜ በእጃችን መሆኑ ነው፡፡ ተከታቢውም ከታቢውም እኛ ራሳችን ነን! ችግሩ ግን ‘በእጅ የያዙት ወርቅ…’እንደሚባለው አናደንቀውም፡፡ አንጠቀምበትም፡፡

ሆኖም የስሜት መረበሽ ከአስተሳሰብና ከባህሪ ጋር የተያየዙ የስነ-ልቦና ችግሮች ሲያጋጥሙ የባለሙያ ድጋፍ ማግኘታችንን አንርሳ፡፡ ምንም እንኳ በሃገራችን ይህ መስክ በሚጠበቀው ልክ ባይለመድም፤ አገልግሎቱን የሚሰጡ ተቋማትን ብዙ ባናይም በአሁኑ ሰዓት በተለይ በአዲስ አበባ በጣት የሚቆጠሩ የስነ-ልቦና አገልግሎት ማዕከሎች ብቅ ብቅ እያሉ ነው፡፡ እስከአሁን ባለኝ መረጃ ፖስተሪቲ የስነ-ልቦና አገልግልት፣ ዶ/ር በየነች የስነ-ልቦና አገልግሎት፣ አልታ የስነልቦና እና ስልጠና ማዕከል እንዲሁም እኔ የምሰራበት አሃ የስነል-ቦና አገልግሎት መኖራቸወንና አገልግሎቱን በመስጠት ላይ እንደሆኑ አውቃለሁ፡፡ ነገር ግን ሰማኒያ ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ ላላት ሀገራችን ኢትዮጵያ ያውም ብዙ አምራች ዜጋ ላለት ሃገር እነዚህ ማእከላት በምንም መመዘኛ በቂ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ መንግስት የዜጎች አካላዊ፣ ማህበራዊ፣አእምሮኣዊና መንፈሳዊ ደህንነታቸው የተጠበቀ ይሆን ዘንድ በሚከፈቱት ት/ቤቶች ፣ ዩኒቨርሲቲ/ኮሌጆች፣ የጤና ተቋማት እና የወጣት ማእከሎች ይህ አገልግሎት በጥራት እንዲኖር ቢያደርግ የአእምሮ ጤና መታወክ ችግርን በእጅጉ መቀነስ ብቻ ሳይሆን ጤናማ እና በእራሱ እስር ቤት የሚማቅቅ ዜጋን ነፃ እንደማውጣት ይቆጠራልል፡፡ በተመሳሳይ በስለ-ልቦና አገልግሎት ዘመኔ የታዘብኩት ሰዎች በራሳቸው እስር ቤት ውስጥ እንዴት እንደሚኖሩ ነው፡፡ ትልቁ አጥር ደግሞ ፍርሃት፣ ፀፀት፣ ጥርጣሬ፣ አለማመን፣ አለመተማመን፣ ተስፋ ቢስ መሆን ነው፡፡ ሌላዉ ችግር፤ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ስንሆን የተሸከምናቸውን ዝባዝንኬዎች እንኳ መመልከት እና መጣል አለመቻላችን ነው፡፡ ይህም ማለት ያለንን ሃብት(የአስተሳሰብና ችግር የመፍታት) አቅማችንን መጠቀም አንችልም ማለት ነው፡፡ ለዚህ ማሳያ ይሆን ዘንድ ስለአንድ ውሉ የጠፋበት ሰው ታሪክ አውግቻችሁ ለዛሬዉ ላብቃ፡፡

ውሉ የጠፋበት ሰው

አንድ ግራ የተጋባ ሰው ማለቂያ የሌለው በሚመስል ጎዳና ላይ እየተጎተት ይጓዝ ነበር፡፡ይህ ሰው ሊደፋው የደረሰ የሚመሰል የሸክም ዓይነት ተሸክሟል፡፡ ጆንያ ሙሉ አሸዋ በጀርባው አዝሏል፤በዉሃ የተሞላ ወፍራም የዉሃ ፕላስቲክም በሰውነቱ ላይ ጠምጥሟል፤ በቀኝ እጁ ቅርፅ አልባ ድንጋይ ይዟል፤ በግራው ደግሞ ትልቅ ሸክላ አንጠልጥሏ፤በአንገቱ ዙሪያ አሮጌና የተበጣጠሰ ገመድ ጠምጥሟል፤ በእግሮቹ ላይ ደግሞ የዛጉ ሰንሰለቶችን አደግድጎ ቁርጭምጭሚቱ እስከሚደማ በአቧራማ እና አሻዋማ መንገድ ላይ ይኸን ሁሉ ኮተት ተሸክሞ ይጎተታል፤በራሱ ላይ ደግሞ ያልበሰለ ዱባ ተሸክሞ እንዳይወድቅበት ፈርቶ መከራውን ያያል፡፡ አንድ እርምጃ በተራመደ ቁጥር ሰንሰለቱ ጩኸቱ ብቻ ይሰቀጥጣል፡፡እያማረረ እና እያላዘነ የአርባ ቀን እድሉንም እየረገመ በዝግታ ወደፊት ይራመዳል፡፡ አንድ በአጠገቡ የሚያልፍ ሰው “አንተ ሰው እንደዚህ ደክሞህ ይህን የሚያክል ሸክላ እጅህ እስከሚገነጠል ማንጠልጠልህ ለምን ይሆን?” ብሎ ጠየቀው፡፡ ዉሉ የጠጠፋበትና ግራ የተጋባው ሰው….”ምን የማልረባ ደደብ ነኝ እሰከ አሁን አላየሁትም ነበር” ብሎ መለሰ፡፡ እሱንም ሲወረውር ትንሽ ቀለል አለው፡፡ እንደ ገናም በመንገዱ ላይ ብዙ ርቀት ከተጓዘ በኋላ አንድ ገበሬ አገኘውና “አንተ ሰው በደንብ ያልበሰለ ዱባ ተሸክመህ መቸገርህ ለምን ይሆን? እነዚህን ከባባድ እና ወደኋላ የሚጎትቱህን ብረቶችስ መሸከምህ ለምን ?” ብሎ ጠየቀው፡፡ ዉሉ የተጠፋበትም ሰው ስለጠቆምከኝ አመሰግናለሁ፡፡ እስካአሁን አላስተዋልሁትም ነበር ብሎ ሰንሰለቱንም አወለቀ ያልበሰለዉንም ዱባ ወረወረ፡፡ የበለጠም ቀለል አለው፡፡ ነገር ግን በተጓዘ ቁጥር ህመሙና ስቃዩ በዛበት፡፡ ሌላ ገበሬ ከማሳው ብቅ ሲልም ሰዉየውን በአግራሞት ተመለከተው፡፡ “አንተ ሰው ጆንያ ሙሉ አሸዋ ተሸክመሃልሳ? መንገድህ በሙሉ ተዝቆ የማያልቅ አሸዋ አይደለም እንዴ?የምትሄድበት መንገድ አሸዋ ሙሉ እንደሆነ አይታይህም? ትልቁ የዉሃ ጎማህም ልክ የሰሃራ በረሃን የምታቋርጥ ነው እኮ ያስመሰለህ፡፡ በመንገዱ ዳር ኩልል ብሎ የሚፈሰውን የምንጭ ውሃ አልተመለከትከውምን?” ሰዉየዉም ይህን ሲሰማ ካላቅሙ የተሸከመውን የውሃ ላስቲክ መሬት ላይ ዘረገፈው፡፡ ወደዚያው ቆም ብሎ በመጥለቅ ላይ ያለችውን ፀሃይ ይመለከት ጀመር፡፡ በምትጠልቀው ፀሐይ ብርሃን ውስጥ ራሱን መመልከት ጀመረ፡፡ ከባዱን ድንጋይ አሁንም ተሸክሞታል፤አላራምድ እንዳለውም ገባው፡፡ ወረወረዉም፡፡ ከድክሙ ሁሉ ተገላገለ፡፡ በነፋሻማው ምሽትም በነፃነት ማደሪያ ፍለጋ ጉዞዉን ቀጠለ፡፡
በመጨረሻም ልክ እንደዚህ ሰው የማይጠቅሙንንና ወደኋላ የሚጎትቱንን የስሜት እና የአስተሳሰብ ጓዞች ለመጣል ድፍረት ይኑረን፡፡አቅማችንንም እንጠቀም፡፡በትክክል የማይጠቅሙን መሆነቸውንም እንመልከት፡፡ በእርግግጥ የማይጠቅሙን ከሆኑ ጨክነን ለመጣል እንመን፡፡ ያን ጊዜ ጨለማው ብርሃን ይሆናል፡፡ግራ የሆነብንም ቀኝ ይሆናል፡፡ ርምጃችንም ፈጣን ይሆናል፡፡ ማየትና ማራገፍ ካቃተንም የአስተሳሰብና የስሜት ኮተቶች ሳይጨፈልቁን እና ጤናችንን ሳያዉኩት፤ ኑሯችንንም ሳይበክሉት የስነ-ልቦና ባላሙያ እናማክር፡፡ በቸር እንሰንብት፡፡

ሞገስ ገ/ማሪያም
moges@ahaethiopia.com
አሃ የስነ-ልቦና አገልግሎት

Source – 8896 Hello Doctor Ethiopia

Spread the love
  •  
  •  
  •  
  •  
  •  
  •  
  •  
  •  
  •  
  •  

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.