የስኳር ህመም በኢንሱሊን ማጠር እና በደም ውስጥ የሚገኘው የስኳር መጠን ከልክ በላይ መብዛት የሚመጣ በሽታ ነው፡፡ብዙ የስኳር በሽታ አይነቶች ቢኖሩም በጣም የተለመዱት ታይፕ 1፣ ታይፕ 2 እና በእርግዝና ጊዜ የሚኖር የስኳር በሽታ  ናቸው፡፡

2.28_glucosetestየስኳር በሽታን እና የኢንሱሊን በሰውነትህ ውስጥ ያለውን ወሳኝ ሚና በደንብ እንድትረዳ ሰውነትህ በጤናማ ጊዜ እንዴት እንደሚሰራ ትንሽ እናውራ፡፡ ሰውነትህ በሚሊዮን በሚቆጠሩ ህዋሳት የተሰራ ነው፡፡ እነዚህ ህዋሳቶች ሀይላቸውን የሚያገኙት ከቀላል ንጥረነገሮች ነው፡፡ አብዛኛው የምትበላው ምግብ ተፈጭቶ እና ተሰባብሮ ግሉኮስ ወደሚባል ቀላል የስኳር አይነት ይቀየራል፡፡ግሉኮስ በደም አድርጎ ወደተለያዩ ህዋሳት በመሄድ ቀን በቀን የሚያስፈልግህን ሀይል ለሰውነትህ በመስጠት ያገለግላል፡፡

ከጨጓራ ጀርባ የሚገኝ ቆሽት የተባለ የአካል ክፍል ኢንሱሊንን ያመርታል፡፡ ኢንሱሊን የሰውነትህ ህዋሳት የምትበላውን ስኳር እንዲጠቀሙ የሚያስቻላቸው ሆርሞን ነው፡፡ ኢንሱሊን ሆርሞን በደም ውስጥ የሚገኘውን የግሉኮስ መጠን ይቆጣጠራል፡፡ ሁልጊዜም ኢንሱሊን በትንሽ በትንሹ ከቆሽት ይለቀቃል፡፡ በደም ውስጥ ያለው ግሉኮስ ሲጨምር ለምሳሌ ከምግብ በኋላ የኢንሱሊን መጠንም ይጨምራል፡፡ በዚሀን ጊዜ ደም ውስጥ የነበረው ግሉኮስ ወደ ህዋሳት ይገባል፡፡ በደም ውስጥ ያለው የግሉኮስ መጠንም ወደነበረበት ይመለሳል፡፡

በተቃራኒው የደምህ የግሉኮስ መጠን ሲቀንስ ግሉካጎን የተባለ ሌላ በቆሽት የሚመረት ሆርሞን ይለቀቃል፡፡ ይኼም ግሉኮስ ከሚጠራቀምባቸው እንደጉበት ካሉ አካላት በመውሰድ በደም ውስጥ ያለው ግሉኮስ ከሚገባው በላይ እንዳይቀንስ ያደርጋል፡፡ በተጨማሪም ሰውነትህ ምግብ እንዲያምርህ በማድረግ የግሉኮስ መጠንህን ለመጨመር ይሞክራል፡፡

የስኳር በሽታ ያለባቸው ሰዎች ይኼ ጤናማ አሰራር ስለማይኖራቸው በደማቸው የሚገኘው የግሉኮስ መጠን ከመጠን በላይ ይጨምራል፡፡

የስኳር በሽታ ከሚከተሉት አንዱ ሲከሰት ይመጣል፡፡

 • ቆሽት ኢንሱሊንን እስከነጭራሹ ማምረት ሲያቅተው.
 • ቆሽት በቂ ኢንሱሊን ማምረት ሲያቅተው እና
 • በቆሽት የሚመረተውን ኢንሱሊን ሰውነታችን መጠቀም ሲያቅተው

በህክምና ቋንቋ የስኳር ህመም አለብህ የሚባለው ከስምንት ሰአት በላይ ምግብ ሳትበላ ቆይተህ በደምህ ውስጥ የሚገኘው የግሉኮስ መጠን 126 ሚሊ ግራም/ዴሲ ሊትር (ሚ.ግ./ዴ.ሊ.) እና ከዛ በላይ ሲሆን አሊያም በማንኛውም ሰአት ሲለካ በደምህ ውስጥ የሚገኝ የግሉኮስ መጠን ከ200 ሚ.ግ/ ዴ.ሊ. እና ከዛ በላይ ሲሆን ነው፡፡ የስኳር ህመምተኛ ተራ ውስጥ ለመመደብ እነዚህን ምርመራዎች ከአንድ ጊዜ በላይ ተሰርተው እውነት መሆን አለባቸው፡፡

ታይፕ 1 የስኳር ህመም

ታይፕ 1 የስኳር ህመም ምንድን ነው?

በወጣቶች እና በህፃናት ላይ በብዛት የሚከሰተው ይኼ ህመም በሰውነት የሚመረቱ የበሽታ መከላከያ ኬሚካሎች የቆሽትን ህዋሳት በማጥቃት ሲገድሉ እና ኢንሱሊን መመረት ሲቆም ይመጣል፡፡ በጤናማ ጊዜ ባክቴሪያ እና ቫይረስ የመሳሰሉ ከሰውነት ህዋሳት ውጭ የሆኑ እንግዳ ነገሮች የሚያጠቁት እነኚህ ኬሚካሎች ባልታወቀ ምክንያት የሰውነትን የተለያዩ ህዋሳትን በማጥቃት ችግር ይፈጥራሉ፡፡ በዚህ አይነቱ የስኳር ህመም ጊዜ ምንም አይነት ኢንሱሊን አይመረትም፡፡

ስለዚህ ደም ውስጥ የሚገኘው ስኳር ወደ ህዋሳቶች አይገባም፡፡ በደም ውስጥ የሚገኘው የስኳር መጠን ከልክ በላይ በመጨመር የስኳር ህመምን ያስከትላል፡፡ በሽታውን ከምልክቶቹ ተነስቶ ማወቅ ቢቻልም ብዙ ጊዜ ግን አደጋ የማያስከትሉ ምልክቶች ስለሆኑ ልብ አይባሉም፡፡

ታይፕ 2 የስኳር ህመም

ታይፕ 2 የስኳር ህመም ምንድን ነው?

በብዛት የሚታየው ታይፕ 2 የስኳር ህመም በኢንሱሊን አለመመረት ሳይሆን በኢንሱሊን እጥረት ይመጣል፡፡ በዚህ ህመም የተያዙ ሰዎች ቆሽት ምንም እንኳን ኢንሱሊን የማምረት ብቃት ቢኖረውም የሚያመርተው ኢንሱሊን ለሰውነታቸው በቂ የማይሆን ሲሆን ወይም ደግሞ ኢንሱሊንን የሚጠቀሙት ሌሎች የሰውነት ክፍሎቻቸው የተመረተውን ኢንሱሊን መጠቀም ያቅታቸዋል፡፡ በዚህ ጊዜ በደም ውስጥ ያለው ግሉኮስ ወደህዋሳቶች መግባት አይችልም፡፡ ህዋሳቶችም ትክክለኛ ስራቸውን መስራት አይችሉም፡፡ ደም ውስጥ የሚገኘው የስኳር መጠን ከሚገባው በላይ ይበዛል፡፡በተጨማሪም የሚከተሉት ችግሮች ያጋጥሟቸዋል፡፡

 • የውሃ እጥረት(Dehydration) – በደም ውስጥ የሚገኘው ስኳር መብዛት የሽንት መጠንን ይጨምራል፡፡ በዚህም ጊዜ የውሃ እጥረት ይከሰታል፡፡
 • የስኳር በሽታ ኮማ
 • የብዙ ሰውነት ክፍሎች ጉዳት

ታይፕ 2 የስኳር ህመም መንስኤዎች ምንድ ናቸው?

ማንኛውም ሰው በዚህ በሽታ ሊጠቃ ይችላል፡፡ ይኼ በሽታ በአንድ ምክንያት ብቻ ሳይሆን በብዙ ምክንያቶች ይመጣል፡፡ ቤተሰብ ውስጥ በበሽታው የተጠቃ ሰው መኖር ለሌላው የቤተሰብ አባል በበሽታው የመያዝ እድልን ይጨምራል፡፡ የአኗኗር ዘይቤን የሚከተለው ይኼ በሽታ ከመጠን በላይ ውፍረት በተለይ ደግሞ የወገብ ዙሪያ ውፍረት (ቦርጭ) ለበሽታው ከሚያጋልጡ ነገሮች ዋነኛው ነው፡፡

በጣም ከፍተኛ የደም ግፊት፣ በደም ውስጥ የሚገኝ ከፍተኛ የኮሌስተሮል መጠን፣ በእርግዝና ጊዜ የሚኖር የስኳር ህመም፣ ከፍተኛ የአልኮል ተጠቃሚ መሆን፣ ስብ የበዛበት አመጋገብ ፣ እንቅንቅሴ ያለማድረግ፣ በእድሜ እየገፉ መሄድ ተጨማሪ ለበሽታው የሚያጋልጡ ነገሮች ናቸው፡፡

የስኳር ህመም ምልክቶቹ ምንድን ናቸው?

የበሽታው ምልክቶች ከሰው ወደ ሰው ቢለያዩም የሚከተሉትን ያጠቃልላል፡፡

 • ሀይለኛ የውሀ ጥማት፣
 • ከመጠን በላይ የሆነ ረሀብ፣
 • የአፍ መድረቅ፣
 • ማቅለሽለሽ እና ማስታወክ፣
 • ቶሎ ቶሎ መሽናት፣
 • ክብደት መቀነስ፣
 • ድካም፣
 • የአይን ብዥታ፣
 • የእጅ እና እግር መደንዘዝ፣
 • የቆዳ እና የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽኖችን የመሳሰሉት ናቸው፡፡አንድ ሰው ታይፕ 2 የስኳር ህመም በሽታ እንዳለበት ሳይታወቅ እስከ ሃያ አመት ሊኖር ይችላል፡፡ ብዙ ህመምተኞችም በሽታው እንዳለባቸው የሚያውቁት ህመሙ በሚያመጣቸው መዘዞች ከተጠቁ በኋላ ነው፡፡

የስኳር ህመም መዘዞች ምንድን ናቸው?

የስኳር ህመም ብዙ ጉዳቶችን ያስከትላል፡፡ በተለይ በጣም የሚዋዥቅ የደም ስኳር መጠን እነዚህን መዘዞች ያፋጥናቸዋል፡፡ የስኳር በሽታ ጊዜው በሄደ ቁጥር እየቆየ የሚያስከትላቸው እና ወዲያው በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚያስከትላቸው የተለያዩ መዘዞች አሉ፡፡

የአጭር ጊዜ መዘዞች ምንድን ናቸው?

የአጭር ጊዜ መዘዞች የምንላቸው የኬቶን አሲድ መብዛት እና በጣም ከፍተኛ የደም ግሉኮስ ከከፍተኛ የደም ውህዶች (ኦስሞላሪቲ) ጋር (other explanation)ናቸው፡፡

የኬቶን አሲድ መብዛት በብዛት ከታይፕ 1 ጋር ይያያዛል፡፡ በሃያ አራት ሰአት ውስጥ የሚከሰት ማቅለሽለሽ እና ማስመለስ፣ በጣም ሀይለኛ የሆድ ቁርጠት፣የትንፋሽ ማጠር፣ ውሃ መጥማት እና ብዙ ሽንት መሽናት አንዳንዴም ኮማ ምልክቶቹ ናቸው፡፡ የኬቶን አሲድ መብዛት የሚከሰተው በሰውነት ውስጥ ያለው ኢንሱሊን እስከነጭራሹ ሲጠፋ እና የኢንሱሊንን ተቃራኒ ስራ የሚሰሩት እንደግሉካጎን እና ካቴኮህላሚን የመሳሰሉ ሆርሞኖች ሲበዙ ነው፡፡ ይህንን ሁኔታ በሰውነት ውስጥ ከሚያስከስቱ ነገሮች የመጀመሪያው የኢንሱሊን መርፌን በተለመደው ሰአት በአግባቡ አለመውሰድ ነው፡፡ በተጨማሪ ኢንፌክሽን፣ እንደኮኬይን ያሉ ንጥረነገሮች ተጠቃሚ መሆን፣ እርግዝና እና የልብ በሽታዎችን መጥቀስ ይችላል፡፡

ከፍተኛ የደም ግሉኮስ ከከፍተኛ የደም ውህዶች (ኦስሞላሪቲ )በታይፕ 2 የስኳር ህመም ጊዜ የሚኖር ሲሆን ቀድሞ ከነበራቸው የቀነሰ የኢንሱሊን መጠን ከረዥም ጊዜ የውሃ ጥም ጋር አብሮ ሲኖር ይከሰታል፡፡ ለብዙ ሳምንታት የቆየ የሽንት መብዛት፣ የክብደት መቀነስ፣ ኮማ መገለጫ ምልክቶቹ ናቸው፡፡ እነዚህ ሁሉ ችግሮች በጣም ከፍተኛ አደጋ ውስጥ የሚከቱን ቶሎ ህክምና ካልተደረገላቸው እስከህይወት ማጥፋት ስለሚደርሱ እነዚሀ ምልክቶች በታዩበት ጊዜ ወዲያው ሆስፒታል መሄድ አስፈላጊ ነው፡፡

የረዥም ጊዜ መዘዞች ምንድን ናቸው?

የስኳር ህመም በሁሉም የአካላት ክፍሎቻችን ላይ ችግር ያስከትላል፡፡ ለእነዚህ ችግሮች መከሰት የተለያዩ ነገሮች የየራሳቸውን ሚና ይጫወታሉ፡፡ ለረዥም ጊዜ የቆየ የስኳር በሽታ (በአመታት ለሚቆጠር ጊዜ)፣ በደንብ መቆጣጠር ያልተቻለ የደም ግሉኮስ መጠን፣ ከፍተኛ የደም ግፊት፣ በሰውነት ውስጥ የሚኖሩ የሆርሞን ለውጦች ለምሳሌ በእርግዝና ወቅት እና ሲጋራ ማጨስ የነዚህን ችግሮች መከሰት ያፋጥናሉ፡፡

• የአይን ችግሮች

አይን ውስጥ የሚገኙ የደም ስሮች በስኳር በሽታ ምክንያት የተለያዩ ለውጦች ያካሂዳሉ፡፡ በዚህም ጊዜ ደም ከደምስሩ ውጪ እንዲፈስ ያደርጋል፡፡ ይሕም ብዥታን ያስከትላል፡፡ በጣም ሲብስም እይታን እስከ መከልከል ሊያደርስ ይችላል፡፡

• የኩላሊት በሽታ

ለረዥም ጊዜ የቆየ የደም ግሉኮስ መጠን መብዛት በኩላሊት የደም ዝውውር ላይ ችግር ከማምጣቱ በተጨማሪ በኩላሊት ዋናው የስራ መሰረት የሆነውን የትንንሽ ደም ስሮች ስብጥር (glomerulus) ቅርፅ ይቀይራል፡፡እንዲሁም ለተደጋጋሚ የሽንት ቱቦ ኢንፌክሽንም ምክንያት ይሆናል፡፡ በስኳር ህመም ከተያዙ ሰዎች ከ20-40% የሆኑት በኩላሊት በሽታ ይያያዛሉ፡፡ ሲጋራ ማጨስ እና የስኳር ህመም ያለበት የቤተሰብ አካል የኩላሊት በሽታ ተጠቂ መሆኑ ባንተ ላይ የበሽታውን የመከሰት እድል ያፋጥነዋል፡፡

• የነርቭ ችግር

50% በሚሆኑት በሁለቱም አይነት የስኳር ህመም በተያዙ ሰዎች ላይ ይከሰታል፡፡ እንደሌሎቹ መዘዞች ሁሉ በሽታው ከስኳር በሽታ የረዥም ጊዜ ቆይታ እና ከደም ግሉኮስ መጠን መዋዠቅ ጋር ይያዛል፡፡ በሽታው እቆየ በሄደ ቁጥር እና የደም ግሉኮስ መጠንን መቆጣጠር ላይ ችግር ካለ የነርቭ ችግር የመከሰት እድሉን ይጨምረዋል፡፡ ከሱ በተጨማሪ ከፍተኛ ውፍረት እና ሲጋራ ማጨስም ለበሽታው ያጋልጣሉ፡፡ በተጨማሪም የደም ግፊት እና የልብ ችግሮች መኖር ከበሽታው ጋር ይያያዛሉ፡፡

በሁለቱም እግሮች ላይ የሚኖር የነርቭ ችግር በብዛት የሚታየው አይነት ነው፡፡ ይኼም የእግሮች ስሜት ማጣት እና ሲነኩ አለመሰማት በሽታው እየባሰ በሄደ ቁጥር ይጀምራል፡፡ የነርቭ ችግሩ ገና ሲጀምር ግን እንደመጠዝጠዝ እና ማቃጠል የመሳሰሉ ስሜቶች ከእግር ጣቶችህ ጀምረው ወደላይ እግር ቀስ በቀስ የሚተላለፍ ይሆናል፡፡ ምንም እቅስቃሴ ሳታደርግ የሚኖር እና ማታ ማታ የሚብስ የእግር ህመም የዚህ በሽታ መገለጫ ነው፡፡ በሽታው እየተባባሰ ሲሄድ ህመሙ የሚቆም ሲሆን ስሜት ማጣቱ ግን ይቀጥላል፡፡

የስኳር በሽኛ የሆነ ሰው በየአመቱ የነርቭ ምርመራ ማድረግ አለበት፡፡ አልኮል መጠጥ አለመጠጣት፣ ሲጋራ አለማጨስ፣ የእግር ቁስለትን መከላከል እንዲሁም በመድሃኒት እና በአኗኗር ዘዴ የደም ግሉኮስን መቆጣጠር ዋነኞቹ የመከላከያ መንገዶች ናቸው፡፡

• የእግር ቁስል

በስኳር ህመም የተጠቃ ሰው እግር ብዙ አደጋዎች ይደርሱበታል፡፡ የነርቭ ችግር መኖሩ የህመምተኛውን የህመም ስሜት ስለሚቀንስ ምንም አይነት አደጋ እግሩ ላይ ቢደርስ ለማወቅ ይከብደዋል፡፡ ከባድ እና በተደጋጋሚ የሚከሰቱ የእግር አደጋዎችን ለምሳሌ እንደሚስማር ባሉ ስለታማ ነገሮች ተወግተው ለቀናት እና ለሳምንታት የማያውቁበት ጊዜ ይኖራል፡፡ ከዛ ባለፈ የእግር አረጋገጡ ትክክል ስለማይሆን ብዙ ጫና ያሳድርበታል፡፡ የእግር ደም ስሮችም በበሽታው ስለሚጠቁ ምንም አይነት ቁስል ቶሎ እንዳይድን ያደርጋሉ፡፡ በተጨማሪም እግር ላብ ስለማያልበው እና የደም ዝውውሩ ስለሚስተጓጎል የመድረቅ እና የመሰነጣጠቅ ባህሪ ይኖረዋል፡፡ ይኼም ለእግር መቁሰል ከሚዳርጉ ምክንያቶች እንደ አንዱ ሆኖ ይጠቀሳል፡፡

እራስን ከዚህ ችግር መጠበቅ ዋናው እና ጠቃሚው ነገር ነው፡፡ እግር ከቆሰለ በኋላ የመዳን እድሉ በብዛት አናሳ ስለሆነ የህክምና መንገዱ በአብዛኛው የሞተውን እግር መቁረጥ (amputation) ነው፡፡ ስለዚህም እዚህ ደረጃ ላይ ሳይደረስ በፊት እራስን መጠበቅ ተገቢ ነው፡፡ የሚከተሉትን ነገሮች በማድረግ እራስህን ልትንከባከብ ትችላለህ፡፡

 1. ምንም አይነት የሚጠብህን ወይም ያዝ የሚያደርግህን ጫማ አለማድረግ፡፡ ጫማህ ምቹ መሆን ይገባዋል፡፡
 2. በየቀኑ እግርህ አገላብጠህ መፈተሽ፡፡ ትንሽ ቁስል፣ የተላጠ ቆዳ ካለ ወደሆስፒታል መሄድ ተገቢ ነው፡፡
 3. የእግርን ንፅህና መጠበቅ እና የተለያዩ ቅባቶችን በመጠቀም ከድርቀት መከላከል
 4. የቆሰለ እግርን እራስ ለመንከባከብ አለመሞከር፡፡ ምንም አይነት ትንሽ ቁስል ብትሆን ሆስፒታል መሄድ አለብህ፡፡
 5. በባዶ እግር መሄድን የመሳሰሉ አላስፈላጊ ባህርያትን ማስቀረት
 6. በተጨማሪም የደም የግሉኮስ መጠንን በአግባቡ መቆጣጠር
• የጨጓራ እና የአንጀት ችግር

በጨጓራ እቅስቃሴ እና አፈጫጨት ሂደት ላይ ችግር ስለሚኖር ምግብ ከጨጓራ ወደ አንጀት የሚጣራበት ጊዜ መጨመር እና በአንጀት ላይ በሚኖረው ችግር ምክንያት ደግሞ ተቅማጥ እና የሆድ ቁርጠት የተለመዱ ችግሮች ናቸው፡፡ የሆድ ድርቀት እና ተቅማጥ በተከታታይ እየተፈራረቁ ሲከሰቱ ተቅማጡ ማታ ማታ በብዛት ይከሰታል፡፡ ከነዚህ በተጨማሪም የሆድ መነፋት፣ የምግብ ፍላጎት መዘጋት፣ ማቅለሽለሽ ፣ ማስታወክ እና ትንሽ በልቶ መጥገብ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ የሆድ ችግር ካለ የአይን እና የነርቭ ችግሮችም አብረውት ይከሰታሉ፡፡

ምንም እንኳን በሽታው ለረዥም ጊዜ ከሚኖር የደም ግሉኮስ መብዛት እና ከነርቭ ችግር ጋር የተያያዘ ቢሆንም አንዳንዴ የአመጋገብ ዘይቤን መቀየር ሊረዳ ይችላል፡፡ቶሎ ቶሎ እና ትንሽ ትንሽ ለመፈጨት የሚቀሉ (ፈሳሽ) ነገሮችን መመገብ ችግን ሊቀነስ ይችላል፡፡ እንዲሁም ጮማን ከምግብህ ውስጥ ማስወገድ በጣም ጠቃሚ እርምጃ ነው፡፡ነገር ግን የደም ግሉኮስ መጠንን መቆጣጠርን የመሰለ ፍቱን መከላከያ መንገድ የለም፡፡

• የሽንት ቱቦ እና የሽንት ፊኛ ችግር

የሽንት ፊኛ ችግር ሲጀምር ሽንት ሲመጣብህ ባለማወቅ እና ሽንትሀን ስትሸና ደግሞ ሙሉ ለሙሉ ለመሽናት በማስቸገር ነው፡፡ የሽንት ፊኛ ጡንቻዎች መኮማተር በቀጠለ ቁጥር የፊኛው ሽንት የመቋጠር አቅሙም እየቀነሰ ይሄዳል ይኼም ሽንት መቆጣጠር ማቃት፣ ቶሎ ቶሎ መሽናትን እንዲሁም ተደጋጋሚ የሽንት ቱቦ ኢንፌክሽኖች እንዲኖሩ ያደርጋል፡፡ ሽንት አልወጣም ካለ ቀጭን ቱቦ የሽንት ፊኛ ውስጥ ተከትቶ እንዲወጣ ማድረግ ሊጠበቅብህ ይችላል፡፡

• ስንፈተ-ወሲብ (Erectile Dysfunction)

ስንፈተ ወሲብ በሽታው በቆየብህ ቁጥር እና እድሜህ በገፋ ቁጥር ተያይዞ ይመጣል፡፡ የአኗኗር ዜይቤን ማስተካከል፣ የተመጣጠነ ምግብ መብላት፣ ሲጋራ እና አልኮል መጠጣት ማቆም፣ ስፖርት መስራት እንዲሁም ጭንቀትን መቀነስ የብዙ ህመምተኞችን ስንፈተ-ወሲብ ሲያቃልል ይታያል፡፡ ተጨማሪ መፍትሄዎችን ሊሰጥህ ስለሚችልይኼ ችግር ካለብህ ዶክተርህን አማክር፡፡

በሴቶች ላይም ወሲብ የመፈፀም ፍላጎት መቀነስ፣ በወሲብ ጊዜ የሚኖር ህመም እና የብልት መድረቅ ሊከሰት ይችላል፡፡ ኢንፌክሽን ካለ እሱን በማከም፣ የተለያዩ የብልት ቅባቶችን( vaginal lubricants) መጠቀም እና ሆርሞኖች መውሰድ ችግሩን ይቀንሰዋል፡፡ ስለዚህ ዶክተርሽን ብታማክሪ ጥሩ መፍትሄ ታገኛለሽ፡፡

• የልብ በሽታ

የልብ ድካም፣ ድንገተኛ ሞት፣ የልብ ደም ዝውውር መገታት (MI) እና የደም ስር በሽታዎች የስኳር በሽታን ተከትለው የመከሰት እድላቸው እንደሚጨምር ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ በተለይ ደግሞ ታይፕ 2 የስኳር ህመም ያለባቸው ሰዎች ላይ ልብ ችግሮች በበለጠ ይከሰታሉ፡፡ የስኳር ህመም በሌለባቸው ሰዎች ላይ የሚኖረው እና ዋነኛው የልብ ህመም ምልክት የሆነው የደረት ህመም ስለማይኖራቸው በሽታውን ቶሎ ለማወቅ አስቸገፋሪ ያደርገዋል፡፡ በስኳር ህመምተኞችን ለዚህ ችግር ተጋላጭ ከሚያደርጉ ምክንያቶች መካከል ከመጠን ያለፈ ውፍረት( obesity)፣ የደም ግፊት፣ እንቅስቃሴ አለማድረግ፣ ሲጋራ ማጨስን መጥቀስ ይቻላል፡፡ የደም ግሉኮስ መጠንን አለመቆጣጠር ከልብ በሽታ ጋረ ያለው ግንኙነት በደንብ አይታወቅም፡፡በስትሮክ የመጠቃት እድልም ከስኳር ህመም ጋር ተያይዞ ይጨምራል፡፡

ከዚህ በመነሳት ማንኛውም የስኳር ህመምተኛ በየጊዜው የተለያዩ የልብ ምርመራዎችን ማድረግ አለበት፡፡ የአኗኗር ዘይቤን ማስተካከል፣ እንቅስቃሴ ማድረግ እንዲሁም የደም ግሉኮስ መጠንን በጥንቃቄ መቆጣጠር እንዲሁም የደም ግፊትን በየጊዜው መለካት የበሽታው የመከሰት እድል ሊቀንሱ ቢችሉም በየጊዜው የሚደረግ ምርመራን የመሰለ የመከላከያ መንገድ ግን የለም፡፡

• የቆዳ እና የጥርስ ችግሮች

የደም ግሉኮስ መብዛት ለጀርሞች ጥሩ የመራቢያ ሁኔታን ስለሚፈጥር ቆዳ እና ጥርስ በኢንፌክሽን የመጠቃት አዝማሚያ አላቸው፡፡ የጥርስ መበስበስ እና መውለቅ እንዲሁም ቆዳ ላይ የሚታዩ ቁስለቶች ከዚህ ጋር ይያያዛሉ፡፡የደም ግሉኮስ በጨመረ ቁጥርም እነዚህ ችግች ይጨምራሉ፡፡

የስኳር ህመም ህክምና ምን ይመስላል?

ታይፕ 1 የስኳር ህመም ያለባቸው ሰዎች ምንም አይነት ኢንሱሊን ስለማያመርቱ ኢንሱሊን ይሰጣቸዋል፡፡ ይኼ ኢንሱሊን በመርፌ መልክ የሚሰጥ ሲሆን አንዴ ከተጀመረ በኋላም ያለማቋረጥ መወሰድ አለበት፡፡ የታይፕ 2 ህመምተኞች ደግሞ የሚዋጡ ክኒኖች ይሰጣቸዋል፡፡ ነገር ግን ቆሽታቸው እየደከመ በሄደ ቁጥር እና ኢንሱሊን ማምረት ሲያቅተው በመርፌ የሚሰጠው ኢንሱሊን ይታዘዝላቸዋል፡፡ ምንም እንኳን መድሃኒቶቹ የስኳር ህመምን ለመቆጣጠር ዋነኛዎቹ መሳሪያዎች ቢሆኑም የአኗኗር ስርአትህን በማስተካከል ከጤነኛው ሰው በተለየ ለራስ እንክብካቤ ማድረግ አለብህ፡፡

የስኳር ህመም መድሃኒቶች ምን ችግር ያመጣሉ?

እንደማንኛውም መድሃኒት እነዚህም መድሃኒቶች የራሳቸው የሆነ ጎጂ ጎን አላቸው፡፡ ዋናው እና የመጀመሪያው የደም ግሉኮስ መጠን በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ (hypoglycemia) ነው፡፡ በተጨማሪም ውፍረት እና የኢንሱሊን መርፌ የሚወጋባቸው ቦታዎች ማበጥን ያስከትላሉ፡፡ እነዚህ ችግሮች ከሁሉም መድሃኒቶች ጋር ተያያዥ አይደሉም፡፡

የደም ግሉኮስ መጠን በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ እና የስኳር ህመም

በብዛት የታይፕ 1 በሽተኞችን የሚያጠቃ ቢሆንም ታይፕ2 በሽተኞች ላይም ይከሰታል፡፡ እራሱን በማባባስ እስከሞት ድረስ ሊዳርግ የሚችል ችግር ሲሆን መድሃኒትን በአግባቡ ባለመጠቀም አሊያም ሌሎች ምክንያቶችን ተከትሎ ይመጣል፡፡ ይኼ ችግር የሚከሰተው ኢንሱሊን በሰውነት ውስጥ ከሚገባው በላይ ሲጨምር ነው፡፡ ኢንሱሊን በስኳር ህመምተኞች ላይ በሚከተሉት ጊዜ ይበዛል፡፡

 1. ከሚያስፈልገው በላይ ኢንሱሊን ከወሰድክ፣ በሰአቱ ካልወሰድክ ወይም ትክክለኛ ያልሆነውን የመድሃኒት አይነት ከወሰድክ
 2. በሰአቱ አለመመገብ እና የምትበላውን የምግብ መጠን መቀነስ
 3. የሚያስፈልግህ የግሉኮስ መጠን ከወትሮው መጨመር ለምሳሌ ብዙ እንቅስቃሴ ማድረግ
 4. የሰውነትህ ለኢንሱሊን ያለው ምላሽ ሲጨምር፣ለምሳሌ ክብደት ከቀነስክ
 5. በሰውነትህ ውስጥ የሚመረተው ግሉኮስ መጠን መቀነስ ለምሳሌ አልኮል ከጠጣህ
 6. ኢንሱሊን ከደምህ ውስጥ የሚጣራበት ሂደት ከተጓተተ ለምሳሌ በኩላሊት ችግር ምክንያት

የደም ግሉኮስ መጠን ሲያንስ መጀመሪያ የሚጎዳው አእምሮ ነው፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ የዚህ ችግር ምልክቶች እራስን መሳት፣ ግራ መጋባት፣ የባህሪ ለውጦች እንዲሁም መንቀጥቀጥ( seizure) ያካትታሉ፡፡ በተጨማሪም የእጅ መንቀጥቀጥ፣ የልብ መምታት፣ ጭንቀት፣ ማላብ፣ ረሃብ፣የመሳሰሉ ምልክቶቸም ይኖሩታል፡፡ እነዚህ ምልክቶች ግን በስኳር ህመም በሽተኞች ላይ በብዛት ስለማይታዩ ችግሩ የከፋ እንዲሆን ያደርጉታል፡፡

በደም ውስጥ ግሉኮስ ከተገቢው በላይ እንዳይቀንስ የተለያዩ እርምጃዎችን መውሰድ ይቻላል፡፡ ይኼም እራስን በደንብ መንከባከብ እና መድሃኒትን እንዲሁም ምግብን በሰአቱ መውሰድ በተጨማሪም ከአቅም በላይ የሆነ እንቅስቃሴ አለማድረግ እና ከአልኮል መጠጥ መቆጠብን የመሳሰሉትን ያጠቃልላል፡፡

የስኳር ህመምን መዘዞችን እንዴት መከላከል እችላለሁ?

የስኳር መዘዞች ከደም የስኳር መጠን ከፍ ማለት ጋር ይያዛሉ፡፡ በደንብ ያልተቆጣጠሩት የደም ስኳር መጠን መዋዠቅ ለነዚህ ጉዳቶች ያጋልጣል፡፡ ስለዚህ የስኳር በሽተኛ ከሆንክ የተሰጠህን መድሃኒት በአግባቡ መውሰድ፣ የተመጣጠነ ምግብ መብላት እና በየጊዜው ወደ ሆስፒታል እየሄድክ የተለያዩ ምርመራዎችን በማድረግ የስኳር ህመም መዘዞችን መከላከል ትችላለህ፡፡ በተጨማሪም እንቅስቃሴ ማድረግ እና የሲጋራ እንዲሁም የአልኮል ተጠቃሚ ባለመሆን እነዚህን መዘዞች የመከሰቻ ጊዜ ልታራዝመው ትችላለህ፡፡
የስኳር ህመም በሽተኛ ሰው የሚከተለውን የአመጋገብ ስልት መጠቀም አለበት፡፡

ስብ ከአጠቃላይ ካሎሪ 20–35%
ካርቦሀይድሬት ከአጠቃላይ ካሎሪ 45–65%
ፕሮቲን 
 
ከአጠቃላይ ካሎሪ ከ10-35%
ተጨማሪ ፍራፍሬ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.