ኤች.አይ.ቪ ማለት በሽታ ተከላካይ የሆኑ ነጭ የደም ሴሎችን በተለይም ሲዲ ፎር ሊንፎሳይትስ የተባሉትን በመቀነስ ቀስ በቀስ የሰውነታችንን በሽታ የመከላከል አቅም አዳክሞ ለሌሎች ተደራራቢ በሽታዎች አሳልፎ የሚሰጥ የሰውን ልጅ ብቻ የሚያጠቃ ቫይረስ ነው፡፡

HIVአንድ ሰው ኤች.አይ.ቪ በደሙ ውስጥ መኖሩ ሊታወቅ የሚችለው በደም ምርመራ ብቻ ነው፡፡ ቫይረሱ ወደ ደሙ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ለብዙ ዓመታት እንደማንኛውም ጤናማ ሰው ሥራውን እያከናወነ መኖር ይችላል፡፡ ምንም እንኳን በኤች.አይ.ቪ የተያዙ ሰዎች ለብዙ ጊዜ የሕመም ምልክቶችና ስሜቶች ሳያሳዩ ጤናማ ሆነው ቢቆዩም ቫይረሱ በደማቸው ስለሚገኝ በቀላሉ ለሌላው የማስተላለፍ አደጋ ወይም እድል የሰፋ ነው፡፡
ስለሆነም ቫይረሱ ያለበትንና የሌለበትን ግለሰብ ያለ ደም ምርመራ ማወቅ ስለማይቻል ልቅ የሆነ የግብረ ሥጋ ግንኙነት መፈጸም ለቫይረሱ ሊያጋልጥ ስለሚችል ጥንቃቄ ማድረግ ይበጃል፡፡ ቫይረሱ ሰዎች ቀስ በቀስ የኤድስ ሕመም ስሜቶችና ምልክቶች እየታዩባቸው ሲሄዱ የኤድስ ሕመምተኛ ይሆናሉ፡፡ ኤድስ ማለት የሰውነት በሽታን የመከላከያ ኃይል/አቅም በኤች.አይ.ቪ ምክንያት በመዳከሙ የሚከሰት በሽታ ነው፡

የኤች.አይ. መተላለፊያ መንገዶች ምን ምን ናቸው ?

በሀገራችን ኤች.አይ.ቪ ከሰው ወደ ሰው በሶስት ዋና ዋና መንገዶች ይተላለፋል፡፡ ጥንቃቄ በጎደለው ልቅ የግብረ ሥጋ ግንኙነት ፤ ኤች.አይ.ቪ ካለባት እናት ወደ ፅንስ ወይም ልጅ
እና በደም አማካኝነት ማለትም በኤች.አይ.ቪ የተያዘ ሰው ደም በመጠቀም ኤች.አይ.ቪ ከሰው ወደ ሰው ሊተላለፍ ይችላል፡፡
• ጥንቃቄ የጎደለው የግብረ ሥጋ ግንኙነት ሲባል ምን ማለት ነው ?
ከጋብቻ በፊትና ከጋብቻ ውጭ የሚደረግ ማንኛውም ልቅ የሆነ የግብረ ሥጋ ግንኙነት ሁለቱም ተጓዳኞች ተመርምረው ቫይረሱ የሌለባቸው መሆኑን እስካላረጋገጡ ድረስ ያለኮንዶም የሚያደርጉት ማንኛውም የሆነ የግብረ ሥጋ ግንኙነት ጥንቃቄ የጎደለው የግብረ ሥጋ ግንኙነት ይባላል ነው፡፡
• ኤች አይ ቪ ከእናት ወደ ፅንስ ወይም ልጅ እንዴት ይተላለፋል ?
ኤችአይቪ ከእናት ወደ ፅንስ ወይም ልጅ የሚተላለፈው ኤችአይቪ ያለባት እናት በእርግዝናዋ ወቅት ፣ በወሊድ ጊዜ እና ጡት በምታጠባበት ጊዜ ኤች.አይ.ቪው ወደ ፅንሱ/ልጁ ሊተላለፍ ይችላል፡፡

ኤች.አይ. በደም አማካኝነት ከሰው ወደ ሰው እንዴት ሊተላለፍ ይችላል ?
• ኤች.አይ.ቪ በደም አማካኝነት ከሰው ወደ ሰው ሊተላለፍ ይችላል፡፡ ይህም ሊሆን የሚችለው በበርካታ መንገዶች ነው፡፡ የተለገሠ ደም ሳይመረመር ለሌላ ሕመምተኛ ከተሰጠ ፣ንጽሕናቸው ባልተጠበቀ የሕክምና መሣሪያዎች በተለይም በሕገወጥ ሕክምና መሣሪያዎች መወጋት፣ ጥርስ መነቀስ፣ ፅንስ ማቋረጥ በመሳሰሉት…በቤት ውስጥ ስለታምና ሹል ነገሮችን መርፌ፣ ወረንጦ፣ መርፌ ቁልፍ፣ መቀስ፣የጥፍር መቁረጫ፣ምላጭ ለንቅሳት የሚጠቀሙበት መሳሪያ፣ ጥርስ መፋቂያ የመሳሰሉት መሳሪያዎችን በጋራ በመጠቀም እንዲሁም በጋራ ስለታምና ሹል ነገሮችን በመጠቀም በሚፈጸሙ ጎጂ ልማዳዊ ተግባራት ለምሳሌ እንጠል በመቆረጥ፣ የሴት ልጅ ግርዛት ምክንያት፣ ጉሮሮ በማስቧጠጥ፣ ግግ በማስወጣት ኤች.አይ.ቪ በደም አማካኝነት ከሰው ወደ ሰው ሊተላለፍ ይችላል፡፡
ለኤች.አይ. የሚያጋልጡ ሁኔታዎች ምን ምን ናቸው ?
ኤች.አይ.ቪ ሁሉንም የሕብረተሰብ ክፍል የሚያጠቃ ቢሆንም የተወሰኑ ሰዎችና የኅብረተሰብ ክፍሎች ለዚህ ችግር በይበልጥ ተጋልጠው ይታያሉ፡፡ ከነዚህም ውስጥ ሴተኛ አዳሪዎችና በሥራቸው ፀባይ ከቦታ ወደ ቦታ የሚዘዋወሩ ሰዎች ይገኙበታል፡፡ ተገቢው ጥንቃቄ ካልተደረገ ማንኛውም ሰው ለኤች.አይ.ቪ የመጋለጥ እድሉ የሰፋ ነው ፡፡ ከአቅም በላይ የአልኮል መጠጦችን በመውሰድ ፣ እንደ ካናቢስ፣ ኮኬይን፣ ጫት የመሳሰሉ አደንዛዥ ዕፆችን በመጠቀም ፣ ከትዳር በፊት ወይም ከትዳር ውጪ ከተለያዩ ሰዎች ጋር በሚደረግ ጥንቃቄ የጎደለው የግብረ ስጋ ግንኙነት ፣ በአባለዘር በሽታዎች ሲያዙ ፈጥኖ ወደ ሕክምና ተቋም ባለመሄድ ፣ ባሕላዊ የሆነ ሌሎች የሚፈጸም የግብረ ሥጋ ግንኙነት ቁርኝቶች፣ለምሳሌ ዋርሳ፣ የሟች ሚስት መውረስ፣ ቅምጥ ማስቀመጥ፣ ውሽምነት ወዘተ… የመሳሰሉት ለኤች.አይ.ቪ ከሚያጋልጡ ሁኔታዎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው ፡፡
ኤች.አይ. የማይተላለፍባቸው መንገዶች የትኞቹ ናቸው ?
ኤች.አይ.ቪ የማይተላለፍባቸውን መንገዶች ጠንቅቆ ማወቅ ተገቢ ነው፡፡ ምክንያቱም በቫይረሱ ልያዝ እችላለሁ በሚል ፍራቻ ብቻ ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩትንና የኤድስ ሕሙማንን ከማግለል ባሻገር ራስን ከማኅበራዊ ግንኙነቶች የማራቅ አዝማሚያ ሊከሰት ስለሚችል ነው፡፡ኤች.አይ.ቪ ከማይተላለፍባቸው መንገዶች ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው፣
• አብሮ በመስራት፣ አብሮ በመብላትና በመጠጣት
• ጉንጭ ለጉንጭ በመሳሳም ፣
• እጅ ለእጅ በመጨባበጥ፣
• በትንፋሽ /ጎን ለጎን በመቀመጥ ወይመ በማውራት/፣
• በመፀዳጃ ቤት፣ በመዋኛ ገንዳ /አካባቢ/፣ በሕዝብ ገላ መታጠቢያና ሌሎችንም መሰል መገልገያዎች በጋራ በመጠቀም፣
• በትንኝ፣ ቁንጫና ቅማል በመነከስ፡፡

ለማሳወቅ ያህል ኤች.አይ.ቪ ከሰው አካል ውጭ ለብዙ ጊዜ መቆየት የማይችል ስለሆነ ከአንዱ ወደ ሌላው ሰው ለመተላለፍ ቀጥተኛ ንክኪን ይጠይቃል፡፡ ኤች.አይ.ቪን በተመለከተ ቀጥተኛ ንክኪ ማለት በተለይም ቫይረሱ ያለበት ሰው ደም ወይንም የብልት ፈሳሾች ከሌላው ጤነኛ ሰው ደም ጋር የሰውነት ቆዳ ቁስል /የቆዳ ክፍተት/ ባለበት ሁኔታ ሲነካካ ማለት ነው፡፡

አብዛኛውን ጊዜ በቀጥተኛ ንክኪ ሊከሰት የሚችለው ጥንቃቄ በጎደለው የግብረ ሥጋ ግንኙነት፣ ስለታምና ሹል በሆነ መሣሪያዎችን በጋራ በመጠቀም እንዲሁም ቫይረሱ ካለባት እናት ወደ ፅንስ/ልጅ በመተላለፉ ሁኔታ ብቻ ነው፡፡ ቫይረሱ ያለበት ደም የሚለገስ ቢሆን ኖሮ ይህም ቀጥተኛ የደም ንኪኪ የሚያስከትል ነው፣ ይሁን እንጂ በሀገራችን ያልተመረመረ ደም ለሕሙማን ስለማይሰጥ ኤች.አይ.ቪ በዚህ መንገድ የመተላለፍ እድሉ የመነመነ ነው፡፡

የኤች.አይ./ኤድስ የሕመም ስሜቶችና ምልክቶች ምን ምቹ ናቸው ?
የኤድስ የሕመም ስሜቶችና ምልክቶች የሚባሉት በዋናነት የሰውነትን የበሽታ መከላከያ ኃይል መዳከም ተከትለው ሊከሰቱ የሚችሉ የሌሎች የተለያዩ ተደራራቢ በሽታዎች የሕመም ስሜቶችና ምልክቶች ስለሆኑ እዚህ ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል፡፡ አንድ ሰው የኤድስ ሕመምተኛ ሊባል የሚችለው ከእነዚህ የሌሎች በሽታዎች የህመም ስሜቶችና ምልክቶቹ መከሰት በተጨማሪ ኤች.አይ.ቪ በደሙ ውስጥ መኖሩ በደም ምርመራዎች ሲረጋገጥ ጭምር መሆኑን ልብ ልንለው ይገባል፡፡

የሰውነት በሽታን የመከላከል አቅም እየተዳከመ ሲሄድ የተለያዩ በሽታዎች የሕመም ስሜቶችና ምልክቶች መታየት ይጀምራሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል ዋነኞቹ ከዚህ በታች የተዘረዘሩት ሲሆኑ
• የሰውነት ክብደት በአጭር ጊዜ ውስጥ መቀነስ
• አንድ ወርና ከዚያም በላይ የሚቆይ ተቅማጥ ፣
• ከአንድ ወር በላይ የሚቆይ ትኩሳት ፣
• በቀላሉ የሚድኑ በሽታዎች በተደጋጋሚ መታየት፣ ቶሎ አለመዳን ፣
• የሰውነት እጢዎች /በአንዳንድ አካባቢዎች ፍርንትት ይባላል/ መቆጣትና ማበጥ ፣
• የነርቭ የአእምሮ መታወክ ፣
• በአፍና በጎሮሮ አካባቢ ቁስለት ፣
• በሳምባ ነቀርሳ /ቲቢ/ መጠቃት፣
• በብልት ላይና አካባቢ የሚታይ ኪንታሮት እና ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ቁስል ፣
• የቆዳ በሽታ /በተለምዶ አልማዝ ባለጭራ የሚባለው ፣የቆዳ ካንሰር፣

እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት የኤድስ የሕመም ምልክቶችና ስሜቶች የኤድስ ሕመምተኛ ያልሆነ ሰውም በሌላ በሽታ በሚታመምበት ወቅት ሊታዩ እንደሚችሉ መዘንጋት የለበትም፡፡ ቫይረሱ ወደ ሰውነት ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ከላይ የተዘረዘሩት የኤድስ የሕመም ስሜቶችና ምልክቶች እስኪታዩ ድረስ ከ3 እስከ 12 ዓመታት ሊወሰድ ይችላል፡፡ ከዚህም በመነሳት ሁለት ነገሮችን ማወቅ ይገባል፡፡

አንድ ሰው ዛሬ ኤች.አይ.ቪ ተያዘ ማለት ወዲያውኑ የአልጋ ቁራኛ ይሆናል ማለት ሳይሆን እንደማንኛውም ሰው እየሠራ ለብዙ ዓመታት ከቫይረሱ ጋር መኖር ይችላል፡፡ በደም ምርመራ እስካልተረጋገጠ ጊዜ ድረስ በአይን በማየት ብቻ ቫይረሱ በደሙ ውስጥ ያለበትን ወይንም የሌለበትን ሰው ማወቅ አይቻልም፡፡ አንድን ግለሰብ እንዲሁ በዓይን በማየት ከቫይረሱ ነፃ ነው ብሎ በመገመት ወሲባዊ ግንኙነት መፈጸምም ለኤች.አይ.ቪ ራስን ማጋለጥ ስለሆነ ማንኛውም ሰው ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርበታል፡፡
የቫይረሱን ስርጭት እንዴት መከላከልና መቆጣጠር ይቻላል ?

• ከጋብቻ በፊት እንዲሁም ከጋብቻ ውጭ የግብረ ሥጋ ግንኙነት አለማድረግ፣ /መታቀብ/ ከሁሉም በላይ ለኤች.አይ.ቪ ከመጋለጥ ያድናል፣

• በምርመራ ከቫይረሱ ነፃ በሆኑ ሁለት ተቃራኒ ፆታዎች መካከል የሚደረግ በመተማመን ላይ የተመሠረተ ለዘለቄታ የአንድ ለአንድ የተጣጣመ ወሲባዊ ግንኙነት፣

• ከጋብቻ በፊትና ከጋብቻ ውጭ በተለያዩ ምክንያቶች የግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚደረግ ከሆነ ኮንዶምን ሁልጊዜ በትክክለኛው መንገድ መጠቀም ፣

• ከቤተሰብ አባላት ማን ኤች.አይ.ቪ እንዳለውና እንደሌለው ያለምርመራ ለማወቅ ስለማይቻል፣ ስለታምና ሹል ዕቃዎችን በጋራ አለመጠቀም፣ በተለይም በቤት ውስጥ ወላጆችና ልጆች የሚጠቀሙባቸውን ምላጭ፣ መርፌ፣ ወረንጦ ወዘተሯ መለየት፣

• የጥርስ ቡሩሾችና መፋቂያዎች በጋራ አለመጠቀም ፣

• ሕጋዊነታቸው በማይታወቅ የህክምና ተቋማት አለመታከም ፣

• ለኤድስ ሕመምተኛ እንክብካቤ በሚሰጥበት ወቅት ከሰውነት ፈሳሽ ጋር ንክከ እንዳይኖር በአካባቢው የሚገኘውን ቁሳቁስ ለምሳሌ የእጅ ጓንት፣ ፊስታል ፤ፕላስቲክ፣ ደረቅ ጨርቅ፣ ወፍራም ቅጠል ወዘተ መጠቀም፣

• ማናቸውንም ጎጂ ልማዳዊ ተግባራት በማስተማርና በሕጋዊ መንገድ መከላከል ፣

• በቫይረሱ መያዛቸውን ያወቁ ወይም የተገመቱ እናቶች /ከእርግዝና በፊትም ሆነ በኊላ/ ወደ ሕክምና ባለሙያ በመሄድ የምክር አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ መምከር፣ ማበረታታት፣ ለባለቤቶቻቸው ነግረው እንዲያስመረምሩ ማድረግ ይጠቅማል፣

• ከቫይረሱ ጋር ለሚኖና በኤድስ ሳቢያ ደጋፊ ላጡ ወገኖች በቤተሰብም ሆነ በኅብረተሰብ ደረጃ ሳይገለሉ ፍቅርና ርህራሄ የተሞላበት ድጋፍ መስጠት፣ ራሳቸውን የቻሉ ዜጎች እንጂ ጥገኞች አድርጎ አለመመልከት፣ የጥገኝነት ስሜት እንዲያሳድሩ አለመገፋፋት፣

• በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ስለኤች.አይ.ቪ/ኤድስ የሚያውቁትን ለሌሎች ማጋራት፣ ያላወቁትን በውይይት ማዳበር፣ ስለኤች.አይቪ መተላለፊያ መከላከያ ዘዴዎች በግልጽ እንዲነገር ማድረግ ፣

• በቤተሰብ አባላት መካከል ኤች.አይ.ቪና ሌሎች አባላዘር በሽታዎች አስመልክቶ ግልጽ ውይይት የማድረግ ልምድ እንዲዳብር መጣር ፣

• ሌሎች የአባለዘር በሽታዎች ሲከሰቱ ፈጥኖ ሕክምና ተቋም መሄድና የታዘዙትን መድኃኒቶች በአግባቡ መውሰድና የወሲብ ተጏዳኙም ተገቢውን ሕክምና እንዲያደርግ መገፋፋት፡፡

ኤች.አይ. ከእናት ወደ ጽንስ/ልጅ እንዳይተላለፍ የመከላከያ ዘዴዎች

• ከጋብቻ እና ከእርግዝና በፊት የኤች.አይ.ቪ ምርመራ ማድረግን መምከር ፣

• ከቫይረሱ ጋር የምትኖር እናት መምከር፣የወሊድ መከላከያ ዘዴ እንድትጠቀም መምከር

• አርግዛ ከተገኘች ወደ ፅንስ እንዳይተለለፍ የሚከላከል መድኃኒት እንድትወስድ መምከር፣ መድኃኒቱ ወደሚኝበት ጤና ድርጅት መምራት ፣

• በወሊድ ጊዜ በአቅራቢያው ወደሚገኘው የጤና ድርጅት መሄድ እንዳለባት መምከርና ማበረታታት ፣

• ሕፃኑ ከተወለደ በኊላ የሚቻል ከሆነ በጡት ወተት ምትክ የላም ወይም የፍየል ወይም ሰው ሠራሽ ወተት /ፎርሙላ ወተት/ ለመስጠት መሞከር ካልተቻለ የጡት ወተት ብቻ ስድስት ወር ለማይበልጥ ጊዜ መስጠት፣ ከዚያ ጨርሶ አለማጥባትን ማስረዳት ፣ ከስድስት ወር በኊላ ተመጣጣኝ ምግብ ማስጀመርን መምከር፡፡
በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ የምክርና የኤች.አይ. የደም ምርመራ አገልግሎትጥቅሞች ምን ምንድን ናቸው ?
• ተመርምረው ቫይረሱ የሌለባቸው ሰዎች በበለጠ ጥንቃቄ ጥሩ ሕይወት እንዲመሩ ያስችላቸዋል፣

• ጥርጣሬ/ጭንቀት ለማስወገድ ይረዳል

• ውጤትን በፀጋ ተቀብሎ ከቫይረሱ ጋር እንዴት አብሮ መኖር እንደሚቻል ለማወቅ ፣
• ለኤች.አይ.ቪ የሚያጋልጡትን የግል ባሕሪያት ለይቶ በማወቅ ዘለቄታ ያለው የባሕሪይ ለውጥ ለማምጣት ፣

• ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ ሰዎች የራሳቸውን ጤንነት ለመጠበቅ ለጤና ጠንቅ ከሆነ ነገሮች እንዲርቁ ለማድረግ፣ ለምሳሌ ጥንቃቄ የጐደለው የወሲብ ተግባራት ከአልኮልና ሌሎች አደጋ ከሚጋብዙ አደንዛዥ ዕፆች ወዘተ…
•ቫይረሱን ለሌላው ወገን ላለማሰራጨት ፣
• የሕክምና ክትትል ለማድረግ ፣
• የወሊድም ሆነ ለሌሎች ተላላፊ በሽታዎች የመከላከያ መድኃኒቶችን ለመጠቀም
• የወደፊት ዕቅድን ለማስተካከል ፣
• ድጋፍ የሚሹ ግለሰቦችን ድጋፍ ማግኘት የሚችሉበትን ሁኔታዎች ለማመቻቸት
• የኤች.አይ.ቪን ከእናት ወደ ፅንስ/ልጅ የመተላለፉን ሁኔታ የመከላከል ስራዎችን ለመስራት ፣
• ኤች.አይ.ቪ/ኤድስን እንደማንኛውም ሌሎች በሽታዎች በመቁጠር ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩትንና የኤድስ ሕሙማንን የማግለል ሁኔታ ለመቀነስ፡፡

ኮንደምን በተመለከተ

ኤች.አይ.ቪን ለመከላከል በዋናነት መታቀብ፣ ከዚያ ባሻገር ተመርምሮ መጋባት አስተማማኝ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ የግብረሥጋ ግንኙነት ካስፈለገ ግን ኮንዶም ሁሌም መጠቀም የመጨረሻው አማራጭ ነው

ኮንደም ኤች.አይ.ቪ/ኤድስን ለመከላከልና ሌሎች አባላዘር በሽታዎችንና ያልተፈለገ እርግዝናን ይከላከላል ፣
የኮንደምን የመከላከል ብቃት የሚቀንሱ ዋና ዋና ምክንያቶች መካከል የአገልግሎት ዘመኑ ያለፈበትን መጠቀም ፤ የኮንደም ማሸጊያ መቀደድ ፤ሙቀት /የአካባቢና የሰውነት ሙቀት/ ባለበት ቦታ ኮንደምን ማስቀመጥ፣ ለምሳሌ፣ በኪስ ውስጥ ለረጅም ጊዜ መያዝ፣ ለፀሐይ መጋለጥ፤ በግንኙነት ጊዜ የኮንደም መቀደድ፤ ከግንኙነት በኊላ በሴቷ ብልት ውስጥ ሲቀር

ኮንደምን ከመጠቀም በፊት መወሰድ ያለባቸው ጥንቃቄዎች

በቅድሚ የኮንዶሙ ማሸጊያ ደህና መሆኑን ማረጋገጥ፣ ማስገንዘብ፣

በማሸጊያው ላይ የተጻፈውን የመጠቀሚያ ጊዜ ጽሑፍ ጊዜው አለማለፉን አንብቦ ማረጋገጥ፣

በአውሮፓውያን አቆጣጠር ተጽፎ ከሆነ ስምንት ዓመት በመቀነስ በኢትዮጵያ አቆጣጠር እስከመቼ ድረስ አገልግሎት እንደሚሰጥ መረዳት መቻል፣

ኮንዶሙን ከእሽጉ ለማውጣት በተዘጋጀው ቦታ ምልክት መቀደድ እንዳለበት ማስረዳት

የተበላሸ ኮንዶም ከነማሸገያው ሊወይብ/ቀለሙ ሊለወጥ ስለሚችል በጥንቃቄ ማየት እንደሚገባ ማሳወቅ፣ በዚህ ሁኔታ ያለውን አለመጠቀም ማስረዳት፣

ኮንዶሙ ከአያያዝ ጉድለት መተንፈሱን ለማረጋገጥ በሁለት ጣቶች ይዞ ጫን ሲደረግ መልሶ እንደሚገፋና መጠቀም እንደሚቻል ማስረዳት፣

የተነፈሰ ኮንዶም መልሶ እንደማይገፋ /ጠርመስ ብሎ እንደሚቀር/ አለመጠቀምን ማስረዳት፣

ከመጠን በላይ ከተወጠረ የብልሽት ምልክት ሊሆን ስለሚችል በዚህ ሁኔታ ያለውን ኮንዶም መጠቀም ትክክል እንዳልሆነ ማብራሪያ መስጠት ፣

እሽጉን ለመቅደድ በመቀስ ወይም በምላጭ በመጠቀምና በጥፍር መጠቀም ኮንዶሙን እንደሚጐዳ ማወቅ

ኮንደሙን ከማሸጊያው በእጅ ጣት ቀዶ ማውጣት ፣

ቅባት የሌለው ኮንዶም የተበላሸ መሆኑን ማወቅ ፣

ኮንዶሙን በወንድ ብልት ከማጥለቁ በፊት በሁለት ጣት የኮንደሙን ጫፍ ጫን አድርጐ አየሩን ማስወጣት ኮንደሙን እንዳይቀደድ የሚረዳ መሆኑን ማወቅ ፣

በጫፍ ላይ ያለው ቦታ ለወንድ አባለዘር ማጠራቀሚያ የሚገለግል መሆኑን መረዳት ፣

የወንድ የዘር ፍሬ ከፈሰሰ በኊላ ብልቱ ሳይሟሽሽ ከሴት ብልት ማውጣት እንደሚገባ ማወቅ

የወንድ ዘር ፈሳሽ ከኮንደሙ ወደ ውጪ እንዳይፈስ ተጠንቅቆ ኮንደሙን በጥንቃቄ ከወንድ ብልት ማውለቅና መቋጠር እንዳለበትና እጅ ላይ ቁስል ካለ ጥንቃቄ መወሰድ

አንድ ኮንዶም የሚያገለግለው ለአንድ ጊዜ ብቻ መሆኑን ማወቅ ፣ የተጠቀሙበት ኮንዶም ሕፃናት እንዳይጫወቱበት፣ከሌላ ቆሻሻ ጋር በማድረግ ማቃጠል፣በውሃ የሚጸዱ ሽንት ቤቶች እንዳይደፈን አለመክተትናኮንዶም በሚገባ ከተወገደ በኊላ እጅን በሳሙና መታጠብ አለመዘንጋት

ጎጂ ልማዳዊ ተግባራትና ኤች.አይ./ኤድስ
በሀገራችን በተለያዩ አካባቢዎች የሚዘወተሩ ጎጂ ልማዳዊ ተግባራት /ለምሳሌ እንጥል ማስቆረጥ፣ የሴት ልጅ ግርዛት፣ ጉሮሮ ማስቧጠጥ፣ ግግ ማስወጣት ወዘተ./ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ሥርጭትና ለሚያስከትለው ጉዳት መባባስ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ፡፡
እነዚህ ተግባራት በቀጥታ የኤች.አይ.ቪ መተላለፊያ መንገዶች ሲሆኑ ከዚህ በተለየ ደግሞ ከትዳር ውጪ ባሕላዊ የወሲብ ትስስር /ዋርሳ፣ የሟች ሚስት መውረስ ቅምጥ ወዘተ/ ያለእድሜ ጋብቻ፣ አስገድዶ መድፈርና ጠለፋ ወጣት ሴቶች ወደማያምኑበት የግዴታ ትዳር ገብተው ለቫይረሱ እንዲጋለጡ ሊያደርግ የሚችሉ ልማዶች ናቸው፡፡ በዚህ መንገድ ተገደው ትዳር የያዙ ወጣት ሴቶች ኮብልለው ወደ ከተማ ሊገቡና በሴተኛ አዳሪነት ኑሮ ላይ ሊሠማሩም ስለሚችሉ በቀላሉ ለኤች.አይ.ቪ በመጋለጥ ቫይረሱን ሊያስፋፉ ይችላሉ፡፡
በባህላችን ውስጥ ጎጂ ልማዳዊ ተግባራት ብቻ ሳይሆኑ በርካታ ጠቃሚ ልማዶችም እንዳሉ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ ያህል ዘመድ ከዘመድ የመረዳዳቱ፣ በድንግልና እስከ ጋብቻ የመቆየቱ የመሳሰሉት የቆዩ ባህላዊ ልማዶች ኤች.አይ.ቪ/ኤድስን ለመቆጣጠር ታላቅ ድጋፍ የሚሰጡ ስለሆነ መጎልበት ይኖርባቸዋል፡፡

በኤች.አይ.ቪ/ኤድስ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ድጋፍና እንክብካቤ መስጠት፣

ከቫይረሱ ጋር ለሚኖሩ ወገኖችና የኤድስ ህሙማን ሳይገለሉ ፍቅርና ርህራሄ በተሞላበት የሚረዱበትን መንገድ ማመቻቸት እንዲሁም ማበረታታት ፣

ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ ወገኖች ማንኛውም የህመም ስሜት ሲኖራቸው በቅርብ በሚገኘው ጤና ድርጅት ሄደው ሕክምና እንዲያደርጉ መምከር፣ ማበረታታት፣

የኤድስ ሕሙማን የታዘዙላቸውን መድኃኒቶች ሳያቋርጡ በአግባቡ እንዲወስዱ ማበረታታት ፣ መከታተል፣
ከቫይረሰ ጋር ለሚኖሩ ወገኖችና የኤድስ ህሙማን የስነ-ልቦና ድጋፍ መስጠት፣ ማበረታታት፣ ወይም በጤና ተቋማት/በቀበሌ ውስጥ በኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ዙሪያ የሚሠሩና የምክክር አገልግሎት የሚሰጡ ካሉ ወደ እነርሱ መምራት ፣
በኤድስ ሳቢያ ወላጅ አልባ የሆኑ ህፃናት በሕብረተሰብ አቀፍ ማህበራዊ ድርጅቶች በኩል ድጋፍ ማግኘት እንዲችሉ መርዳት ፣

በአባላዘር በሽታዎች የተያዙ ሰዎች ወደ ህጋዊ ህክምና ድርጅት ቀርበው ቶሎ ህክምና እንዲያገኘ እና ፍቅረኛቸውን/የወሲብ ጓደኛቸውንም እንዲታከሙ ማበረታታት ፣

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.