ባህላዊ ዕውቀትም ይሁን ዘመናዊ ሳይንስ ያገቡ ሰዎች ከወንደላጤዎች የተሻለ ረጅም ዕድሜ እና ጤንነት እንዳላቸው ይገልፃሉ፡፡

“ከላጤዎች ጋር ሲነፃፀር ባለትዳሮች ጤናማዎችና እና ለረጅም ዘመን ለመኖር የታደሉ ናቸው” ይላሉ በካሊፎርነያ ዩኒቨርስቲ ሳይኮሎጂስት የሆኑት ዶክተር ቴዎዶር ሮቤልስ፡፡ “ጥናቶች እንደሚያሳዩት ባለትዳሮች በተለይ ወንዶች ረዘም ላለ ዕድሜ ይኖራሉ፡፡ በልብ በሽታዎች የተነሳ የመሞት ዕድላቸው ከላጤዎች ሲተያይ ያነሰ ነው፡፡ ጤናማ ሰዎች ትዳር የመመስረት ፍላጎት አላቸው” በማለት ትዳር ጤናማ የማድረግ አቅም እንዳለው ይገልጻሉ፡፡
“የሚረዳዱና የሚተጋገዙ ጥንዶች ጤናማነታቸው ከግንኙነታቸው ጋር ተያያዥነት አለው” ይላሉ የኦሃዮ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ባልደረባዋ ዶክተር ጃኒስ ኪኮልት ግላሰር፡፡
ትዳር ለጤና በምክንያት
የጥሩ ባህርይ ባለቤት ያደርጋል

ጥንዶች በትዳር ሲጣመሩ በአደንዛዥ ዕፅ፣ በሲጋራ፣ እና በሌሎች ለጤና ጎጂ በሆኑ ነገሮች የሚደርሰባቸው ጉዳት እየቀነሰ ይሄዳል፡፡
“አብረው ለመኖር ሲስማው በፈቃደኝነትም ይሁን በትዳር አጣማሪያቸው ጉትጎታ ከነዚህ ሱሶች ስለሚታቀቡ ወይንም አወሳሰዳቸውን ስለሚቀንሱ የሚከሰት ነው” ይላሉ በኦሃዮ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ሳይኮሎጂስት እና ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ክርስቶፈር ፍገንደስ፡፡

ማህበራዊ ግንኙነት
“ባለትዳር ከሆንክ/ሽ እስከ አሁን ከፈጠርካቸው/ ሻቸው ግንኙነቶች በጣም መቀራረብ የሠፈነበት እንደሆነ ትረዳለህ/ሽ፡፡ ይህ ማለት በማንኛውም ወቅት የምትፈልገውን/ጊውን እገዛ እና ድጋፍ ሊያደርግልህ/ ሽ የሚችል ሰው አለህ/ሽ ማለት ነው፡፡” ይላሉ ዶ/ር ጃኒስ፡፡
“በሌላ በኩል ደስተኛ ያልሆኑ ሰዎች ከማህበራዊ ኑሮ የተገለሉ ይሆናሉ፡፡ ይህም ወደ ድብርት ይመራቸዋል፡፡ የጤንነታቸውን ሁኔታም አይከታተሉም” ሲሉ በኒው ዮርክ ዩኒቨርሲቲ ሳይኪያትሪስት የሆኑት ዶክትር ሱዴፕታ ቫርማ ይናገራሉ፡፡

ጤናማ ልምዶችን ያዳብራሉ
ባለቤትዎ ጤናማ ልምዶችን እንዲያዳብሩ ሊረዱዎ ይችላሉ፡፡ “ባለቤትዎ በእርስዎ ባህርይ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ያሳድራሉ፡፡ ይህን መመገብ የለብህም/ሽም፤ አልኮል ቀንስ/ሺ ወዘተ የሚሉት ከዚህ በጎ ተፅዕኖ የሚመነጩ ናቸው” ይላሉ ዶክተር ቴዎዶር ሮቤልስ፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በትዳራቸው ደስተኛ የሆኑ ሰዎች የዶክተሮቻቸውን ትዕዛዝ እንደሚያከብሩ አንድ ጥናት ይገልፃል፡፡
ከሚወዱት ሰው ጋር ለረጅም ጊዜ መኖርዎ ሌሎች የጤና ጠቀሜታዎችም አሉት፡፡ “አብዛኞቻችን ከፍቅረኞቻችን ጋር ለመዝናናት መኖራችን በጎ ጎን አለው፡፡ በትዳር ተጣምሮ መኖር ከሚያስገኘው ጋር ሲወዳደር ግን አነስተኛ ነው” ዶክተር ክርስቶፍር “ከትዳር የምናገኘው ፍቅርና መተጋገዝ ለራሳችን የምንሰጠውን እንክብካቤ እንዲጨምር ያደርጋል፡፡ ይህ የሚሆነው የትዳር ተጣማሪያችን በኛ ደስተኝነት ላይ የማይተካ ሚና ስላለው ነው” በማለት ዶክተር ቫርማ የትዳር ጥቅም ከፍተኛ እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡
ቀለበት ማጥለቅ ብቻውን በቂ አይደለም፡፡ የተሻለ ትዳር ማለት የተሻለ ጤና ማለት ነው፡፡ የልብ ቀዶ ጥገና ከተደረገላቸው በሽተኞች ውስጥ በጥሩ ትዳር ውስጥ ያሉት የመዳን ዕድላቸው ከሌሎቹ የተሻለ እንደሆነ ከ15 ዓመታት በላይ የተካሄደ አንድ ጥናት ያስረዳል፡፡ ፍቅርና ደስታ በራቀው ትዳር ውስጥ የሚኖሩ በሽተኞች የመዳን እና በቶሎ የማገገም ዕድላቸው ዝቅተኛ እንደሆነም ጥናቱ ሳይጠቅስ አላለፈም፡፡

ለዚህ የተሰጠው ዋነኛ ምክንያት መጥፎ ትዳር ለከፍተኛ ጭንቀት የሚዳርግ በመሆኑ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የበሽታ መከላከል አቅምን ክፉኛ ያዳክማል፡፡ በተለየ ሴቶች ለዚህ ዓይነቱ ጭንቀት ተጋላጭ ናቸው፡፡ በትዳር ላይ በሚጋጥም ጥላቻ (ያለ መወደድ ስሜት) ሴቶቹ ስሜተ ስስ መሆናቸው ለችግር አጋልጧቸዋል
ይላሉ ዶክተር ጃኒስ፡፡

ዶክተር ጃኒስ እና የጥናት ቡድናቸው በምርመራክፍሎች ውስጥ ጥንዶች ባስቀመጡት ስውር ካሜራ ሲጨቃጨቁ ሁኔታውን በመቅረፅ ለማጥናት ሞክረዋል፡፡ “በክርክርና ባለመስማማት ወቅት ጥላቻን የሚያሳዩ ጥንዶች ጭንቀትን የሚያባብሱ ሆርሞኖች መጨመር ታይቶባቸዋል፡፡ የቃላት መቋሰሉ ከፈጠረው ህመም ለመዳንም ብዙ ጊዜ ይወስድባቸዋል” ብለዋል፡፡
ጠቅለል ተደርጐ ሲቀመጥ ከባድ የትዳር ችግር ያለባቸው ሰዎች የበሽታ መከላከል አቅም ሊዳከም ይችላል፡፡ የትዳር የጤናማነት ሁኔታ ወንዶችንም የጤና ችግር ሊያስከትልባቸው ይችላል፡፡

“በጥናታችን እንደደረስንበት ከሆነ ድብርት፣ አለቅጥ ክብደት መጨመር እና ከፍተኛ የደም ግፊት ደስተኛ ባልሆነ ትዳር ውስጥ በሚኖሩ ሴቶች ላይ ይታያሉ፡፡ ነገር ግን ወንዶች ትዳራቸው በሚፈጥርባቸው ብስጭት የአደንዛዥ ዕጾች ሱሰኛ ከሆኑ ተመሳሳይ የጤና ጉድለት ሊያገጥማቸው ይችላል” ሲሉ ዶክተር ቫርማ የችግሩን ስፋት ያስረዳሉ፡፡ እንደሳቸው እምነት ሁለቱም ፆታዎች ደስታ የራቀው ትዳር በሚያስከትላቸው አለመመቸቶች ይጠቃሉ፡፡ ይሁንና የሚያሳዩት የጉዳት መጠን ግን የተለያየ ነው፡፡
ብቸኞች

አንድ ሰው ብቸኛ (single) ነው ሲባል ከሌሎች ጋር የቅርብ ወዳጅነት መመስረት አይችልም ማለት አይደለም፡፡ ሌሎች ደግሞ ለፍቅር የሚሆናቸውን ሰው ባለማግኘታቸው ብቸኛ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ለዚህ ዋነኛው መፍትሔ ጥሩ ጓደኞችን ማፍራት ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ሊያስቡልዎና ሊጠነቀቁልዎ እርስዎም ተመሳሳዩን ሊያደርጉላቸው ይችላሉ፡፡ ይህ ዓይነቱ ራስን በጥሩ ሰዎች መሃከል ማኖር ትዳራቸውን በፍቺ ለበተኑ ሰዎችም ይሠራል፡፡

ፍቺ ካለዕድሜ ከመሞት ጋር ተያያዥነት እንዳለውና በተለይ በወንዶች ላይ በስፋት እንደሚታይ የአሪዞና ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ዶክተር ዴቪድ ስባራ ይናገራሉ፡፡ “በዕድሜ በሰል ካሉ ሰዎች ውስጥ ከፍቺ በኋላ በደስታ የተሞላ ህይወት ሲመሩ የሚታዩ ይኖራሉ፡፡ ደስታ በራቀው ትዳር ውስጥ ካሉና ትዳርዎ እንዲሠራ የሚችሉትን ያህል ከለፉ በኋላ ተስፋ እንደሌለው ካወቁ ፍቺ ምክንያታዊና አምነን መቀበል ያለብን አማራጭ ይሆናል፡፡ ተፋትተው ደስተኛ ሆነው መኖር ከቻሉ ፍቺ የሚያመጣቸው ጐጂ ጐኖች ሊያሳስብዎ አይገቡም” ይላሉ ዶክተር ዴቪድ፡፡

ከፍቺ በኋላ ሴቶች ከወንዶች በተሻለ መልኩ ጥሩ ስሜት ሊሰማቸው ይችላል፡፡ “ላጤዎችን እና የጤናቸውን ሁኔታ ስናይ ሴቶቹ ከወንዶቹ በተሻለ ጤንነት ላይ ይገኛሉ፡፡” የሚሉት ዶክተር ክርስቶፈር ባለትዳሮች ወይንም አብረው የሚኖሩ ፍቅረኞች ለመስማማት በማይችሉበት ወቅት በአክብሮት ያለ ዘለፋ እንዲነጋገሩ ይመከራል፡፡ ጥላቻ በከፍተኛ ሁኔታ የሚንፀባረቅበት ክርክርና ጭቅጭቅ ለጤና ጉዳት ያጋልጣል፡፡ በተገቢው ሁኔታ መነጋገር ሲባል ማዳመጥ፣ መስጠት፣ ቅድሚያ መስጠት እና የተናጋሪውን ስሜት መረዳትን ያጠቃልላል፡፡ በሰው ልጆች ውስጥ ያለው ትልቁ ፍላጐት ለመወደድ መንሰፍሰፍ ሲሆን እውቅና ማግኘት ደግሞ ሌላው ነው፡፡ ይህን ካደረጉ “እያዳመጥኩህ/ሽ ነው” የሚል መልዕክት ያስተላልፋሉ፡፡ ይህ አይነቱ መተሳሰብ የትዳር ችግሮቻችሁን በቀላሉ ለመፍታት እና ለመስማማት ያስችላችኋል፡፡

ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ ታትሞ ወጥቶ ነበር

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.