በ  ታደሰ ገብረማርያም

c8941629757be3adf5da03297576b409_Lበመላው ዓለም በጉበት በሽታ (ሄፒታይተስ) በየዕለቱ አራት ሺሕ ሰዎች፣ በዓመት ደግሞ 1.5 ሚሊዮን ሰዎች ለሕልፈተ ሕይወት ይዳረጋሉ፡፡

በኢትዮጵያ ደግሞ ወደ አሥር ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች የቫይረሱ ተጠቂ ይሆናሉ ተብሎ እንደሚታሰብ ዶ/ር ብርሃኔ ረዳይ የኢትዮጵያ ጋስትሮንትሮሎጂ አሶሴሽን ፕሬዚዳንት አስታወቁ፡፡

በዓለም ለአምስተኛ በኢትዮጵያ ደግሞ ለሦስተኛ ጊዜ ሐምሌ 21 ቀን 2007 ዓ.ም. ተከብሮ የዋለውን የዓለም የጉበት በሽታ ቀንን አስመልክተው የአሶሴሽኑ ፕሬዚዳንት በተለይ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በዓለም ላይ ይህን ያህል የሚገድል ሌላ ተላላፊ በሽታ የለም፡፡ በአንዳንድ ጥናቶች ላይ እንደተመለከተው ከሆነ ኤችአይቪ፣ ቲቢ እና ወባ አንድ ላይ ተደምረው ሄፒታይተስ የሚገድለውን ያህል አይገድሉም፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ የቫይረሱ ተጠቂዎች ብዛት ሊታወቅ የቻለው በጥናት ላይ በተመረኮዘ ዳሰሳ ሳይሆን የኤክስፐርቶች ግምት መሆኑን ጠቁመው፣ ግምቱም የተሠራው የሌሎች አገሮችን ተመሳሳይ አኗኗር ዘዴ፣ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥና ውስን የሆኑ ጥናቶች በመመርኮዝ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ማኅበሩ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በዚሁ በሽታ ዙሪያ ላይ ትኩረት ያደረገ አገር አቀፍ የዳሰሳ ጥናት ለማካሄድ ተስማምቷል፡፡ ይህም የዳሰሳ ጥናት በሚቀጥለው ዓመት ይጀመራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ጋስትሮንትሮሎጂ ማለት የምግብ ማንሸራሸሪያና ማዋሃጃ አካላት መሆኑንና ይህም የምግብ መውረጃ ቱቦን፣ ጨጓራን፣ ቆሽት፣ ሀሞት ከረጢት፣ ጉበት፣ ትንሹንና ትልቁን አንጀቶች ያካተተ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ሄፒታይተስ ‹‹ሲ››ን ማዳን፣ ሄፒታይተስ ‹‹ቢ››› ደግሞ ተከትቦ መከላከል ይቻላል፡፡ ስለዚህ ልንቆጣጠረውና ከተያዝንም ልንድን የምንችለው ነው፡፡ ለዚህም በቂ ግንዛቤ፣ እንዲሁም የሚያስፈልጉ ምርመራዎችንና ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል፡፡ በዋነኛነት ለኤችአይቪ የሚደረጉ ጥንቃቄዎች በሞላ ለሄፒታይተስ ቫይረሶችም ጠቃሚ ነው፡፡

ዶ/ር አዲስ ታምሬ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ‹‹ኢትዮጵያ ሄፒታይተስን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስፈልጉ ስትራቴጂዎች አዘጋጅታለች፣ በተለይም ሄፒታይተስ ‹‹ሲ›› ያደረባቸውን ሕሙማን አክሞ ለማዳን የሚያስችሉና በአሜሪካ ገበያ ውስጥ 84 ሺሕ ዶላር የሚያወጡ መድኃኒቶችን በአገር ውስጥ በማምረት ለበሽተኞች የሚደርሱበት ሁኔታ አመቻችታለች፤›› ብለዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት ለኤችአይቪ የተከናወኑ ሥራዎች ሄፒታይተስንም ለመከላከል ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ ኤችአይቪ፣ ሄፒታይተስ ቢ እና ሲ የሚተላለፉባቸው መንገዶች ጥንቃቄ በጎደለው የወሲብ ግንኙነት፣ በደም ንክኪ፣ በመርፌና ስለታም ከሆኑ ነገሮች ጋር በተያያዘ ነው፡፡ ስለዚህ አንድ ዓይነት የመተላለፊያ መንገዶች ስላላቸው የመከላከያ መንገዶቹም አንድ ዓይነት ናቸው፡፡

በዚህም የተነሳ ባለፉት ዓመታት መሠራት የሚገባቸው በመከላከሉ ዙሪያ ስለነበረ ከመከላከሉ አንፃር ኢትዮጵያ ከሌሎች አገሮች በተሻለ ተንቀሳቅሳለች ማለት እንደሚቻል ነው የተናገሩት፡፡

ሄፒታይተስ ቢ ክትባት የሕፃናት ክትባት ፓኬጅ ውስጥ እንዲገባ ካደረጉት 47 የአፍሪካ አገሮች መካከል አንዷ ኢትዮጵያ ናት፡፡ የክትባቱ መድኃኒቶች 99 በመቶ ያህሉ ኢትዮጵያ ውስጥ ይመረታሉ፡፡ ይህም ሆኖ ግን ለበሽታው ተጋላጭ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሎ ለተለዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ይደርሳሉ ማለት እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡

መድኃኒቱንና ሕክምናውን በተለይ ደሀ ተኮር በሆነ መልኩ ማቅረብ የሚቻልበትን ሁኔታ ጉዳዩ በይበልጥ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ምክክር በማድረግ ላይ መሆኑን ዶ/ር አዲስ ጠቁመው፣ ደሀው የትምህርት ደረጃውና መረጃ የማግኘት ዕድሉ ዝቅተኛ ስለሆነ በተጠቀሰው በሽታ የመጋለጥ ዕድሉ ከፍተኛ እንደሚሆን አስረድተዋል፡፡

በብሔራዊ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ሕክምና ማዕከል በተከናወነው በዚሁ የአከባበር ፕሮግራም ላይ የዓለም ጤና ድርጅት ተወካዮች፣ የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሜዲካል ኮሌጅ መምህራንና ተማሪዎች ተገኝተዋል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here