በአብዛኛው የአለማችን ክፍል ልጅ ሳይወልዱ በፊት የሚጋቡ ጥንዶች ቁጥር ከመቼውም ጊዜ በላይ እየቀነሰ መጥቷል።በሀብታሞቹ ሀገራት ከአምስቱ ሁለቱ፣በላቲን አሜሪካ ደግሞ ከሶስቱ ሁለቱ ልጆች ከጋብቻ ውጭ የሚወለዱ ናቸው።የየሀገራቱ ሕጎች በጋብቻ ውስጥ ያልተወለዱ ህፃናትን የሚያስተናግዱበት መንገድም የተለያየ ነው።

በአንዳንድ ኢስላማዊ ሀገራት እናቶቻቸው በዝሙት ወንጀል በሞት ሲቀጡ ከጋብቻ ውጭ የተወለዱ ልጆች ወላጅ አልባ ይሆናሉ። ዘ ኢኮኖሚስት ነው ይህን ጽሁፍ ጥር 7 2008 ያወጣው።የእኛን ሕግም እያነሳሳን እንቀጥል።

 

በቻይና ደግሞ ከጋብቻ ውጭ የሚወለዱ ህፃናት (ሕዝባዊ አገልግሎቶችንም ሆነ መታወቂያ ወረቀት እንኳን ሳይቀር)የሚጠበቅላቸው በጣም ጥቂት መብቶቸ ብቻ በመሆናቸው ከሞላ ጎደል ሁሉንም የውርጃ ሰለባ ያደርጋቸዋል።

በቀጥታ ያልተጋቡ ወላጆችን ልጆች ማግለል በተው ሀገራት እንኳን ሳይቀር የተጋቡና ሳይጋቡ አብረው በሚኖሩ ወላጆች መሀል ልዩነት የሚያደርጉ ሕጎች ህፃናቱን እየጎዱ ይገኛሉ።
በአንዳንድ ስፍራዎች እንደ ኢንግላንድ እና አሜሪካ ጥንዶች ሁለት አማራጮች ይቀርቡላቸዋል። መጋባት ወይም በሕግ ምንም ግንኙነት እንደሌላቸው መቆጠር።
እንደ ፈረንሳይ እና ኔዘርላንድስ ያሉት ሌሎች ሀገራት ደግሞ ለጥንዶች ‘ቀላል ጋብቻ’ ከሚባለው የተወሰኑ የጋብቻ ባህሪያትን እንደ የግብር እፎይታ፣ወይም ከፍቺ በኃላ ንብረት መጋራት ያሉትን ከሚያካትት ከጋብቻ ጋር ተቀራራቢ አማራጭን ከጋብቻ በተጨማሪ አቅርበዋል።

በሶስተኛው ጎራ የሚገኙት እንደ አውስትራሊያ እና ኒው ዘላንድ ያሉ ሀገራት ደግሞ የተወሰነ አመታትን አብረው ለቆዩ ያልተጋቡ ጥንዶች በሕጉ የተቀመጠው የአብሮ መኖር ጊዜ እንደሞላ ወዲያውኑ አብዘኛዎቹን የጋብቻ ግዴታና መብቶች እንዲኖራቸው ያደርጋሉ።
የመጀመሪያውን አማራጭ በተመለከተ ጥቅሙ ቀላልነቱ ነው።ወይ ሕጋዊ ጋብቻ ፈፅሙ አልያ የባልና የሚስትነት ግዴታም ሆነ መብት የላችሁም የሚል ነው።ችግሩ ታድያ ብዙ ጥንዶች ይህንም እያወቁ ጋብቻ አለመፈፀማቸው ነው።

በመሆኑም አንዳንዶች መለያየቱ ሲመጣ ወይም አንደኛው አጋር ሲሞት ባዶአቸውን ተንሳፈው ይቀራሉ።ያለጋብቻ አብረው ከሚኖሩት ጥንዶች አንዳኛቸው ሳይናዘዙ ከሞቱ ለምሳሌ በኢንግላንድ ውስጥ ሌላኛው ምንም ነገር ላይወርስ ይችላል።ተጋቢዎች እንደሚሰጣጡት ስጦታ ሳይሆን የተሰጠው የኑዛዜ ስጦታም ቢኖር የውርስ ቀረጥ ይጣልበታል። የቤተሰቡ ቤት የባለቤትነት ምስክር ወረቀት ላይ ያለው የአንዱ ተጋቢ ስም ብቻ ከሆነም ሌላኛው ተገፍትሮ ባዶውን ሊወጣ ይችላል።

እነኚህ ችግሮች ታዲያ ሁለተኛው አማራጭ ለጥንዶቹ ግንኙነት ሰፋ ያሉ የሕጋዊ ውሎችን በማቅረቡ ያለውን ጠቀሜታ ይጠቁማሉ።

በፈረንሳይ ‘‘ፓክቴ ሲቪል ደ ሶሊዳሪቴ’’ በጣም ተመራጭ ጋብቻ ያልሆነ ግንኙነት ነው። ይህ ግንኙነት በብዙ መልኩ ከጋብቻ ጋር ቢመሳሰልም ለማፍረስ ቀላል ነው።አንደኛው ተጣማጅ የተመዘገበ የበቃኝ ደብዳቤ በመስጠት ወይም ከሌላ ሰው ጋር በመጋባት የአብሮነቱን ህልውና እንዲያከትም ማድረግ ይቸላላል።በተመሳሳይ ግማሽ ያህሉ ያልተጋቡ የደች ጥንዶች ግንኙነታቸውን ‘‘በአብሮነት ስምምነት’’(cohabition agreement)በመፈራረም የሚያጠብቁት ሲሆን ስምምነቱ በሚለያዩበት ጊዜ ሀብትና ወጪያቸውን እንዴት እንደሚከፋፈሉ በዝርዝር የሚያስቀምጥ ነው።

ሆኖም ግን እነኚህ ጋብቻን መሰል ብዙ አማራጮች ባሉባቸው ሀገራት ውስጥ እንኳን ብዙ ጥንዶች አንዱን ሲመርጡ አይታይም።በመሆኑም አንደኛቸው ከሞቱ ወይም እህል ውሀችን አበቃ ብለው ከተለያዩ በሕግ እንደ ባዳ ነው ሚታዩት ልክ እንደ እንግሊዛውያን ያልተጋቡ ጥንዶች።

በመሆኑም አንዳንድ ሀገራት ሶስተኛውን አማራጭ አክለዋል።ጥንዶቹ በግልፅ እንደማይፈልጉ ካልተስማሙበት በስተቀር የተወሰኑ አመታትን አብረው ከኖሩ ከሞላ ጎደል ሕጉ እንደተጋቡ ሰዎች ይቆጥራቸዋል። ለረጅም ጊዜ የቆየው ያለጋብቻ አብሮ መኖር ሲያበቃ በአውስትራሊያ ወይም በኒው ዘላንድ ጥንዶቹ ቀለብ፣የጋራ ንብረት ድርሻ እና ከጋብቻ ጋር ተመሳሳይ የሆነ የኑዛዜ ወራሽነት መብት ይኖራቸዋል።

ካለ ነፃ ፍቃዳቸው ሰዎችን የጋብቻ እንዲፈፅሙ መግፋቱ በጣም አፋኝነት መስሎ ሊሰማ ይችላል።የሚያሳዝነው ግን አብዛኞቹ ጥንዶች ግንኙነታቸውን መደበኛ ባለማረጋቸው ሊያጋጥማቸው የሚችለውን አደጋ ቀድመው በቅጡ አለመረዳታቸው ነው።ለረጅም ጊዜ ሳይጋቡ አብሮ መኖር የጋብቻ መብትና ግዴታ በማይፈጥርባቸውም አገራት ብዙ ሰዎች በስህተት ሳይጋቡ አብሮ ለተወሰነ ጊዜ መቆየቱ የጋብቻን መብትና ግዴታ እንደሚያስከትል ያምናሉ።

የተደረጉ ጥናቶች ሚጠቁሙት ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ብሪታንያውያን የረጅም ጊዜ ሳይጋቡ አበሮ የመኖር ግንኙነት በኮመን ሎው(ያልተፃፈ ሕግን በሚከተሉ እንደ እንግሊዝና አሜሪካ ያሉ የሕግ ስርአቶች) ውስጥ ጋብቻ መሆኑን ያምናሉ ።እንደዚያ አይነት ጋብቻ ግን በነዚህ ሀገራት ሕግ አይታወቅም።አብዛኛዎቹ አሜሪካውያን ደግሞ ለሰባት አመት ሳይጋቡ መኖር ለግንኙነቱ ሕጋዊ እውቅና ያስገኛል ብለው ነው ሚያስቡት እውነታው ግን አለማስገኘቱ ነው።

ህፃናት በሌሉበት ግንኙነት ውስጥ ጥንዶቹ የግንኙነታቸውን ሁኔታ መወሰን መቻል አለመቻላቸው ላይ መንግስት እጁን ማስገባት የለበትም። ህጻናት ካሉ ግን የህፃናትን ጉዳት ለማስወገድ ግን የበለጠ ዘላቂነት ያለውና ጥንዶቹ ሲለያዩ ወደፊት የልጆቻቸውን አስተዳደግና መብትና ግዴታቸውን የሚመለከት የጋብቻ አይነት ውል እንዲገቡ ማድረጉ ምክንያታዊ ነው።በዚህም ህፃናት ያላቸው ጥንዶች ከሁኔታቸው ጋር ተስማሚ የሆኑ የጋብቻ ጋር ተቀራራቢ አማራጮች መሀል እንዲመርጡ ሊፈቀድላቸው ይገባል።

የሚሻላቸውን ካልመረጡና ህፃናት ካሉዋቸው አሁንም የተሰጣቸውን አማራጭ በሌላ መለወጥ አለበት። ይህ አማራጭ ለረጅም ጊዜ ሳይጋቡ አብረው የኖሩ ጥንዶችን ውርስን፣ከተለያዩ በኃላ የሚኖራቸውን መተዳደሪያ እና የንብረት ክፍፍልን በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ጥንዶቹ በግልፅ እንደማይፈልጉት ተስማምተው ካልወሰኑ በስተቀር እንደ ተጋቡ ባልና ሚስት አድርጎ ሚቆጥር ነው።

የኛስ ሕግ ምን ይል ይሆን?
.=============
የተሻሻለው የፌደራሉ የቤተሰብ ሕግ አንቀፅ 98 ላይ ጋብቻ ሳይፈፅሙ እነደ ባልና ሚስት በትዳር መልክ መኖር እውቅና የተሰጠው ግንኙነት ነው።

በዚህ ግንኙነት ወስጥ ያሉ ጥንዶች እንደ ባልና ሚሰት አብረው ኖሩ ለመባል በሕግ እንደ ተጋቡ አይነት ሰዎቸ ሁኔታ ማሳየታቸው አስፈላጊና በቂ ነው።

ሆኖም በታወቀና በተደጋገመ ሁኔታ የሩካቤ ሥጋ ገንኙነት መፈፀማቸው ብቻ እንደ ባልና ሚስተ ሳይጋቡ ይኖራሉ ለማለት በቂ አይደለም።በዚህ ግንኙነት ውስጥ ያሉ ጥንዶች የጋራ ወጪያቸውን እንደየአቅማቸው የሚሸፍኑ ሲሆን ከሶስት አመት ላላነሰ ጊዜ አብረው ከኖሩ በግንኙነቱ ውስጥ ያፈሩት ንብረት የጋራ ሀብት ይሆናል።

በዚህ ግንኙነት ውስጥ የተወለዱ ልጆችን በተመለከተ በቤተሰብ ሕጉ አንቀፅ 130 መሰረት እንደ ባልና ሚስት አብረው ሲኖሩ የተፀነሰ ወይም የተወለደ ልጅ አባት ነው ተብሎ የሚገመተው ከእናትየዋ ጋር እንደ ባል አብሮ የሚኖረው ሰው ነው።

እንደ ባልና ሚሰት ሳይጋቡ አብረው የሚኖሩ ጥንዶች ግንኙነታቸውን በማንኛውም ጊዜ ማቋረጥ የሚችሉ ሲሆን አለመግባባት ከተነሳ ደግሞ ጉዳያቸውን ፍርድ ቤት ማቅረበ ይችላሉ። በተጨማሪ ይህ ግነኙነት መኖሩን ጥንዶቹ ባይጋቡም የተጋቡ ሰዎችን ሁኔታ እንደሚያሳዩና ቤተዘመዶቻቸው እና ማህበረሰቡ እንደ ተጋቡ ሰዎች የሚኖሩ ናቸው ብሎ እንደሚገምታቸው በማስረዳት ማረጋገጥ ይቻላል።

በተሻሻለው የፌደራሉ የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 107 መሰረት ከጋብቻ ስርአት ወይም ጋብቻ ሳይፈፅሙ እንደ ባልና ሚስት አብሮ ከመኖር ውጭ በአንድ ወንድና በአንዲት ሴት መካከል የሚደረጉ ሌሎች ግንኙነቶች በሕግ ፊት ምንም ውጤት አያስከትሉም።

ዘ ኢኮኖሚስት ካቀረባቸው የአለማቸን ሶስት ዋና ዋና ሳይጋቡ አብሮ የመኖር የሕግ አማራጮች አንዲሁም ከኛው ሕግ ምረጡ ብትባሉ የትኛውን ትመርጣላችሁ?

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.