የምትፈልጋትን ዓይነት የፍቅር አጋር እንዴት ማግኘት ትችላለህ? (ለወንዶች ብቻ)

1

ዕድሜዬ 28 ነው፡፡ በአንድ መንግሥታዊ ባልሆነ ግብረ ሰናይ ድርጅት ውስጥ ተቀጥሬ እሰራለሁ፡፡ ራሴን በሚገባ የማስተዳድር ሰው ነኝ፡፡ ቤተሰቤ ያን ያህል የእኔን እርዳታ ባይፈልጉም አልፎ አልፎ ግን አንዳንድ ነገር አደርግላቸዋለሁ፡፡ ትዳር በዓመትና በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ የመመስረት ፍላጎት አለኝ፡፡ የምፈልጋትን አይነት የፍቅር አጋር ግን እስካሁን ድረስ አላገኘሁም፡፡

ከሁለት ሴቶች ጋር ከዚህ በፊት መቀራረብ የቻልኩ ቢሆንም አንዳቸውም ከወራት የዘለለ ዕድሜ ኖሯቸው ወደ ትዳር ማምራት አልቻሉም፡፡ አንዳንድ ጊዜ ‹‹ይኼ ነገር እኮ እንደው ምንም አልሳካ አለ፤ ችግር ይኖርብኝ ይሆን እንዴ?›› ብዬ አስባለሁ፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ ‹‹ለነገሩ ያው ጊዜው ነው እውነተኛ አፍቃሪ እኮ አይገኝም፡፡ ሰው ማንነትን ሳይሆን ምን ምን አለው ብቻ ነው የሚለው፣ ሞልቶ ስላልተረፈኝ ይሆናል›› እላለሁ፡፡ አሁን አሁንማ እንደው አዳዲስ ሰው የመተዋወቅ ዕድሉም የለኝም፡፡ አንዳንዴ ለመተዋወቅ እሞክርና ያን ያህል እኔም ገፍቼ አልሄድም በእነሱ በኩልም የተለየ ፍላጎት አላይም፡፡ ሳልሰማ ወይ ህጉ ተቀይሮ ይሆን እንዴ? ብዬ ለራሴ ፈገግ እላለሁ፡፡ የምፈልጋትን አይነት የህይወት አጋር እንዴት ማግኘት የምችል ይመስላችኋል?›› 

ከምስጋና ጋር በረከት ነኝ፡፡

መልስ፡-

የሰው ልጅ በህይወቱ ዘመን ከሚያደርጋቸው ዋና ዋና ውሳኔዎች መካከል አንዱ የትዳር አጋር ምርጫ ማድረግ ነው፡፡ የትዳር አጋር ለማግኘት ወጥ ቀመር ባይኖርም ጠቃሚ የሆኑ አጠቃላይ መርሆዎች ይኖራሉ፡፡ እነዚህን መርሆዎች ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ጥያቄህን ለመመለስ እሞክራለሁ፡፡

የአንተ ጥያቄ ‹‹የምፈልጋትን አይነት የህይወት አጋር እንዴት ማግኘት እችላለሁ?›› የሚል ስለሆነ ለዚህ ሊረዱህ የሚችሉ ሀሳቦችን ከዚህ በታች እገልፃለሁ፡፡

ለትዳር መድረስን ማረጋገጥ፡- የአንተ ዕድሜ 28 በመሆኑ ከዕድሜ አንፃር ከመድረስም አልፈሃል ማለት ይቻላል፡፡ ከዝቅተኛው የጋብቻ ዕድሜ አስር ዓመት ያህል ርቀሃል፡፡ መልካም የጋብቻ ወቅት የሚባለው 20ዎቹ አጋማሽ አካባቢ እንደሆነ ይታሰባል፡፡ ከዚህ አንፃር የአንተ ዕድሜ ለጋብቻ ከበቂ በላይ ነው፡፡ የኢኮኖሚ ነገር ሲታሰብ መንግሥታዊ ባልሆነ ድርጅት ውስጥ ትሰራለህ፤ ራስህን በሚገባ የምታስተዳድር ሰው ነህ፤ ወላጆችህም ቢሆኑ የአንተን እርዳታ የሚፈልጉ አይነት ሰዎች አይመስሉም፡፡ ስለዚህ በኢኮኖሚ በኩል ያለውንም ፈተና አልፈሃል፡፡ ከውስጣዊ ዝግጅት አንፃር ደግሞ ለማግባት ፍላጎት አለብ፡፡ አንዳንድ እርምጃዎችንም እየወሰድክ ትገኛለህ፡፡ ለጋብቻ መድረስህ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ አሁን ወደ ትዳር አጋር ፍለጋ እንሂድ!

መስፈርትን መቃኘት፡- ዋነኛው የአንተ ችግር እንደሆነ የተገለፀው የምትፈልጋትን አይነት የትዳር አጋር ማግኘቱ ላይ እንደሆነ ‹‹የምፈልጋትን አይነት የፍቅር አጋር ግን እስካሁን ድረስ አላገኘሁም›› የሚለው ሐሳብ ያሳያል፡፡ ለትዳር ዕጩ ከሚሆኑ ሴቶች መካከል አንዷን ለመምረጥ መስፈርት ያስፈልግሃል፡፡ በቅድሚያ አንተ የምትፈልጋትን የትዳር አጋር ምን አይነት ሴት እንደሆነች በትክክል እወቅ፡፡ መቼም የሆነ መስፈርት እንዳለህ አስባለሁ፡፡ ማንም ሰው የሚፈልገውን ሳያውቅ መምረጥ አይችልም፡፡ ምርጫ ካለ መስፈርት አለ ማለት ነው፡፡

የትዳር አጋር ተፈልጋ የማትገኘው በምርጫ መስፈርት ዝርዝር ብዛትና ደረጃ ችግር ሊሆን ይችላል፡፡ መስፈርቶችን ለትዳር አጋር ምርጫ ከመጠቀምህ በፊት በአንተ ለካቸው፤ አንተ መስፈርቶቹን ማለፍ ከቻልክ ጥሩ መስፈርት ነው ማለት ነው፡፡ ሌላም ሴት ማለፍ ትችላለች፡፡ አንተ በሁሉ ነገር ፍፁም እንዳልሆንክ፤ ፍፁም ሴትም የለችም፡፡

የትዳር ጓደኛ ምርጫ መስፈርቶችን በተመለከተ ጥቂት ጠቃሚ ሃሳቦችን ላንሳልህ፡፡ መልካም የትዳር አጋር ለማግኘት ከዚህ በታች የተጠቀሱ ነጥቦች ወሳኝ ናቸው፡፡

የዕድሜ መጣጣም፡- የሰው ውበት፣ ስሜት፣ አስተሳሰብ፣ እውቀትና ፍሬያማነት እንደ ዕድሜው የተለያየ ነው፡፡ በዕድሜ ከአንተ ጋር የምትጣጣም፣ አቻ የምትሆንህ ሴት ብታገኝ ይመረጣል፡፡ የአንተ ‹‹እናት›› ወይም ‹‹ልጅ›› የማትመስል እኩያህ የሆነች ሴት እርሷ ጥሩ የፍቅር ጓደኛ ትሆንሃለች፡፡ ሀብት፣ ንብረትና ሌሎች ጥቅሞችን ከእርሷ ወይም በእርሷ በኩል ለማግኘት ብለህ በዕድሜ የማትመጥንህን ሴት አትሞክር፡፡ በውጫዊ ውበት ተማርከህ ደግሞ በዕድሜ ከአንተ በጣም የምታንስ ሴትን መፈለግም ዞሮ ዞሮ በትዳር ውስጥ የፍቅር መጣጣም ችግርን ያስከትላል፡፡

የባህር/ሰብዕና መጣጣም፡- የፍቅር ጓደኛሞችን የትዳር ግንኙነት አስደሳችና ዘላቂ የሚያደርገው ዋናው የሁለቱ የባህሪይ መጣጣም ነው፡፡

የሰው ባህሪይ/ሰብዕና ከወጣትነት ዕድሜ በኋላ አንፃራዊ ቋሚነት አለው፡፡ ቁጡነት፣ ትዕግስተኝነት፣ አባካኝነት፣ ቆጣቢነት፣ ጠብ ጫሪነት፣ ዳተኛነትት ትጉነት፣ ተጠራጣሪነት፣ ታማኝነት… የሰብዕና መገለጫዎች ናቸው፡፡ ከአንተ ባህሪይ ጋር የሚሄድ ባህሪይ ያላትን ሴት መፈለግ ያስፈልግሃል፡፡ አንተም ሆንክ እርሷ ትክክለኛ ባህሪያችሁን በመጀመሪያ ግንኙነት ላትገልፁ ትችላላችሁ፡፡ ስለዚህ እንደ አስፈላጊነቱ ስፋትና ጥለቀት ያለው ጥናት ሊፈልግ ይችላል፡፡ የአንተም ሆነ የእርሷ ባህሪይ በቤተሰብ አካባቢ በሚገባ ስለሚታወቅ በጥበብ ከቤተሰብና ከጎረቤት ሰዎችና የትምህርትና የሰፈር ጓደኞች መረጃ መሰብሰብ ጠቃሚ ነው፡፡

የትምህርት ደረጃ፡- የሰው የመግባባት መጠኑ እንደ እውቀቱ ይለያያል፡፡ ተመጣጣኝ የትምህርት ደረጃ ያላቸው ጥንዶች እርስ በእርስ ለመግባባት የሚያስችላቸው እውቀት ይኖራቸዋል፡፡ የትምህርት ደረጃ እውቀትን መጨመር ብቻም ሳይሆን በማንነት ላይ ተፅዕኖ ስላለው ተመጣጣኝ ትምህርት ያላቸው ጥንዶች እርስ በርስ የመቀባበላቸው ዕድል የሰፋ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ከአንተ ጋር በትምህርት ደረጃ ተመጣጣኝ የሆነች ወይም የምትቀርብ የትዳር አጋር ብታገኝ ይመረጣል፡፡

ባህል፡- እያንዳንዱ ሰው ያደገበት ባህል ውጤት ነው፡፡ በእያንዳንዱ ባህል ውስጥ መደበኛ ባልሆነ መንገድ የሚሰጥ ትምህርት አለ፡፡ ይህ ትምህርት የአንድን ሰው አስተሳሰብ፣ አመለካከት፣ የህይወት ዘይቤ፣ ቋንቋ፣ ሃይማኖት፣ አመለካከት፣ የህይወት ዘይቤ፣ ቋንቋ፣ ሃይማኖት፣ ሰብአዊ ግንኙነት፣ ይቀርፃል፡፡ አንተና የትዳር አጋር የምትሆንህ ሴት ያደረጋችሁት በተለያየ ባህል ውስጥ ከሆነ፣ ሁለታችሁም ከዚህ በላይ በተጠቀሱ ነገሮች ልትለያዩ ትችላላችሁ፡፡ ይህ ልዩነት ደግሞ በእናንተ ግንኙነት ላይ አሉታዊ ተፅኖ ያሳድራል፡፡ ስለዚህ በምርጫህ ሂደት ከባህል አንፃር ከአንተ ጋር የምትጣጣም ሴት ልጅ መምረጥ ሊመጣ የሚችለውን አሉታዊ ተፅዕኖ ለመቀነስ ይረዳሃል፡፡

የቤተሰብ ፈቃደኝነት፡- አንድ ጎልማሳ በህይወቱ ምርጫ ለማድረግ ሙሉ ሰው ነው፡፡ አንድ ሰው መልካምም ሆነ ክፉ ምርጫ በማድረግ በሚያጋጥመው ሁኔታ ቤተሰብ መሳተፉ አይቀርም፡፡ አንድ ሰው ከቤተሰቡ ጋር ያለው ግንኙነት በደም የተሳሰረ ስለሆነ ግንኙነቱ ጠንካራና ዘላቂነት አለው፡፡ በተለይ ማህበራዊ ትስስሩ ኃይለኛ በሆነበት እንደ ሀገራችን ባለ ማህበረሰብ ውስጥ ውሳኔዎችን ቤተሰብን አማክሮ ማድረግ ብልህነት ነው፡፡

በትዳር ጓደኛ ምርጫህ ቤተሰብህ ተገቢውን ምክርና ድጋፍ በመስጠት ከተሳተፉ በትዳር ጉዞህ ከአንተ ጋር ይሆናሉ፡፡ የእርሷ ቤተሰብ አንተን ከተቀበሉ እውነተኛ የቤተሰብ ቅልቅል ይፈጠራል፡፡ በሁለታችሁ አማካኝነት የሁለታችሁ ቤተሰብ ዘላቂ ወዳጅነትና ዝምድና ፈጠሩ ማለት ነው፡፡ የሁለታችሁ ወይም የአንዳችሁ ቤተሰብ ስምምነታችሁን አለመቀበል መጋባታችሁን ባይከለክልም በትዳር ጉዟችሁ ላይ መፍትሄ የሚፈልግ የቤት ሥራ ይሆንባችኋል፡፡

ፍቅር፡- የትዳር ግንኙነት ማሰሪያ ገመድ ፍቅር ነው፡፡ ትዳር በፍቅር ጀምሮ በፍቅር እንዲያልቅ የምታገባትን ሴት ከልብህ እንደምትወዳት እወቅ፡፡ ለትዳር ዕጩ ከሆኑ ሴቶች መካከል ዕድሜ ልክህን ከእርሷ ጋር ለማሳለፍ የተሰጠ ልብና የማያዳግም ውሳኔ ሊኖርህ ይገባል፡፡ ስለዚህ ከጊዜያዊ ስሜት ባለፈ ሁኔታ እርሷን በማንነቷ የሚቀበልና የሚንከባከብ ፍቅር ካለህ በትክክለኛ ጎዳና ላይ ነህ፡፡ ከልብህ የማትወዳት ከሆነ ግን በሁኔታዎች ግፊት እርሷን ማግባት የለብህም፡፡ ይህ በገዛ ፈቃድህ በራስህ ላይ መሸከም የማትችለውን የህይወት ዘመን ሸክም መጫን ነው፡፡

እንግዲህ መስፈርት ካለህ ከእነዚህ ሐሳቦች አንፃር እንደገና ቃኛቸው፡፡ ቅኝታቸውን ካስተካከልህ በኋላ ተጠቀም፤ እንደ አስፈላጊነቱም አንዳንዶቹን ማሻሻል ወይም መለወጥ ትችላለህ፡፡

ያልተሳኩ ሙከራዎችን መገምገም፡- የትዳር አጋር መፈለግ ሂደት ነው፡፡ በእያንዳንዱ እርምጃ እየተማርክበት የምትሄድ እንጂ በአንድ ጊዜ የሚሳካ ነገር ላይሆን ይችላል፡፡ ዋናው ነገር ከሂደቱ አለመሳካት መልካም ነገር ተምረህ ወደፊት የተሻላ ነገር ለማድረግ መሞከር ነው፡፡

አለመሳካትን ለትምህርት ከተጠቀምክበት የተሻለ ምርጫ ለማድረግ ዕድል ይኖርሃል፡፡ ነገር ግን አንተ የጀመርከው ነገር ለፍሬ አለመብቃቱ አንተ ስለራስህ እንድትጠራጠር ምክንያት ከሆነ ጉዳቱ የከፋ ይሆናል፡፡

የትዳር አጋር ምርጫ አለመሳካቱ ብቻ ሳይሆን በማንነትህና ስለሌሎች ባለህ እይታህ ላይ አሉታዊ ውጤት ያሳድራል፡፡ ከሁለት ጊዜ ሙከራ በኋላ በአንተ ህይወት እየሆነ ያለው ይህን ይመስላል፡፡ ማንነትህን መጠራጠር፣ ሴቶችን መኮነንና በሁኔታዎች ማሳበብ ቀስ በቀስ ራስህንም እንዳትቀበልና ከሰዎችም ጋር ተገቢውን ግንኙነት እንዳታደርግ ምክንያት እየሆነ ነው፡፡

ስለዚህ እስካሁን ድረስ የወሰድካቸው እርምጃዎች አንተ ወደምትፈልገው ውጤት ያላደረሱህ ለምን እንደሆነ ሚዛናዊ በሆነ ሁኔታ ገምግም፡፡ ማሻሻል የምትችላቸውን ነገሮች አስተካክልና ወደፊት ቀጥል፡፡

ትጋትን መጨመር፡- ከደብዳቤህ መንፈስ ትንሽ የትጋት ማነስ ያለብህ እንዲሁም ነገሮችን ቀለል አድርገህ የምትመለከት አይነት ሰው ትመስላለህ፡፡ የምትፈልጋትን አይነት የፍቅር ጓደኛ በእጅህ ለማስገባት ትጋት ያስፈልግሃል፡፡ የሴቶቹን ፍላጎትና የልብ መከፈት እያስተዋልክ የግንኙነት ጥልቀትህን ቀስ በቀስ እየጨመርክ መሄድ ይገባሃል፡፡ የተዋወካትን ሴት ልጅ በመልካም ሁኔታ በመያዝ ትውውቁን ወደ ግንኙነት ማሳደግ፣ ለአንተ ፍላጎት እንዲኖራት ራስህን በተገቢው መንገድ ማስተዋወቅ፣ እርሷንም ለማወቅ ጥረት ማድረግ፣ ቀጠሮ ወስዶ መገናኘት፣ ግንኙነቱን ማሳደግ፣ አለመግባባቶቹን በሰከነ መንገድ መፍታት፣… እያልክ ሂደቱን እስከ ግብ ድረስ መቀጠል አለብህ፡፡

መልካም የትዳር አጋር የምታገኘው በትጋት ከሰራህ ነው፡፡ በትጋት የሚሻና የሚፈልግ ሰው መልካም ሚስት ያገኛለ፡፡ ሴቶችም ከልቡ የሚፈልጋቸውን ሰው ማየት ይፈልጋሉ፡፡ ደጅ ማስጠናቱን ሁሉ ችሎ የሚከታተላቸውና ለእውነተኛ ፍቅርና ጓደኝነት የሚፈልጋቸው ሰው ያገኛቸዋል፡፡ በማያቋርጥ ትጋትና መሻት ውስጥ እውነተኛ ፍቅር መኖሩን የሚያመክት ፍንጭ እንዳለ ይታሰባል፡፡ ስለዚህ በሴቶቹ ፍላጎት አለማሳየታቸው ተከፍተህ አትሽሽ፡፡ ‹‹እምቢ›› ወይም ‹‹ችላ›› ማለታቸው የአንተን እውነተኛ ፍቅርና ፍላጎት ለመለካትም የሚጠቀሙበት መንገድ ሊሆን ይችላል፡፡ በእርግጥ የአንተ ኢላማም ከአቅም በላይ ከሆነ ተገቢ ባልሆነ ስፍራ ጊዜን ማጥፋት ይሆናል፡፡ ኢላማህን በልክህ አድርግ፣ እስክትመታም ትጋ፣ ተስፋ አትቁረጥ!

የግንኙነት አድማስን ማስፋት፡- እንደ ፈላጊ የምትፈልገውን ለማግኘት ያ የሚፈለገው ነገር ያለበት ቦታ መሄድ ያስፈልግሃል፡፡ ዓሳ ለማጥመድ ዓሳ የሚገኝበት ወንዝ ወይም ባህር መሄድ አለብህ፡፡ ዓሳ ወደ ቤት አይመጣልህም፡፡ ‹‹አሁን አሁን አዳዲስ ሰው የመተዋወቅ እድሉም የለኝም›› የሚለው ሐሳብ ለአንተ የትዳር አጋር ፍለጋ ጉዞ ትልቅ እንቅፋት ሊሆን ይችላል፡፡

ለመሆኑ ከአዳዲስ ሰዎች ጋር የመተዋወቅ ዕድል እንዳይኖርህ ያደረገው ነገር ምንድነው? አንተ የምትፈልጋት ሴት እቤት አትመጣልህም፡፡ እርሷ ልትገኝ የምትችልባቸው ስፍራዎች በመሄድ ትውውቅና ግንኙነት መመመስረት ይገባሃል፡፡ እነዚህ የትዳር ጓደኛ የምታገኝባቸው ስፍራዎች የተለያዩ ናቸው፡፡ ለምሳሌ የስራ ቦታ፣ ጎረቤት፣ የስብሰባ ቦታዎች፣ ገበያ ስፍራ፣ ተከራይተህ የምትኖርበት ግቢ ውስጥ፣ ትምህርት ቤት፣ አምልኮ ስፍራ፣ ታክሲ መጠበቂያ አካባቢ፣ ታክሲ ውስጥ፣ መዝናኛ ስፍራዎች፣ ምግብ የምትመገብበት ሆቴል፣ ወዘተ ናቸው፡፡

በተገቢ ጊዜ መሰሎችህ ያሉበት ስፍራ በመሄድ የፍቅር ጓደኛህን መፈለግ ጀምር/ቀጥል እንጂ ‹‹ከአዳዲስ ሰዎች ጋር የመተዋወቅ ዕድል የለኝም›› ብለህ ጊዜህን በከንቱ አታሳልፍ፡፡ ልብህ ከፈቀደ ከሰዎች ጋር የመተዋወቅ መንገድ አይጠፋም ብዬ አስባለሁ፡፡

በመጨረሻም መልካም የትዳር አጋር የሚያገኝ ሰው ቀድሞ ራሱን ያወቀ ሰው ነው፡፡ እውነተኛ አፍቃሪ ለማግኘት አንተ በቅድሚያ እውነተኛ አፍቃሪ መሆን አለብህ፡፡ ሴት ልጅ እውነተኛ ፍቅርን ከአንተ ካገኘች በተለይ በወጣትነት ጊዜ ‹‹ምንም›› አትፈልግም፡፡ እውነተኛ ፍቅር ከሀብትና ከሌሎች ጥቅሞች ይልቅ ሴት ልጅን ወደ ግንኙነት የመሳብ ኃይል አለው፡፡ ስለዚህ ከልብህ አፍቅር፤ የልብ አፍቃሪ ታገኛለህ!

1 COMMENT

  1. This time things are getting complicated.No woman believes man and no man believes any woman.I am also waiting to have my true women but i don’t know why i can get one.When i told them my real life they don’t believe me.you can suggest me if you are willing.Thanks a lot for your cooperation!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.