በሊሊ ሞገስ

ወንዶች ትዳር ከመሰረቱ በኋላ ከዚያ በፊት ያደርጓቸው የነበሩትን ማህበራዊ መስተጋብር ወይም ተጨማሪ ገቢን ለማግኘት ሲያከናውኗቸው የነበሩ ተግባሮችን በጠቅላላ ያቆማሉ፡፡ ይህ አካሄድ በሴቶችም ላይ ጎልቶ ይስተዋላል፡፡ ባለቤታቸው ጠቀም ያለ አስቤዛ የሚሰጥ ከሆነም ስራቸውን አቁመው ተጧሪ የሚሆኑ ሴቶችም ከብዙ በጥቂቱ አይጠፉም፡፡ እናም እንደ ቀድሟቸው ከጓደኞቻቸውም ሆነ ከቤተሰቦቻቸው ጋር መገናኘትና ራሳቸውን መንከባከብን ያቆማሉ፡፡ ይህ ብዙ ሴቶች ካገቡ በኋላ የሚፈፅሙት ስህተት እንደሆነ ይገመታል፡፡

‹‹ትዳር ሙሉ ሰው ያደርጋል›› ከሚለው በተቃራኒ፣ ብዙዎቹ በትዳቸው ግማሽ ሰው ሆነው ደስታ እንዲያጡም ይህ አካሄድ የራሱ የሆነ አሉታዊ አስተዋፅኦ ያደርጋል፡፡
አንዲት ሴት በትዳር ህይወቷ ስላጋጠማት ችግር ያወጋችኝን ላካፍላችሁ ወደድኩ፡፡

‹‹…ከባለቤቴ ቢኒያም ጋር ስንጋባ ውጭ ውጭ የምትል ሴት ለትዳር አትረባም በሚል፣ ባለቤቴን በሚገባ ለመንከባከብ እንዲመቸኝ ስራዬን አቆምኩ፡፡ ጓደኞቼንም ተውኳቸው፡፡ ትዳር ከመያዜ በፊት ለረጅም ጊዜ በሳምንት አንድ ቀን ከጓደኞቼ ጋር ተራራ የመውጣት ፕሮግራም ነበረኝ፡፡ ይህ ተግባር ፍፁም ደስታን ይስጠኝ ነበር፡፡ ከመደበኛ ስራዬም ውጪ ባለኝ ትርፍ ጊዜ ስፖርት አዘውትሮ ነበር፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በተለያዩ የበጎ አድራጎት እንቅስቃሴዎች ላይ መሰተፌ ውስጣዊ እርካታን ስለሚፈጥርልኝ፣ በህይወቴ በጣም ደስተኛና ምቹ ባህሪ ያለን ሰው ነበርኩ፡፡ ሆኖም ትዳር ከመሰረትኩ በኋላ እነዚህን እንቅስቃሴዎች በሙሉ እርግፍ አድርጌ በማቆም ሙሉ ጊዜዬንና ትኩረቴን ለባለቤቴ መስጠት ጀመርኩ፡፡

ከጓደኞቼ ጋር ከማሳልፈው ጊጊ ይልቅ ከባለቤቱ ጋር እራት በልቼ የፍቅር ፊልም ለማየትና በቤት ውስጥ እየተዝናኑ ለማሳለፍ ወሰንኩ፡፡ ባለቤቴም ምርጫዬን አልተቃወመም፡፡ እንዲያውም በመጀመሪያ ለትዳራችን ስምረት ስል ከጓደኞቼ ጋር መገናኘት ማቆሜን ስነግረው፣ አብረን ብዙ ጊዜ ለማሳለፍ መምረጤና ለትዳሬ ዋጋ በመክፈሌ ተደስቶ እጅግ አመስግኖኝ ነበር፡፡ ከጥቂት ወራት በኋላ ግን ባለቤቴ ለእኔ ያለው ፍቅር ባይቀንስም አዳዲስ ባህሪያትን ማንፀባረቅ ጀመረ፡፡ ከእራት በኋላ ከእኔ ጋር ሆኖ ፊልም ከማየት ለብቻው ሆኖ መጽሐፍ ማንበብ መረጠ፡፡

ይባስ ብሎ በሳምንት አንዴ ከጓደኞቹ ጋር እየተጨዋወተ ለማምሸት ፕሮግራም አደረገ፡፡ ይህ የባለቤቴ ተግባር በጣም አናደደኝ፡፡ ስሜቴን የማረግብበት ምንም መፍትሄ ስላጣሁ እቤት ቁጭ ብዬ በመብሰልሰሌ በጣም ተጎዳሁ፡፡ ባለቤቴም ከጓደኞቹ ጋር ተዝናንቶ ሲመጣ ሰላም ልሰጠው አልቻልኩም፡፡ በዚህም ምክንያት በቤታችን ሰላም ከጠፋ ሰነባብቷል፡፡

አሁን አሁን ሳስበው፣ የመጀመሪያ ውሳኔዬ እጅግ የተሳሳተ መሆኑ ይሰማኛል፡፡ በመሆኑም ማንኛውም ሰው ለትዳሩ የሚገባውን ትኩረት እና እንክብካ መስጠቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ትዳሩን አደጋ በማይከት መልኩ ራሱን ማዝናናትም ሆነ ማህበራዊ ግንኙነቶቹን ማስፋት ከዚህም በተጨማሪ ምርጫው በሆኑ መዝናኛዎች ላይ መሳተፍ አለበት ብዬ አምናለሁ›› በማለት ተሞክሮዋን አካፍላናለች፡፡

እርግጥ ነው ከትዳር በኋላ ቀደምት እንቅስቃሴዎቻቸውን የሚተዉ ወንዶች ባይጠፉም፣ በአብዛኛው በዚህ መንገድ ሲጓዙ የሚታዩት ሴቶች መሆናቸው የዛሬው ጽሑፌም ሴቶች ላይ ያተኩራል፡፡ በዚህም መሰረት እንደ ሄለን ያሉ ሴቶች ከትዳር በኋላ የግል ምርጫዎቻቸውን እርግፍ አድርገው በመተው ቤት ቤት ማለት ሲያበዙ ከሚገጥሟቸው ተግዳሮቶች በመነሳት ከነገሩን መካከል የተወሰኑትን ጠቅለል ባለ መልኩ አቅርቤዋለሁ፡፡
የግል ፍላጎት (እንቅስቃሴን) መተው ያለው ትዳራዊ አንድምታ!

– እንደ ሃና ባለቤት ብዙዎቹ በትዳር መባቻ ሚስቶቻቸው ጓደኞቻቸውንና ሌሎች በግላቸው የሚያከናውኗቸውን እንቅስቃሴዎች ትተው ከእነሱ ጋር ብቻ ጊዜያቸውን ሲያጠፉ ደስ ይላቸዋል፡፡ እንዲያውም አንዳንዴ ሚስቶቻቸው ከጓደኞቻቸው ጋር ያላቸውን ግንኙነት ማቆም እንዳለባቸው ያስጠነቅቋቸዋል፡፡ ትንሽ ቆይተው ግን ባሎች ራሳቸው አዲስ ነገር ፍለጋ ውጭ ውጭ ማለት ይጀምራሉ፡፡

– ባሎች ሚስቶቻቸው በራሳቸው ስራ ሲጠመዱ ማየት የበለጠ ይመቻቸዋል፡፡ ቤታቸው መምጣት የሚናፍቃቸው ሚስታቸው ከእነሱ የተለየ የግል ህይወት ሲኖራት ነው፡፡ አንዲት ሴት ባሏ ወደ ቤት ሲገባ መጽሐፍ እያነበበች፣ ድርሰት እየፃፈች ወይም የግል ስራዋን እየሰራች ከጠበቀችው፣ ወይም ‹እስካሁን ጥለኸኝ ጠፋህ አይነት…› ወቀሳ ይልቅ አብረዋት ስሚሩ ባልደረቦቿ የምታጫውተው ወይም አዳዲስ ሐሳቦችን የምታካፍለው ከሆነ የተሻለ ነፃነት እንደሚሰማው ብዙዎች መስክረዋል፡፡ ሠራተኛ ሚስት ያለቻቸው ባሎች እነሱ የማያውቁትን ነገር ባለቤታቸው ስታጫውታቸው፣ በመካከላቸው ያለው ጓደኝነትና የውይይት አጀንዳ ስለሚጎሉበት ይበልጥ ይደሰታሉ፡፡

– እስቲ እርስዎ ባለትዳር ከሆኑ ከባለቤትዎ ጋር ያለዎትን የቀን ተቀን ግንኙነት ልብ ብለው ያጢኑ፡፡ ባለቤትዎ ከእርስዎ ጋር መነጋገር የሚፈልገው መቼ ነው? ለረጅም ሰዓት ስልክ ሲያነጋግሩ ወይም ስራ ሲይዙ አልያም አስቸኳይ ቀጠሮ ይዘው ለመውጣት ሲጣደፉ? ከዚህ በተቃራ እርስዎ ባለቤትዎን ለማዋራት ቁጭ ብለው ያለምንም ስራ ሲጠብቁት እሱ በስራ ተጠምዶ የማውራት ፍላጎቱ ሲቀንስ ማስተዋል የተለመደ ነው፡፡

በተመሳሳይ መልኩ በመጀመሪያው ትዳር ዓመት ስህተት እንደፈፀመች የምትናገረው ኑኑ እንዲህ ትላለች፡- ‹‹አብዛኞቹ ወንዶች የሚስቶቻቸው አትኩሮት በእነሱ ላይ ብቻ ሲሆን ደስ ይላቸዋል የሚል የተሳሳተ እምነት ነበረኝ፡፡ በመሆኑም ስራዬን በመልቀቅ ባለቤቱን ለመንከባከብ ወሰንኩ፡፡ ይህ በሆነ በሁለት ዓመቱ ግን ከባለቤቴ ጋር መሰለቻቸት ላይ ደረስን፡፡ ይሄን ስገነዘብም የመንግሥት ሠራተኛ መሆኔን ባቆምም በግሌ ሌላ ስራ ጀመርኩ፡፡ በመሆኑም ከባለቤቴ ውጭ ከጓደኞቼ ጋር አብሬ መዝናኛ ቦታዎች እሄዳለሁ፤ ለአራት ዓመት ያህል በሳምንት ሁለቴ ቴኒስ እጫወት ነበርና ይህም የተስተካከለ አቋም እንዲኖረኝ ከማድረጉም በላይ ንቁ፣ ደስተኛና መንፈሰ ጠንካራም አድርጎኛል፡፡

በቤተክርስቲያን በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ላይ ከመሳተፍ ባሻገር፣ በማታ ፈረቃ የኮሌጅ ትምህርት መከታተል ጀምሬም ነበር፡፡ የማከናውነው ነገር በበዛ ቁጥር ባለቤቴ ለእኔ ያለው ፍቅር እየጨመረ መምጣቱን አስተውያለሁ፡፡ እሁድ፣ እሁድ ቴኒ ለመለማመድ ስሄድ ባለቤቴ እንደሚናፍቀኝ ማወቅ ያስደስተኝ ነበር፡፡ አንዳንዴ እኔ ሳልጤቀው ባለቤቴ ቴኒስ ስለማመድ መጥቶ ያየኛል፡፡ እኔም ብሆን ከቀድ ይበልጥ ለራሴና ለማንነቴ የምሰጠው ግምት ጨምሯል፡፡ ባለቤቴም ለእኔ ያለው አትኩሮት ከበፊቱ መጨመሩን ተገንዝቤያለሁ፡፡ በተደጋጋሚም አድናቆን ገልፆልኛል›› ስትል ትናገራለች፡፡ በመጨረሻም ማንኛዋም ትዳር የያዘች ሴት ከባልና ሚስትት ተጨማሪ ህይወት ሊኖራት ይገባል ባይ ነኝ በማለት ልምዷን አካፍላለች፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ የስነ ልቦና ተመራማሪዎች የሚሉት ነገር አለ፡፡ አንድ ሰው ሌላውን ለመውደድና ለመንከባከብ በቅድሚያ ራሱን መጠበቅ እና ማዳን እንዳለበት ሲሆን፣ አንዲት ሴት ጤናዋን እና ስነ ልቦናዋን ከጠበቀች ባለቤቷን በኢኮኖሚ ከመደገፍ በተጨማሪ ትዳሯ እንዲባረክ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ታበረክታለች፡፡ ከዚህ በተቃራኒ ያለ ስራ የተቀመጡ ሚስቶች ብቻቸውን መሆን ስለሚሰለቻቸው በየሰዓቱ ባለቤታቸው ጋ እየደወሉ መነጫነጭ ወይም ጠብ መፍጠር ይቃጣቸዋል፡፡

– በአጠቃላይ ሴቶች መረዳት ያለባቸው ነገር ወንዶች ራሳቸውን በራሳቸው ለመንከባከብ ብቁ መሆናቸውን ነው፡፡ ወንዶች በተፈጥሯቸው ለራሳቸው ፍላጎት ቅድሚያን ይሰጣሉ፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ሴቶች ለሌላው መኖር እና ለስሜታዊ ቅርርቦሽ አብዝተው ይጨነቃሉ፡፡ የራሳቸውን ፍላጎት ሳያሟሉ ሌሎች ያሟላሉ፡፡ ለዚህ ተግባራቸው ምስጋና ሳያገኙ ወይም ዕውቅና ሳይቸራቸው ምስጋና ሳያገኙ ወይም እውቀት ሳይቸራቸው ሲቀር ስሜታቸው ክፉኛ ይጎል፡፡ ይህ ሲባል ግን ሚቶች በግል ተግባራቸው ተወጥረው ከባለቤታቸው ጋር የሚያሳልፉት ጊዜ ሊኖራቸውአይገባም ማለት አይደለም፡፡ ባለትዳር ሴቶች ከባለቤቶቻቸው ጋር ለመዝናናት፣ ጥሩ የፍቅር ጊዜትን ለማሳለፍ ብሎም በጋራ ጉዳዮ ላይ ለመምከር በቂ ጊዜ ሊኖራቸው ይገባል፡፡

እንደዚሁም ቀደም ሲል ከጓደኞቻቸው ጋር ያደርጉት የነበረውን ለምሳሌ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ኮሌጅ መማርና የግል ስራ መስራት የመሳሰሉትን ካገቡ በኋላም መቀጠል ይገባቸዋል ነው፡፡ ባለቤትዎ በህይወትዎ ትልቅ ቦታ ያለው ሰው ቢሆን፣፣ ህይወትዎን በሙሉ ለባለቤትዎ መስዋዕት በማድረግ ከልክ በላይ መጣበቅ ግን ሸክሙን ሊያከብደው ስለሚችል፣ በውህደት ውስጥ ላለመጥፋት ጥንቃቄ በማድረግ ሚዛናዊ አካሄድ መከተል ተገቢ ነው፡፡

– ባሎች፣ ሚስቶቻቸው ነፃ ሆነው በግላቸው ሲንቀሳቀሱና የሚያከናውኑት ነገር ሲኖራቸው የበለጠ ደስተኛ እንደሚሆኑ ይታመናል፡፡ ሆኖም ባለትዳር ሴቶች ስራ መስራት ያለባቸው ባለቤታቸው ደስተኛ እንዲሆን፣ እንዲናፍቃቸው ወይም በእሱ ላይ የሙጥኝ እንዳይሉ ብቻ አይደለም፡፡ የግል ህይወት ሊኖራቸው የሚገባው ራሳቸውን  ለማስደሰትና የተሻለ ህይወት ለመምራት ብሎም ለተፈጠርንለት አላማ ለመቆም መሆን አለበት፡፡

አንዲት ሴት ከትዳር በፊት ስራ ከነበራት ትዳር ስትይዝ አስገዳጅ ሁኔታዎች ካልተፈጠሩ በቀር ስራ ማቆም የለባትም፡፡ ከትዳር በፊት ጎበዝ ሃይማኖተኛ፣ አስተዳዳሪ፣ ፖለቲከኛና በሌሎችም የሥራ መስኮች ተሳትፎ ያደርጉ የነበሩ ሴቶች ካገቡ በኋላ የቀድሞ ተግባራቸውን ሲያቆሙ እናያለን፡፡ ምናልባትም አንዲት ታዋቂ ፖለቲከኛ የነበረች ሴት ካገባች በኋላ የፀጉሯ ምክትል ጠ/ሚኒስትር ማን እንደሆነ ላታውቅ ትችላለች፡፡ በመሆኑም ለአንዲት ሴት ትዳሯ ራሷን አስራ አዕምሮዋን እንድትገድል የሚያደርጋት ተቋም እንዳልሆነ ልታወቅ ይገባል እላለሁ፡፡

የትኛውንም አይነት እንቅስቃሴ ለብቻ ማከናወን አለመፈለግ

ሌላው የባለትዳር ሴቶች ችግር ደግሞ፣ ትዳር ከያዙ በኋላ ሁሉንም ነገር ከባለቤታቸው ጋር አብረው ማድረግ ያለባቸው ይመስላቸዋል፡፡ ሳያገቡ በፊት በግላቸው ያደረጉት የነበረውን ነገር ትዳር ከመሰረቱ በኋላ ለብቻቸው መስራት የተራራ ያህል ሲከብዳቸወ ይታያል፡፡

ሄለን የተባለች ሴት ትዳር ከያዘች በኋላ እንዲህ አይነት ችግር እንደገጠማት ትናገራለች፡፡ ‹‹ሳላገባ በፊት ማንኛውንም ነገር በግሌ እሰራ ነበር፡፡ መግዛት ያለብኝን ዕቃ፣ የምመርጠውን የዕቃ አይነት፣ የፀጉሬን ሰራርና የልብስ ምርጫዬን ወዘተ… በግሌ እወስን ነበር፡፡ ካገባሁ በኋላ ከተወሰኑ ወራት በኋላ ግን ስለምሰራው ነገር ሁሉ ባለቤቴን ማማከር ጀመር፡፡ በግ ማከናወን የምችለውን ነገር ባለቤቴን ሳላማክር ማድረግ ያስፈራኝ ጀመር፡፡ ቤታችን ቀለም እንዲቀባ ስፈልግ ባለቤቴ አብሮ ጥሩ ቀለም እንዲመርጥ እጠይቀዋለሁ፡፡ ጠረጴዛና ወንበር መግዛት ሲያስፈልግም እንዲሁ ባለቤቴ እንዲመርጥ እፈልጋለሁ፡፡

ሌላው ቀርቶ የፀጉሬ አሰራርና አለባበሴን ባለቤቴ እንዲመርጥ እጠይቀው ጀመር፡፡ ሁልጊዜ ባለቤቴ ስራውን እየተወ አብሮ ሲያማርጠኝ ቆየ፡፡ አንድ ቀን ግን ባለቤቴን የቤት ዕቃዎችን እንዲያገዛኝ ስጠይቀው፣ ብዙ ስራ እንዳለበትና እኔ የመሰለኝን ወይም ከጓደኞቼ ጋር ሄጄ እንድገዛ ሐሳብ ሰጠኝ፡፡ ምርጫዬ እንደሚስማማውም ገለፀልኝ፡፡ ሆኖም ግን ብቻዬን ሄጄ የቤት ዕቃ ለመግዛት አልደፈርኩም፡፡ በቤት ውስጥ ያሉ ዕቃዎችን መለወጥ ቢያስፈልግም ስህተት ከመስራት ያለቁ ወንበሮችና ጠረጴዛዎችን ለስድስት ወር ያህል መጠቀም መረጥኩኝ፡፡

የሄለን አይነት ችግር በብዙ ባለትዳሮች ላይ የሚታይ ነው፡፡ ሄለን ለመስራት የምትፈልገውን ነገር ባሏን ማማከሯ ከአንድ መልካም ሚስት የሚጠበቅ ተግባር ቢሆንም፤ ነገር ግን ባሏ ዕቃ የማጋዛት ፍላጎት እንደሌለው ወይም ሌላ የሚያከናውነው ተግባር እንዳለው ሲገልፅላት ለብቻዋ መንቀሳቀስና ለራሷ ምርጫና ፍላጎት ዋጋ መስጠት ነበረባት፡፡ ይህ አይነቱ አካሄድ በሂደት በራስ የመተማመን መንፈስ ይቀንሳል፡፡

ለባለቤትዎም ሁሌ እርዳታን የሚጠብቅ ሸክም ይሆናሉ፡፡ ጥሩ ትዳር የሚፈጠረው ጥንዶች በግላቸውና በጋራ የሚሰሩትን ማመጣጠን ሲችሉ ነው፡፡ ብዙዎቹ ትዳር የያዙ ሴቶች ግን ያላቸውን ተሰጥኦ መጠቀም ትተው በባለቤታቸው ሐሳብ መመራት ይጀምራሉ፡፡ የግል ህይወታቸውንም አቁመው በጠቅላላ ከባለቤቶታቸው ጋር የተቆራኘ ያደርጋሉ፡፡ ከዕለታት በአንዱ ቀን ባለቤታቸው የግል ህይወቱን መምራት እንደሚፈልግ በተረዱ ጊዜም የመክዳት፣ የመተው፣ የሐዘንና የተበዳይነት ስሜት ይሰማቸዋል፡፡ እርስዎም እንዲህ አይነቱን ስህተት እንዳይፈጽሙ ጥንቃቄ ያድርጉ፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.