ፎሊክ አሲድ በውኃ የሚሟሟ ቪታሚን ቢ 9 የተባለ ንጥረ ነገር ነው፡፡ ፎሊክ አሲድ ሰውነታችን ጤናማ እና አዲስ ህዋስን ለመሥራት ይጠቀምበታል፡፡

asid-folik-ibu-mengandungለምሳሌ ጥፍራችን እንዲያድግ፣ የሰውነታችን ቆዳ አዲስ እንዲሆን፣ ፀጉራችን እንዲያድግ ቪታሚኑ ለሰውነታችን አስፈላጊ ነው፡፡ ፎሊክ አሲድ እና ፎሌት ተመሳሳይ ሲሆኑ ነገር ግን ፎሊክ አሲድ ሰዎች ከፌሌት የሠሩት ለሰውነታችን ጠቃሚ ቪታሚን ነው፡፡

በአጠቃላይ ማንኛውም ሰው አዲስና ጤናማ ህዋስን ለመሥራት፣ የነበረው የሰውነታችን ህዋስ በአዲስ እንዲተካ ፎሊክ አሲድ በበቂ ሁኔታ በሰውነቱ ውስጥ ያስፈልገዋል፡፡ ሴቶች የእርግዝና መቆጣጠሪያ እየወሰዱ እንኳን በበቂ ሁኔታ ፎሊክ አሲድ ያስፈልጋቸዋል ምክንያቱም እርግዝናው ከመታወቁ በፊት ጽንሱ በፎሊክ አሲድ ማነስ የተነሳ ችግር ሊያጋጥመው ስለሚችል፡፡ በተለይም ደግሞ ሴቶች ቅሪት ከመሆናቸው ከአንድ ወር በፊትና ቅሪት በሆኑ በኋላ በሰውነታቸው ውስጥ ፎሊክ አሲድ በበቂ መጠን መኖሩን በባለሞያ ማረጋገጥ አለባቸው፡፡ ይህ ደግሞ ጤነኛ ልጅ እንዲወልዱ ይጠቅማቸዋል፡፡

በእርግዝና ወቅት ከቪታሚኑ ማነስ የተነሳ ከሕፃኑ አንጎለ ሰረሰር የሚነሱ ነርቭዎች ችግር ስለሚያጋጥማቸው የእግር እንቅስቃሴ ለማድረግ ሕፃኑ አይችልም፡፡ አንድም የሕፃኑ ጭንቅላት ሙሉ ለሙሉ ወይም በአጠቃላይ የአለማደግ ችግር ያጋጥመዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ሰውነታችን ተመጣጣኝ ፎሊክ አሲድ ካላገኘ የደም ማነስ ያጋጥመናል፡፡ ቀይ የደም ህዋስን ሰውነታችን ብረት ከሚባለው ንጥረ ነገር፣ ፎሊክ አሲድና ቪታሚን ቢ12 ቢያዘጋጅም፡፡ የፎሊክ አሲድ መጠን ካነሰ ቀይ የደም ህዋስ ማዘጋጀት አይችልም፡፡ ሰውነታችን ቀይ የደም ህዋስን ቶሎ ቶሎ ስለሚሰባብረው ይህንኑም ለመተካት የፎሊክ አሲድ መጠን ተመጣጣኝ መሆን አለበት፡፡ ሰዎች አዲስ ህዋስን ለመሥራት ወይም የነበረውን ለመጠገን ፎሊክ አሲድ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ሆኖም የፎሊክ አሲድ መጠን በሰውነታችን ካነሰ ሰውነታችን አዲሰ ህዋስ መሥራት አይችልም ማለት ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ህዋሱ ትክክለኛ ሥርዓትን ጠብቆ ስለማይሠራም ካንሰር ወይም ትክክለኛ ያልሆነ ህዋስ ሰውነታችን ያሳድጋል፡፡ ስለዚህ የካንሰር ህዋስ በሰውነታችን እንዳይራባ የፎሊክ አሲድ መጠን ትክክለኛ መሆን አለበት፡፡ በአጠቃላይ ፎሊክ አሲድ የተወሰኑ የካንሰር በሽታ ዓይነቶችን ቢከላከልም ሁሉንም የካንሰር በሽታ ይከላከላል ብሎ መደምደም ይከብዳል በማለት የአሜሪካን ካንሰር ሶሳየቲ ያስቀምጣል (http://www.cancer.org)፡፡

ሴቶች አረገዙ ወይም አላረገዙ ከ0.4 እስከ 0.8 ሚሊ ግራም መጠን ፎሊክ አሲድ በየቀኑ ማግኘት አለባቸው፡፡ የሚያጠቡ እናቶች 0.5 ሚሊ ግራም የፎሊክ አሲድ እስከሚያረግዙ ድረስ መውሰድ አለባቸው፡፡ ለሌሎች በሽታ መድኒቶችን የሚወስዱ ሰዎች ተጨማሪ ፎሊክ አሲድ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ለምሳሌ ለሚጥል በሽታ፣ ለሁለተኛው ዓይነት የስኳር ህመም፣ የግትጋቴ፣ የአስም፣ የጉበት በሽታ፣ ሲክል ሴል የሚባለው የደም ማነስ በሽታ መድኃኒት የሚወስዱ ሰዎችና የአልኮል መጠጥ በጣም የሚያዘወትሩ ሰዎች ሐኪማቸውን በማማከር ተጨማሪ የፎሊክ አሲድ መጠን መውሰድ አለባቸው፡፡
የአልኮል መጠጥን ሰውነታቸው የተለማመዱ ሰዎች የአመጋገብ ዘይቤአቸው ወይም ሥርዓታቸው መልካም የአመጋገብ ሥርዓት ካላቸው ሰዎች ያነሰ ስለሆነ በምግብ የሚያገኙት የፎሊክ አሲድ መጠን ስለሚያንስ ተጨማሪ የፎሊክ አሲድ መጠን ያስፈልጋቸዋል፡፡

ፎሊክ አሲድን ከየት ማግኘት ይችላሉ?
መድኃኒቱን በአገራችን ሕጋዊ ከሆኑ ሆስፒታሎች፣ ጤና ጣቢያዎች፣ ፋርማሲዎች፣ መድኃኒት መደብሮች በሐኪም በታዘዘ የመድኃኒት ማዘዣ ማግኘት ይችላሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ቪታሚኑን ልናገኝባቸው የምንችላቸው የምግብ ዓይነቶች የቅጠላ ቅጠል ምግቦች፣ ፍራፍሬዎች፣ ባቄላ፣ እንቁላል፣ ኦቾሎኒ፣ ፓስታ፣ ዳቦ፣ ጥራጥሬ ማግኘት ይቻላል፡፡

የመድኃኒቱ አግባባዊ አጠቃቀምና መወሰድ ያለበት ጥንቃቄ
1.    ሐኪም ባዘዘለዎት መሠረት መውሰድ አለብዎት፡፡ ከሐኪሙ ትዕዛዝ ውጭ መጠኑን መጨመር ብሎም ለረጅም ጊዜ መውሰድ የለበዎትም፡፡
2.    እርስዎ ለዚህ መድኃኒት አለርጅ ከሆኑ መድኃኒቱን መውሰድ የለብዎትም፡፡
3.    የኩላሊት በሽታ ካለበዎት መድኃኒቱን ከመውሰድዎ በፊት ሐኪምዎን ወይም የመድኃኒት ባለሙያን ማማከር ይኖርብዎታል፡፡
4.    በሐኪም ያልተረጋገጠ የደም ማነስ በሽታ ካለብዎት መድኃኒቱን ከመውሰድ ተቀጠቡ፡፡
5.    በዓለም የምግብ፣ የመድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን መሠረት መሠረት ነጠሰ ጡሮች በሐኪም ትዕዛዝ መሠረት ቢወስዱት በፅንሱ ላይ ምንም ዓይነት ችግር እንደማያመጣ ያስቀምጣል፡፡
6.    መድኃኒቱን ቀጥታ የፀሐይ ብርሃንና ሕፃናት የማይደርሱበት ቦታ ማስቀመጥ አለብዎት፡፡
7.    የመድኃኒቱን የመውሰጃ ሰዓት በአጋጣሚ ቢረሱና ቢያስታውሱት ወዲያውኑ በአስታወሱ ጊዜ ከሚቀጥለው የመድኃኒት መውሰጃ ሰዓት ጋር በማቀራረብ መድኃኒቱን መውሰድ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን በዚህ ጊዜ የረሱትን መድኃኒት ተጨማሪ መጠን መድኃኒት መውሰድ የለብዎትም፡፡
8.    በአጋጣሚ ብዙ መጠን ያለው መድኃኒት ቢወስዱና የተለየ ችግር ካጋጠመዎት አቅራቢያያዎ ወዳለ የጤና ተቋም ሔደው ዕርዳታ ይጠይቁ፡፡ የመረጃው ምንጭ ‹‹Med line Plus›› ነው፡፡
(የኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድኃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን)
ከአዘጋጁ፡- ባለሥልጣኑን በኢሜይል አድራሻቸው daca@ethionet.et ማግኘት ይቻላል፡፡

 

ተጻፈ በ  

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.