ዶ/ር ዓብይ ዓይናለም 

ዘመናዊ ሰዎች የሌሎች ሰዎችን ፀጉር ሲያደንቁ ይስተዋላሉ፡፡ ፀጉራቸውን ለመስተካከል/ለመስራት ሲሯሯጡም እናያለን፡፡ በፀጉር አምሮና ተውቦ ለመገኘት ሁሉም እንደየአቅሙ ሲሟሟት ይታያል፡፡ ግን ለምንድነው ሰዎች ፀጉራቸውን የሚንከባከቡት? ለፀጉር የሚጠፋው ገንዘብና ጊዜ ቀላል ነው? ነጋ ጠባ ፀጉር እያደገ፣ እየተስተካከለ፣ እየተበጠረ የሚኖር መሆኑ አያናድድም? ያለማቋረጥ የሚያድግ ፀጉር ባለቤት በመሆን ረገድ፣ የሰው ልጅ ብቸኛ ፍጡር ነው፡፡ እኮ ለምን?

ከአንድ ሁለት ዓመት ወዲህ ፀጉርን በሚመለከት ሳይንሳዊ አመለካከቶች እየተንፀባረቁ ናቸው፡፡ እንደሚባለው ከሰው በስተቀር ሌሎች ፍጡራን አንዴ ፀጉር ከተላበሱ በኋላ ዕድገቱ ይቆማል፡፡ የእኛ ፀጉር ግን ሲሻው ዕድሜ ልክ ሲያድግ፣ ሲመዘዝ ይባጃል፡፡ ለምንድነው የሰው ፀጉር ያለማቋረጥ ለማደግ የቻለው? በእንክብካቤ ብዛት ወይስ በተፈጥሮ? ለዚህ አስተማማኝ ምላሽ ለመስጠት ይከብድ ይሆናል፡፡

በደንብ የሚታወቀው ሁለት አይነት ፀጉር ያለን መሆኑ፡፡ ዋነኛው የጭንቅላት፣ የቅንድብና የሽፋሽፍት፣ ሌላው በሌሎች የሰራ አካላታችን የሚገኙት ናቸው፡፡ እነዚህም እንደየሰዉ ዕድሜ፣ ፆታና ተፈጥሮ ይብዛ ይነስ እንጂ የብሽሽት፣ የብብትና የጢምንም ጨማምሮ ዘጠኝና አስር አይነት ይሆናሉ፡፡ በትከሻ ላይ ዝቅ ብሎ አምሮ የሚታየውም ሆነ በእግር ጣቶች ላይ የምትበቅለዋ ስስ የሆነች ፀጉር፣ ሁሉም እስከሚረግፉ እኩል ይበቅላሉ፡፡ በወር ከአንድ እስከ 1.5 አፅቅ (ሳ.ሜ) የበቀለ ፀጉር አድጎ ሲያበቃ ይረግፋል፡፡ የፀጉር ዕድገት ጊዜም እንደ ፀጉሩ አይነት ይለያያል፣ ርዝመቱም በዚያው ይወሰናል፡፡ ለምሳሌ የእግር ፀጉር ዕድገቱን በሁለት ወራት ያቋርጣል፣ የብብት ፀጉር ለስድስት ወራት፣ የራስ ፀጉር ግን ያለማቋረጥ ዕድገቱ ከስድስት ዓመት በላይ ይዘልቃል፡፡

እጅግም የማይታወቀው የፀጉራችን አስተዳደግ ስልተ ምስጢሩ ሲሆን ወደፊት ግን የሚደረስበት ይሆናል፡፡ ለመሆኑ መቼ ነው የሰው ልጆች የራስ ፀጉር በማያቋርጥ ሁኔታ ማደግ የጀመረው? ተብሎ ሲጠየቅ የዛሬ 240,000 ዓመታት፣ የሰው ልጅ እሳት ማቀጣጠል ከጀመረበት ጊዜ በኋላ ነው ይባላል፡፡ እናም ከብርድ መከላከያ ብልሃት እስካገኘበት ጊዜ ድረስ በፀጉሩ ላይ የአይነትም ሆነ የመጠን/የብዛት ለውጥ ማስከተሉና፣ በለውጡም የማይፈለግ ቦታ የበቀለ ፀጉር ከጊዜ ወደ ጊዜ መርገፉ/መሳሳቱ የዝግመት ለውጥ ሀቅ እንደሆነ ይታሰባል፡፡

የፀጉር መሳሳት በበኩሉ አያሌ ጠቀሜታዎች እንዳሉትም አለመዘንጋት ነው፡፡ ይኸውም ፀጉር ውስጥ ተደብቀውና ተራብተው በሽታ አምጪ የሆኑ ተባዮችን መቀነሱ፣ ከአስቸጋሪው የጫካ ኑሮ ወደ ሜዳማ፣ ሙቀታማና ወደ ባህር አካባቢዎች ሲጠጋ ከፀሐይ ከሚከላከልበት የራስ ፀጉር በስተቀር፣ ራሱን ለማቀዝቀዝ የፀጉሩ ከቀድሞው መቀነስ ላብ በብዛት ለማመንጨት ረድቶታል፡፡ በዚያ ላይ ሰው ልጅ ፀጉሩ እያነሰ በሄደና፣ ለስላሳ ቆዳ በኖረው ቁጥር ይበልጥ ለፍቅር እየተፈላለገ፣ ባለ አናሳ ፀጉሮቹ እየተራቡ፣ ፀጉራሞቹ በብዛት እየቀነሱ እንደሄዱ ይገመታል፡፡ በተባይ አምጪነቱም ይሁን በሌላ ምክንያት የማይፈለግ የነበረው ፀጉር፣ አሁን ደግሞ በአንፃሩ ምን እየተደረገ ነው?

በአሁኑ ጊዜ፣ ፀጉራችንን እጅግ ሲበዛ እንንከባከበዋለን፡፡ ፀጉር የማንነት መገለጫ ሆኗል፡፡ በወጉ የተሰራ ፀጉር አደባባይ ሲወጣ ያስከብራል፣ አድናቂዎችም ያስገኛል፡፡ ሰው ፀጉሩን አበጣጥሮ የሚወጣው ወድዶ አይደለም፡፡ ለራሱ ብቻ ሳይሆን ለሰውም፣ ለሰው ብቻ ሳይሆን ለራሱም ሲል ነው፡፡ ያለበለዚያ ፀጉሩን አንጨባሮ/አንጨፍሮ የወጣ ሰው ምንም ብሩህ አዕምሮ ቢኖው፣ የውስጡን የሚያውቅለት ስለሌለ በቦዘኔነት ወይም ግዴየለሽነት ይፈረጃል፡፡

ፀጉርን አሳምሮ ሽክ ማለት እኮ ብዙ ይናገራል፣ ያናግራልም፡፡ ‹‹ፀጉሯ ወርዶ፣ ወርዶ!›› እየተባለ ይዘፈን የለም? ይሄ እኮ ዛሬ ተጀመረ ሳይሆን ጥንት ጥንታውያንም ያደርጉት ነበር፡፡ የጥንት ሰዎች (አሁንም እንደ ጥንቱ መለመላቸውን በሚኖሩ ማህበረሰቦች ውስጥ እንደሚታየው) የተዋበ የፀጉር አሰራር ዘዴ አላቸው፡፡ የፀጉራቸው አሰራር ዝርያቸውን ወይም ማህበራዊ ማንነታቸውን ገላጭ ነው፡፡ በአገራችንም እንደየአካባቢው ጎገሬ፣ ቁንጮ፣ ጋሜ፣ ጉድሮ፣ ሽሩባ ወዘተ… ወይም ‹‹ፍሪዝ›› የሚሰጠው ትርጉም እንዳለ ሁሉ፣ በሌላው ዓለምም ‹‹እንቁላል ራሶችን››፣ ‹‹ራስ ተፈሪያንስን›› እና የመሳሰሉትን መጠቃቀስ ይቻላል፡፡

የሰው ልጅ ከ2300 ዓመታት በፊት የፀጉር ቅባት፣ ከ8000 ዓመታት በፊት ደግሞ ማበጠሪያ ይጠቀም እንደነበር በጥናት ተረጋግጧል፡፡ በአጠቃላይ ሰዎች የፀጉር ማስዋብን ዘዴ ይጠቀሙ የነበረው ጊዜ ርቀት በ10 ሺዎች ዓመታት እንደሚቆጠሩ ከተገኙ ቅርሶች ታውቋል፡፡ አሁን ላይ ቆመን ጥንተ ጥንታውያን የዋሻ ሰዎች፣ እንዴት እንደኖሩ በዓይነ ህሊናችን መዳሰስ እንችል ይሆናል፡፡

ፀጉራቸውን ለመንከባከብና ለማስዋብ በቂ ጊዜ እንደነበራቸው እንገምታለን፡፡ እነሱ ቀልጣፎች ነበሩ፤ በቀላሉ የማደንና ምግብ የመሰብሰብ ብቃት ነበራቸው፡፡ ስለሆነም ለማህበራዊ ክንውኖች በቂ ትርፍ ጊዜ ነበራቸው፡፡ ለመዋቢያ፣ ማስዋቢያ ቁሳቁሶችን ለመስራት ጭምር ኋላ ቀር ከተባለ ማህበረሰብ ጀምሮ እስከ ዘመኑ የቁንጅና ሳሎኖች ድረስ፣ የፀጉር እንክብካቤ ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ ነው፡፡ በሂደት አንዳንዶቹ ከሌሎቹ የላቁ እንደሚሆኑና የበለጠ ተረፈላጊነት እንደሚኖራቸው ግልጽ ነው፡፡ ስለዚህ የፀጉር ማስዋብ ስራ እጅግ ጥንታዊ ከሆኑት የሙያ መስኮች አንዱ እንደሆነ አይጠረጠርም፡፡

ስለ ፀጉራችን ለምን እንጨነቃለን?

በርካታ ሰዎች የፀጉራቸውን ሁኔታ በመስተዋት እያዩ በየቀኑ ብዙ ሰዓት ያሳልፋሉ፡፡ ስለ ፀጉር ማሰብ ወንድ ሴት የማይል ከመሆንም በላይ ትልቅ ጭንቀት የሚፈጥርበት ጊዜም አለ፡፡

ስለ ፀጉርህ ሁኔታዎች እወቅ

በራስ ቅል ላይ በአማካይ 100,00 የሚደርሱ ፀጉሮች እንዳሉ ይገመታል፡፡ አንድ ነጠላ ፀጉር የሚያድገው  ዕድሜ ልክ ሳይሆን ከሁለት እስከ ስድስት ዓመት ለሚደርስ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ይረግፍና ከጥቂት የሽግግር ጊዜ በኋላ ከዚያው ቀዳዳ አዲስ ፀጉር መብቀል ይጀምራል፡፡ አንድ ነጠላ ፀጉር የራሱ የሆነ የአስተዳደግ ኡደት አለው፡፡ በዚህ ኡደት ምክንያት ምንም አይነት የፀጉር ችግር ከሌለበት ሰው እንኳን በእያንዳንዱ ቀን ከ70 እስከ 100 የሚደርሱ ፀጉሮች ይረግፋሉ፡፡

የፀጉር ቀለም የሚለያየው በምን ምክንያት ነው? ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፒዲያ እንዲህ በማለት ያብራራል፡፡ ‹‹የፀጉር ቀለም በአብዛኛው የሚወሰነው ሜላኒን የተባለው ጥቁር ቡናማ ቀለም ባለው ስርጭትና መጠን ነው›› ሜላኒን በፀጉር፣ በቆዳና በዓይን ውስጥ የሚገኝ የተፈጥሮ ቀለም ነው፡፡ የቀለሙ መጠን በጨመረ መጠን ፀጉርም ጠቆር እያለ ይሄዳል፡፡ የሜላኒን መጠን እያነሰ ሲሄድ ደግሞ የፀጉር ቀለም ከጥቁር ወደ ቡናማነት ወይም ወደ ቢጫነት ያደላ ይሆናል፡፡ ፀጉር ምንም ሜላኒን ከሌለው ግን ሙሉ በሙሉ ነጭ ይሆናል፡፡

ከፎረፎር ሌላ ብዙዎችን የማያሳስባቸው የፀጉር መርገፍ አለዚያም የፀጉር መሸበት ነው፡፡

የፀጉር አስተዳደግ

የፀጉራችን አስተዳደግ የራሱ ዑደት አለው፡፡ ፀጉር የማደጊያ፣ የመሸጋገሪያና የማረፊያ ጊዜ አለው፡፡ ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፒዲያ እንዲህ በማለት ያብራራል፡፡ ‹‹ፀጉር በማረፊያ ጊዜ ማደጉን ያቆማል፡፡ በዚህ ጊዜ አሮጌው ፀጉር የማደጊያው ጊዜ እስኪ ደርስ ድረስ በስሩ ላይ እንዳለ ይቆያል፡፡ በማደጊያ ጊዜ አሮጌው ፀጉር ይረግፍና አዲስ ፀጉር ከስር ይወጣል፡፡ ‹‹በማንኛውም ወቅት ከ85 እከ 90 በመቶ የሚደርስ ፀጉር በዕድገት ላይ ሲሆን ከ10 እስከ 15 በመቶ የሚሆነው በማረፊያ፣ በመቶ የሚሆነው በመሸጋገሪያ ጊዜ ላይ ይሆናል፡፡

ፀጉርህ ሸብቷል?

ሽበት ብዙውን ጊዜ የእርጅና እና የአረጋዊነት ምልክት ተደርጎ ይታያል፡፡ እርግጥ ነው፣ ዕድሜ እየገፋ ሲሄድ ፀጉር ይሸብታል፡፡ ይሁን እንጂ ሽበት የሚመጣው በእርጅና ምክንያት ብቻ አይደለም፡፡ ሽበት ጠቆር ያለ ፀጉር ባላቸው ላይ ጎልቶ የሚታይ ይሁን እንጂ ፆታም ሆነ የፀጉር ቀለም አይመርጥም፡፡

አንዳንዶች በመሸበታቸው ምክንያት ከዕድሜያቸው በላይ ያረጁ መስለው ሊታዩና ይህም አሳሳቢ ሊሆንባቸው ይችላል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ባለመሸበታቸው ምክንያት ትክክለኛው ዕድሜያቸውና መልካቸው አለመመሳሰሉ የሚያሳስባቸው ሰዎችም አይጠፉም፡፡

ፀጉር ከሸበተ ሞተ ማለት አይደለም፡፡ እርግጥ ነው በዓይን የሚታየው ውጪያዊ የፀጉር ክፍል በድን ነው፡፡ የእያንዳንዱ ፀጉር ስር ተብሎ የሚጠራ ሲሆን ህይወት ያለው የፀጉር ክፍል ይህ ብቻ ነው፡፡ የፀጉር ስር እንደ ፀጉር ፋብሪካ ሆኖ ያገለግላል፡፡ በስሩ ውስጥ ያሉት ሌሎች በብዛት ተራብተው ፀጉር ሲፈጠር የቀለም ሴሎች የሚሰሩትን ሜላኒን ይቀባል፡፡ በዚህም የተነሳ የቀለም ሴሎች ሜላኒን መስራት ካቆሙ ፀጉር ነጭ ይሆናል፡፡

የቀለም ሴሎች በድንገት ሜላኒን መስራታቸውን የሚያቆሙት ለምን እንደሆነ ማንም የማያውቅ የለም፡፡ በዚህም ምክንያት ለሽበት የሚሆን አስተማማኝ መድሃኒት ሊገኝ አልተቻለም፡፡ በተጨማሪም ስራቸውን አቁመው የነበሩ የቀለም ሴሎች እንደገና መስራት ሊጀምሩ እንደሚችሉ ተደርሶበታል፡፡

አንዳንዶች ሜላኒን እንደመወጋት ያሉትን አዳዲስ ህክምናዎች ይሞክራሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ ፀጉራቸውን ቀለም ይቀባሉ፡፡ ይህም ቢሆን ዛሬ የመጣ ልማድ አይደለም፡፡ የጥንቶቹ ግሪካውያንና ሮማውያን ፀጉራቸውን ቀለም ይቀበሉ ነበር፡፡ የጥንት ግብፃውያን በበሬ ደም ፀጉራቸውን ያቀልሙ ነበር፡፡

ይሁን እንጀ በየጊዜው ቀለም መቀባት ጊዜና ጥረት የሚጠይቅ ከመሆኑም በላይ የአንዳንዶችን ቆዳ ሊያስቆጣ ወይም ሊያቆስል ይችላል፡፡ ሽበትን በቀለም ማጥቆር ብንወስንም መቀባትን ለማቆም የምንፈልግበት ጊዜ ሊመጣ ይችላል፡፡ በዚህ ጊዜ ከስር የሚያድገውን ሽበት መሸሸግ አስቸጋሪ ይሆንብናል፡፡ ሽት በአዎንታዊ ጎኑ የሚያምርና ከዚህ በፊት ያልነበረህን ግርማ ሞስ የሚያስገኝልህ ሊሆን ይችላል፡፡

የፀጉር መሳሳትና ራስ በራነት

ሌላው የተለመደ የፀጉር ችግር የፀጉር መሳሳትና ራሰ በራነት ነው፡፡ እነዚህም ችግሮች ቢሆኑ ዛሬ የተፈጠሩ አይደሉም፡፡ በጥንቷ ግብፅ ለራስ በራነት ከአንበሳ፣ ከጉማሬ፣ ከአዞ፣ ከድመትት ከእባብና ከዝይ ስብ የተቀመመ መድሃኒት ይሰጥ ነበር፡፡ በዛሬው ጊዜ ራስ በራነትንና የፀጉር መሳሳት ይከላከላሉ የሚባሉ በርካታ ሸቀጦች ሲኖሩ ለእነዚህ ሸቀጦች በየዓመቱ የሚፈሰው ገንዘብ በጣም ብዙ ነው፡፡

በራነት የሚጀምረው ትክክለኛው የፀጉር አበቃቀል ሲዛባ ነው፡፡ ትክክለኛው የፀጉር አበቃቀል በምግብ አለ መመጣጠን፣ ረዥም ጊዜ በሚቆይ ትኩሳት ወይም በቆዳ በሽታ ባሉ ምክንያት የተነሳ ሊዛባ ይችላል፡፡ በተጨማሪም የፀጉር አበቃቀል እንደ እርግዝናና ልጅ መውለድ ባሉ ምክንያቶች ስለሚዛባ አዲስ ፀጉር መበቀል ከመጀመሩ በፊት ብዙ ፀጉር ሊረግፍ ይችላል፡፡ የፀጉሩን አስተዳደግ ያዛባው ምክንያት ሲወገድ ግን እንዲህ ያለው የፀጉር መርገፍ ይቆምና ወደ መደበኛው ሁኔታ ይመለሳል፡፡

ሌላው አይነት የፀጉር መርገፍ ደግሞ ላሽ ይባላል፡፡ ይህ ችግር በሚኖርበት ጊዜ በአንዱ አካባቢ ያለ በርካታ ፀጉር አንድ ጊዜ ይረግፋል፡፡ ላሽ የሚመጣው በሰውነት የበሽታ ተከላካይ ሕዋሳት ላይ በሚደርስ ቀውስ ምክንያት ሳይሆን እንደማይቀር በቅርቡ የተደረጉ የህክምና ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡

በጣም የተለመደው የፀጉር መርገፍ በወንዶች ላይ የሚደርሰው የራስ በራነት አይነት ነው፡፡ ከፊት ያለው ፀጉር ገባ ገባ በማለት ወይም መሀል አናት ላይ ሳሳ በማለት ይጀምርና ቀስ በቀስ እየተባባሰ ይሄዳል፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች ያለው የፀጉር እድገት የተዛባ ሆኖ ከቆየ በኋላ ቀስ በቀስ ጨርሶ ወደ ማቆም ይደርሳል፡፡ ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ እንዲህ በማለት ያብራራል- ‹‹በራነት በጀመረው አካባቢ በነበረው ረዥም፣ ጠንካራና ባለቀለም ፀጉር መብቀል ይጀምራል›› የፀጉር ዕድገት እየቀጠለ ሲሄድ እየሳሳና ዕድሜው እያጠረ ሄዶ ምንም ፀጉር ከማይበቅልበት ደረጃ ላይ ይደርሳል፡፡ ይህ የሚሆነው በዘር ውርሻና በወንዶች ሆርሞኖች ምክንያት ነው፡፡

የወንዶች ራስ በራን  ከአፍላ የጉርምስና  ዕድሜ አንስቶ ሊጀምር ቢችልም አብዛኛውን ጊዜ የሚጀምረው በ30ዎቹ ዓመት መገባደጃና በ40ዎቹ ዓመታት ዕድሜ ነው፡፡ እንዲህ ያለው የፀጉር መርገፍ በብዙ ወንዶች ላይ የሚደርስ ቢሆንም መጠኑ ከዘር ወደ ዘርና ከግለሰብ ወደ ግለሰብ ይለያል፡፡ ያም ሆነ ይህ ለዚህ ችግር የተረጋገጠ መድሃኒት ማግኘት አልተቻለም፡፡ አንዳንዶች በራቸውን ለመሸፈን ሰው ሰራሽ ፀጉር ለማድረግ ወይም በቀዶ ህክምና ፀጉር ለማስተካከል ይመርጡ ይሆናል፡፡ ለተቀረው ፀጉር ተገቢውን እንክብካቤ ማድረግ ፀጉር እንዳይረግፍ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል፡፡

የአንድ ሰው ፀጉር አንዴ መሳሳት ከጀመረ ጨርሶ ይመለጣል ማለት አይደለም፡፡ ነጠላ ፀጉሮች በመቅጠናቸው ምክንያት ሳስቶ ሊሆን ይችላል፡፡ ለመሆኑ የፀጉር ውፍረት ምን ያል ነው? አንድ ጥናት እዳመለከተው ከ50 እስከ 100 ማይክሮ ሊደርስ ይችላል አንድ ሰው እያረጀ ሲሄድ ፀጉሩ ይቀጥናል፡፡ የጥቂት ማይክሮኖች መቀነስ ብዙም ለውጥ የሚያመጣ ላይመስል ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ 100,000 የሚያክሉ ፀጉሮች መኖራቸውን አትዘንጉ፡፡ ስለዚህ ነጠላ ፀጉሮች በትንሹ እንኳን ቢቀጥኑ በጠቅላላው የፀጉር ብዛት ላይ የሚያስከትለው ለውጥ ከፍተኛ ይሆናል፡፡

ለፀጉር እንክብካቤ ማድረግ

ፀጉር በየወሩ 10 ሚሊ ሜትር ያህል ያድጋል፡፡ ፈጣን ዕድገት ካላቸው የሰውነት ክፍሎች አንዱ ነው፡፡ የሰውነት ፀጉሮች ዕድገት በሙሉ አንድ ላይ ቢጀመር በየቀኑ 20 ሜትር ያህል ያድጋል ማለት ነው፡፡

ለሽትና ለራስ በራነት ፍቱን የሆነ መድሃኒት ገና ያልተገኘ ቢሆንም ያለንን ፀጉር ለመንከባከብ ብዙ ልናደርግ የምንችለው ነገር አለ፡፡ በቂና የተመጣጠነ ምግብ መመገብና የራስ ቅል በቂ የደም ዝውውር እንዲያገኝ ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ ከመጠን በላይ ምግብ መቀነስ ወይም የተመጣጠነ ምግብ አለመመገብ ሽበትና የፀጉር መሳት ሊያፋጥን ይችላል፡፡ አዘውትረን ፀጉራችንን መታጠብና የራስ ቅል ቆዳን በጥፍር ሳይቧጥጡ ጥሩ አድርጎ ማሸት ጥሩ እንደሆነ ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡ ይህን ለማድረግ የራስ ቅል ጥሩ የደም ዝውውር እንዲያገኝ ያስችላል፡፡ ፀጉራችሁ በሳሙና ወይም በሻምፖ ከታጠባችሁ በኋላ ጥሩ አድርጋችሁ አለቅልቁት፡፡

ፀጉራችሁን በኃይል አታበጥሩ፡፡ ፀጉራችሁ ረዥም ከሆነ መጀመሪያ ላይ ከስራ ጀምሮ እስከጫፍ አለማበጠር ጥሩ ይሆናል፡፡ ከዚህ ይልቅ በመጀመሪያ ፀጉራችሁን መሀል ላይ ይዛችሁ ጫፍ ጫፉን በማበጠር አፍታቱት፡፡ ቀጥላችሁ ከመሀል አንስታችሁ እስከ ጫፍ አበጥሩ፡፡ በመጨረሻም ፀጉራችሁን ወደታች ልቀቁትና ከስር እስከ ጫፍ አበጥሩት፡፡

ፀጉራችሁ ሸብቶ ስታዩት ወይም ሲረግፍ ሊያሳስባችሁ ይችላል፡፡ ቢሆንም የፀጉራችሁ ሁኔታ አብዛኛውን ጊዜ እናንተን የማያሳስባችሁን ያህል ሌሎችን እንደማያሳስብ አስታውሱ፡፡ ፀጉራችሁን ቀለም መቀባት፣ ሰው ሰራሽ ፀጉር ማድረግ ወይም ህክምና ማድረግ ተፈልጎ ይሆናል፡፡ እንዲህ ማድረጉ ለእናንተ የተተወ ነው፡፡ የፀጉራችሁ ቀለም ምንም አይነት ይሁን ወይም ምንም ያህል ፀጉር ይኑራችሁ ዋና አስፈላጊው ነገር በንፅህናና በስርዓት መያዛችሁ ነው፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.