የደም ቧንቧ መስፋት በሽታ – መንስኤው፤ መፍትሄውና መከላከያው

0

bloodከኢሳያስ ከበደ | Zehabesha Newspaper

ሁለት አይነት የደም ቧንቧዎች አሉ፡፡ ኦክስጅን የተሸከሙና ደምን ከልብ ወደ ሌላው የሰውነት ክፍል የሚወስዱ የደም ቧንቧዎች አርተሪ ይባላሉ፡፡ ጥቅም ላይ የዋለውን ደም ከሌላው የሰውነት ክፍል ወደ ልብ የሚመልሱ ቧንቧዎች ደግሞ ቬን ይባላሉ፡፡

ደም መልሶችም ሆኑ ደም ቅዳ ቧንቧዎች በሁሉም የሰውነታችን ክፍሎች የሚገኙ ናቸው፡፡ ደም ቧንቧን እንደ አንድ ፕላስቲክ ቲዩብ ወስደን መሀል ላይ ቆርጠን ብናየው ግድግዳውን ማየት እንችላለን፡፡ ደም ቅዳ ቧንቧ ግድግዳው ወፍራም ነው፡፡ የውስጠኛው፣ መካከለኛውና የላይኛው ተብለው የሚከፋፈሉ ሶስት ክፍሎች አሉት፡፡ በሌላም በኩል ደም መልስ ቧንቧዎች ግድግዳቸው ቀጭን ነው፡፡ ለዚህ ይመስላል፣ ከደም ቧንቧ መስፋት ጋር ለተያያዙ የጤና ችግሮች የተጋለጡ የሚሆኑት፡፡

ዛሬ በዚህ የደም ቧንቧ መስፋት ችግር ዙሪያ ለአንባቢዎቻችን ሰፋ ያለ መረጃ ለመስጠት ፈልገን አንድ የቀዶ ጥገና ህክምና ስፔሺያሊስትን ማብራሪያ ጠይቀናቸው ነበር፡፡ እንዲያነቡት ጋብዘናል፡፡

ጥያቄ፡- የደም ቧንቧ መስፋት ራሱን የቻለ በሽታ ነው ወይስ የሌሎች በሽታዎች ምልክት ነው? መንስኤውስ ምንድነው ይላሉ?

ዶ/ር፡- የደም ቧንቧ መስፋት (ማቆር) ራሱን የቻለ በሽታ ነው፡፡ ደም በታችኛው የሰውነት ክፍላችን ወይም ከእግራችን አካባቢ በፍጥነት ወደ ሳንባና ልብ መመለስ ሲገባው፣ ለረዥም ጊዜ እግራችን ውስጥ ከቆየ የደም ቧንቧውን እየለጠጠው እና እያሰፋው ይሄዳል፡፡ ቀላል የሆኑ  በቆዳ ላይና ከቆዳ ስር ትናንሽ ሽንትርትር ነገሮች በተለይ ሴቶች ላይ በታፋና በእግር ጀርባ አካባቢ ይታያሉ፡፡ ከዚህ ተነስቶ ከእግራችን ጀርባ አረንጓዴ (ሰማያዊ) የሆኑ ትላልቅ እብጠቶችን የሚያመጡ የደም ቧንቧዎች መቋጠር ይታያል፡፡ ይህ ችግር ገፍቶ ከፍተኛ ደረጃ በሚደርስበት ጊዜ አልሰር እስከ መፍጠር እንዲሁም የእግሮቻችንን ከለር እስከ መቀየር ሊደርስ ይችላል፡፡

የደም ቧንቧ መስፋት የራሱ የሆኑ መንስኤዎች ያሉት በሽታ ነው፡፡ ከመንስኤዎቹ አንፃር ዋና ዋና የምንላቸውን እንይ፡-

– ደም መልስ ቧንቧዎች ደምን ወደ ታችኛው የአካል ክፍል እንዳይመለስ የሚያደርጉ ቫልቮች አሏቸው፡፡ እነዚህ ቫልቮች ብዙውን ጊዜ በተፈጥሮ አለመኖር፣

– ደምን ወደታችኛው የአካል ክፍል እንዳይመለስ የሚያደርጉ ቫልቮች በተፈጥሮ ደካም በሚሆኑበት ጊዜ፤

– ለረዥም ጊዜ ቁሞ መስራት ደም እግራችን አካባ ለረዥም ጊዜ እንዲቆይ ስለሚያደርገው ደም መልስ ቧንቧዎች እየተለጠጡ ይሄዳሉ፤

– በእርግዝና ወቅት የተለያዩ አካላዊና የሆርሞን ለውጦች ይከሰታሉ፡፡ በዚህ ምክንያት በእርግዝና ወቅት የደም ቧንቧ መለጠጥ ይከሰታል፤

– ለረዥም ጊዜ የቆየ ጉበት በሽታ የደም ቧንቧ መስፋትን ያጣል፤

– የፊንጢጣ ኪንታሮት፡፡

ጥያቄ፡- ከፆታ አንፃር በጤና ችግሩ የበለጠ ተጋላጭ ማነው?

ዶ/ር፡- በደም ቧንቧ መስፋት ከወንዶች ይልቅ ሴቶች የበለጠ ተጋላጭ ናቸው፡፡

ጥያቄ፡- ምልክቱ ምንድነው?

ዶ/ር፡- የደም ቧንቧ መስፋት ብዙ ምልክቶችን አያሳይም፡፡ ነገር ግን ችግሩ እየጨመረ ሲመጣ ለረዥም ሰዓት በሚቆምበት ጊዜ የተወሰኑ ምልክቶችን ያሳያል፡፡

– ከፍተኛ የእግር ህመም ስሜት ይኖራል፤

– እብጠት ይኖራል፤

– ውሃ መጠራቀም ይከሰታል፤

– በተለይ ሴቶች ላይ በመቀመጫና በእግር ጀርባ አካባ ሸንተረር የመሰሉ ነገሮች በብዛት ይታያሉ፡፡

– የቆዳ ከለሩ ስለሚቀየር ለእይታ የሚማርክ አይሆንም፤

– ችግሩ መፍትሄ ካልተሰጠውና እየቆየ የሚሄድ ከሆነ እግር አካባ አልሰር ይፈጥራ፡፡

– የቆዳ ቀለም መዥጎርጎር

– የደም ዝውውር መስተጓጎል

– የተለያዩ ቁስሎች ሲፈጠሩ አለመዳን

– የቆዳ መብለጭለጭ

ጥያቄ፡- ደረጃ ካለው ብናየው?

ዶ/ር፡- የደም ቧንቧ ጥበት በሽታ ራሱን የቻለ 4 ደረጃዎች አሉት፡፡ ደረጃቸውን ቀለል ባለ መልኩ ለመግለፅ የጠና ችግሩ እያለ ምንም አይነት ምልክት ሳይኖር ሐኪሙ ብቻ ሲመረምር የሚያገኘው ከሆነ ደረጃ አንድ እንለዋለን፡፡ በሽታው ደረጃ ሁለት ላይ ከደረሰ በእንቅስቃሴ ወቅት ብቻ እገራችንን የህመም ስሜት የሚሰማን ይሆናል፡፡ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል የምንለው፤ ምንም አይነት እንቅስቃሴ ሳይኖር በረፍት ላይ ሁነን የህመም ስሜት መሰማት ከመረ አስጊ ሊባል የሚችል

ደረጃ ላይ መድረሱን ያመላክታል፡፡ ከዚህ ከፍ ሲልም እግር ላይ ቁስለት ሊፈጥር ይችላል፡፡ እዚህ ከደረሰ የከፋ የሚባል ደረጃ ላይ መድረሱን ያሳያል፡፡

ጥያቄ፡- የደም ቧንቧ መስፋት (ማቆር) በሽታ የተከሰተ መሆኑን ለማረጋገጥ የሚካሄደው ምርመራ ምንድነው ይላሉ?

ዶ/ር፡- በሽታው መከሰቱን ለማወቅ ምንም የሚያስቸግር ነገር የለም፡፡ ምክንያቱም ደም መልስ የሚባሉ የደም ቧንቧዎች ከውጭ በግልፅ የሚታዩ በመሆኑ በዓይናችን በማየት ብቻ ማረጋገጥ እንችላለን፡፡ ለደም ቧንቧ መስፋት ምንም አይነት የማረጋገጫ ምርመራ ማድረግ የሚያስፈልገው አይደለም፡፡

ጥያቄ፡- በህክምና ያለው መፍትሄ ምንድነው?

ዶ/ር፡- ለደም ቧንቧ መስፋትን እያንዳንዱ ሰው በቤቱ ውስጥ ሊያደርገው የሚገባ መፍትሄ ይኖራል፡፡ ለምሳሌ ለረዥም ሰዓት አለመቆም፣ ስራ መስራት ካለብን ቶሎ ቶሎ እየተቀመጡ እረፍትን ልምድ ማድረግና ስንቀመጥ እግራችንን ከፍ አድርገን መቀመጥ ጠቃሚ ይሆናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ወፈር ያሉ ስቶኪንጎችን በመጠቀም፣ የሰፋውን የደም ቧንቧ ጨምቀው እንዲይዙትና ደም እንዳያቁር ማድረግ ይቻላል፡፡ በእነዚህ ሁኔታዎች የማይመለስ ከሆነ፣ በህክምናው ያለው የመፍትሄ አማራጭ በቀዶ ህክምና የሰፋውን የደም ቧንቧ ቆጦ ማውጣት ብቻ ነው፡፡

ጥያቄ፡- የደም ቧንቧ መስፋት በወቅቱ ካልታከመ የሚያስከትለው ጉዳት ምንድን ነው?

ዶ/ር፡-የማይድን አልሰር ወይም ሰፊ ቁስል ይፈጥራል፡፡ የተፈጠረው ቁስል የማያቋርጥ ስቃይ ያመጣል፡፡ መራመድን መከልከልና የእግር ውበትን ይቀንሳል፡፡ በተጨማሪም ጫማ አድርጎ ለመጓዝ ያስቸግራል፡፡ በስተመጨረሻም የአጥንት ኢንፌክሽን ያመጣል፡፡

ጥያቄ፡- እንዴት እንከላከለዋለን?

ዶ/ር፡- ህብረተሰቡ ስለደም ቧንቧ መስፋት (ማቆር) በሽታ መኖሩንና ችግሩ በቀላሉ ሊታይ የሚችል እንዳልሆነ እንዲገነዘብ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ ውጭ የደም ቧንቧ መስፋትን ለመከላከል የሚያስችሉ ብዙ ነገሮች የሉም ማለት ይቻላል፡፡ ነገር ግን የባታችንን ጡንቻዎች የሚያጠነክሩ አካላዊ እንቅስቃሴዎችን መስራት በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ አዘውትሮ በእግር መራመድ፣ በስራ ቦታ ብዙ ከመቀመጥና ከመቆም በተወሰነ ጊዜ ውስጥ መንቀሳቀስ ጠቃሚ ይሆናል፡፡ በስተመጨረሻ ሁሉም ሰው በእግር አካባቢ የህመም ሆነ የቆዳ ለውጦች ሲኖሩ በቀላሉ ማለፍ የለበትም፡፡ ሁልጊዜም የደም ቧንቧ መስፋትን ማሰብ ይኖርበታል ለማለት እወዳለሁ፡፡

Spread the love
  •  
  •  
  •  
  •  
  •  
  •  
  •  
  •  
  •  
  •  

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.