በዶ/ር ሆነሊያት ኤፍሬም

በእርግዝና ጊዜ ሲለሚከሰት ከፍተኛ የደም ግፊት መጨመር እና ከፍተኛ መጠን ያለው የፕሮቲን መጠን በሽንት ውስጥ እንዲኖር ስለሚያደርገው በሕክምናው Preeclampsia

(ፕሪኢክላምፕሲያ) ብለን ስለምንጠራው የሕመም ዓይንት በጥቂቱ ልንገራችሁ፡

በእርግዝና ጊዜ የደም ግፊትን መጨመር የሚያስከትለው ትክክለኛ ምክንያት በእርግጠኝነት የማይታውቅ ቢሆንም በዚህ ዙሪያ የሚያጠኑ ተመራማሪዎች ግን የሰውነት ስብ መከማቸት፤የተመጣጠነ ምግብ አለመመገብ፤ለማሕፀን የሚደርሰው የደም ፍሰት መቀነስ እና ተፈጥሮአዊ ሁኔታን እንደ ምክንያት ያስቀምጣሉ፡፡

በእርግዝና ጊዜ ለደም ግፊት መጨመር ሊያጋለጡ የሚችሉ ሁኔታዎች ምንድን ናቸው?

•በእርግዝና ጊዜ የደም ግፊት መጨመር በአብዛኛው የሚከሰተው በመጀመሪያው እርግዝና ላይ እና ዕድሜያቸው ከ20ዓመት በታች ወይንም ከ40 ዓመት በላይ ያሉ ሴቶች ላይ ነው፡፡
በተጨማሪ፡- ከእርግዝናው በፊት የደም ግፊት ችግር ያለባት ሴት
– ከዚህ ቀደም በነበረ እርግዝና ጊዜ የደም ግፊት የነበረባት ሴት
– በእርግዝና ጊዜ የደም ግፊት ያጋጠማት እናት ወይም እህት ያላት ሴት
– የሰውንት ክብደት መጨመር
– በቁጥር ከአንድ ልጅ በላይ እርግዝና
– የስኳር ወይም የኩላሊት ሕመም ያለባት ሴት

በእርግዝና ጊዜ የሚከሰት የደም ግፊት መጨመር ምልክቶች ምንድን ናቸው?

• ከደም ግፊት መጨመርና በሽንት ውስጥ ከሚገኝ ከፍተኛ የፕሮቲን መጠን በተጨማሪ
– ፈጣን የሆነ ሰውንት ክብደት መጨመር (በሰውነት ውስጥ የሚከማች ፈሳሽ)
– የሆድ ሕመም
– ከፍተኛ የሆነ የራስ ምታት
– ከሌላው ጊዜ የቀነሰ የሽንት መጠን ወይንም ምንም ሽንት አለመኖር
– ማዞር
– ከፍተኛ የሆነ ማስመለስና ማቅለሽለሽ ናቸው፡፡
ከመደበኛ የእርግዝና ክትትል በተጨማሪ አንዲት እርጉዝ ሴት የሚከተሉትን ሁኔታዎች ካስተዋለች ወደ ሕክምና ቦታ በመሄድ መታየት ያስፈልጋል፡፡

እነዚህም፡-
1. የደም ግፊት መጠን ከ140/90 በላይ ከሆነ
2. ድንገተኛ የሆነ የሰውነት ክብደት መጨመር
3. የሆድ ሕመም
4. ከፍተኛ የራስ ምታት
5. የሽንት መጠን መቀነስ
6. የዓይን በዥታ፤ተንሳፋፊ መስል ነገሮችን ማየት ካለ ናቸው፡፡
7. ድንገተኛ ወይንም አዲስ የሆነ የእጅ የዓይን አካባቢ እና የፊት ማበጥ መጠነኛ የሆነ የእግር ማበጥ ግን በእርግዝና ጊዜ በአብዛኛው የሚከሰት ነው፡፡

በእርግዝና ጊዜ የሚከሰት የደም ግፊት መጨመር አንዳንድ ጊዜ ምንም ዓይነት ምልክትን ላያሳይ ስለሚችል አደጋ ላይ ላለመውደቅ መደበኛ የእርግዝና ክትትል ማድረግን አለማቋረጥና የደም ግፊት መጠንን በየጊዜው መለካት ተገቢ ነው፡፡

ጤና ይስጥልኝ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.