ብዙዎቻችን የጠዋት ስሜት ቀኑን ሙሉ ምን አይነት ተፅዕኦ እንዳለው አናስተውልም።

ይሁን እንጂ ዘወትር ጠዋት የምንፈፅማቸው ነገሮች ሁሉ ቀናችንን ብሩህ ወይም ጤናማ ያልሆነ የማድረግ አቅም አላቸው።

በየእለቱ ጠዋት የምንፈፅማቸው መጥፎ ልማዶችም እየተለመዱ ይሄዱና በህይዎታችን ላይ የራሳቸውን ተፅእኖ ያሳድራሉ።

ቀጥሎ ዘወትር ጠዋት የምንፈፅማቸው አምስት ስህተቶችን እንመለከታለን።

1. በመጥፎ ስሜት ከእንቅልፍ መንቃት

አንዳንድ ጊዜ በሚረብሽ ድምፅ ወይም ምቹ ባልሆነ ሁኔታ ከእንቅልፍ መንቃትን ማስወገድ አይቻልም።

በጠዋት የመንቃት ችግር ያለባቸው ሰዎች የሚረብሽ ድምፅ ያለው የማንቂያ ደወልን መጠቀማቸው መፍትሄ እንደማይሆንም ይነገራል።

ይህ የሚረብሽ ድምፅ በጠዋት የመጀመሪያውን ስሜትዎን ደብዛዛ የሚያደርግ ይሆናል።

ከእንቅልፍ ከነቁ በኋላ አልጋ ላይ ከመገላበጥ ይልቅ መነሳት ጥሩ ስሜት እንዲኖረን እንደሚያደርግም ነው የሚነገረው።

በሚረብሹ ድምፆች ያለጊዜ የሚነቁ ሰዎች የሚወዱትን ሙዚቃ እያዳመጡ አጭር እንቅልፍ ወይም ናፕ መውስድ ከዚህ ስሜት ለመውጣት ይረዳቸዋል።

2. ጥድፊያ

በጠዋት ለየእለት ኑሯችን መቻኮል አዕምሯችን በቀን ውስጥ የሚያከናውናቸውን ተግባራት በተገቢው መንገድ እንዳያከናውን ያደርገዋል።

ስለሆነም አዕምሮአችን በቀላል ተግባራትና በሚወስዱት ጊዜ ላይ ብቻ ያተኩራል።

ስለዚህ ወደ ስራ ከማምራታችን በፊት ከ30 ደቂቃ በፊት ከአልጋ በመነሳት መዘጋጀት በውሏችን የምናከናውናቸውን ነገሮች ምክንያታዊ በሆነ ጊዜ ለማጠናቀቅ ይረዳል።

3. ቁርስን መዝለል

ይህ በአብዛኛው የሚከሰተው ስንቻኮል ሲሆን፥ አንዳንድ ሰዎች በተለያየ ምክንያት ቁርስ አይመገቡም።

የቁርስን ጥቅም ካለመረዳትና ክብደት ለመቀነስ በሚል አንዳንድ ሰዎች በጠዋት እንደ ሻይና ቡና መጠጣትን በቂ አድርገው ይወስዱታል።

ቡና ምንም እንኳን የማነቃቃት አቅም ቢኖረውም ሰውነታችን የሚፈልገውን ያህል ሀይል እንዲያገኝ አያስችልም።

ስለሆነም ፍራፍሬዎችን፣ ካርቦሃይድሬትና ፕሮቲን የምናገኝባቸውን ምግቦች በጠዋት መውሰድ ቀና ቀን እንዲኖረንና በስራችንም ውጤታማ እንድንሆን ያደርጋል።

4. በቀጥታ ወደ ስራ መግባት

ብዙዎቻችን ወደ ስራ ካመራን በኋላ ወይም ከእንቅልፍ ከነቃን በኋላ በመጀመሪያ የምናደርገው የተላኩ መልዕክቶችን መመልከት፣ ለደንበኞቻችን ስልክ መደወል አልያም ከዚያ ቀን በፊት በተከናወኑ ስራዎች ላይ የታዩ ክፍተቶችን ለመሙላት መሯሯጥ ነው።

በጠዋት በቀጥታ ራሳችንን ወደ ስራ ማሰማራት መልካም ቢመስለንም፥ ምንም የሚያረጋጋና ማሟሟቂያ ጊዜ ስለማይኖረን በረዥም ጊዜ ውጤታማነታችን ላይ የራሱን ተፅዕኖ ያሳድራል።

በጠዋት በቀጥታ ወደ ስራ ከመግባታችን በፊት ራሳችንን የማዳመጫ ጊዜ ወይም በእንቅስቃሴም ሆነ በሌላ ራሳችንን ዘና የሚያደርግ ጊዜ መስጠት ተገቢ ነው።
ይህም ስራችንን በሙሉ ትኩረትና ንቃት ለማከናወን ይረዳል።

5. ከባድ ተግባራትን ማዘግየት

በጠዋት የሆነ ስራ ስንጀምር በመጨረሻ ለማከናወን የምንፈቅደው አስቸጋሪውን ነገር ነው።

ይሁን እንጂ በጠዋት ከባድ የምንላቸውን ስራዎች ማከናወን ሌሎች ስራዎችን ቀኑን ሙሉ በትጋትና በተነቃቃ ስሜት እንድንሰራ ያግዛል።

እያንዳንዳችን ሁሌም አሪፍ ጠዋት ይኖረናል ማለት አይቻልም። ሁላችንም ተመሳሳይ የጠዋት መጥፎ ልማዶች አለን ማለትም አይደለም።

ይሁን እንጂ ሁላችንም ማራኪ ቀን እንዲኖረን የጠዋት ስሜታችን ወሳኝ በመሆኑ ጠዋታችንን በማስተዋልና ከላይ ከዘረዘርናቸው መጥፎ ልማዶች በመራቅ ከጀመርነው በኑሯችን ስኬታማ መሆን እንችላለን።

ከላይ የጠቀስናቸውን ክፉ ልማዶች ለማስወገድ ችግሮች ቢገጥሟችሁም ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ የተለያዩ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ በተደጋጋሚ መሞከር ጥሩ ውጤት ያስገኛል።

ምንጭ፦ http://time.com/

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.