(ዘ-ሐበሻ) ከትዳር ውጭ ከሌላ ሰው ጋር አካላዊ ግንኙነት ማድረግ ለብዙዎቹ የትዳር ጥምረቶች መፍረስ በምክንያትነት ይቀመጣል፡፡ የረጅም ጊዜ የጤና እክል፣ በልጆች አስተዳደግ ላይ የሚፈጠር የሐሳብ ልዩነት፣ የአንድ ወገን ግላዊ ሩጫ ለዚህ ተቋም መናጋት ብሎም መፍረስ ተጠቃሽ ሰበቦች ናቸው፡፡ ነገር ግን ከትዳር ውጪ መሄድን የግንኙነቱ ጥንካሬና ጤናማነት ማሳያ አድርገው የሚወስዱት አሉ፡፡ የቅርብ ጊዜ የምርምር ውጤቶች ደግሞ ሚስቶች፣ ባሎቻቸውን ለማጥቃት ከፍ ሲልም ለመግደል ውስልትናን ነው መነሻ የሚያደርጉት፡፡

በዚህ ጽሑፍ በእርግጥ ከትዳር ውጪ ከሚደረግ ውስልትና በኋላ ያ ትዳር እስከ የትኛው ጥግ ድረስ መሄድ ይችላል? ፍቺ መሰረታዊ መፍትሄ ነወይ? የሚለውን ለማየት ይሞክራል፡፡

ጊዜ የተጎዳውን የተጣማሪ ቁስል ሲፈውስ፣ አቻዊ ጥቅሞች ሚዛን ሲደፉ፣ አንዳንድ ትዳሮች ከውስልትናም በኋላ ጠንካራና የተሻለ ቤተሰብ በመፍጠር ይዘልቃሉ፡፡

ከትዳር ወይም ከፍቅር ግንኙነት መፎረፍ አካላዊ መገለጫዎች አሉት፡፡ መጽሐፉስ ‹‹ያየ የተመኘ…›› አይደል የሚለው፡፡ በመንገድ ወይም በሥራ ቦታ ወይም በመጓጓዣ/ታክሲ… ውስጥ ለአጭር የፍቅር ጨዋታ የተመኛት ሴት ያለች እንደሆነ፣ በተግባር ሳይፈጽመው ቆይቶ ወደ ሚስቱ ቢመለስም ይሄ ሰው ለትዳሩ ታምኗል የሚያሰኙትን መሰረታዊ ሐሳቦች ንዷቸዋል፡፡ ነጥቡ በተመሳሳይ ለሴቶችም እውነት ነው፡፡ ሰዎች ከትዳር ውጪ መሰል ተግባር ውስጥ ሲገቡ፣ ከግንኙነታቸው ማምለጫ መንገድ እየፈለጉ እንደሆነ ማሳያም ነው፡፡

ከትዳር ውጪ ለመሄድ የሚቀመጡ መነሻዎች
ከትዳር ውጪ ለመሄድ ብዙ መነሻ ምክንያቶችን መቁጠር ይቻላል፡፡ ለአንዳንዶቹ እንደውም ወደዚህ ተግባር ለመግባት የተጓዳኛቸው የወሲብ ግንኙነት መነሻ ምክንያት አይደለም፡፡ ለራስ የሚሰጥ ዝቅተኛ ግምት፣ የአልኮል ጥገኝነት፣ ልክ ያጣ የወሲብ ሱሰኝነት ናቸው ዋና ዋናዎቹ መነሻዎች፡፡

ከትዳር ውጪ የሚሄዱ ሰዎች ጨምረዋል
ምን ያል ሰዎች ከትዳራቸው ውጪ ይሄዳሉ? ጥናቶች በዚህ ጉዳይ ላይ ተጨባጭ ውጤት ለማምጣት ተቸግረው ቆይተዋል፡፡ የቅርብ ጊዜዎቹ ግን ለጥሩ ምላሽ የተቃረቡ ይመስላል፡፡ የጥናቶቹ ሌላ ሪፖርት ሙሉ ህይወታቸውን በትዳር ውስጥ ካደረጉት መካከል 25 በመቶ ወንዶች ከሚስቶቻቸው ውጪ የወሲብ ግንኙነት ፈፅመዋል፡፡ በሴቶቹ በኩል ደግሞ ለአንዴም ሆነ በተደጋጋሚ ጊዜ (ድግግሞሹ በጥናቱ አልተካተተም) ከሌላ ሰው ጋር አልጋ የተጋሩት ከ10-15 በመቶ የሚሸፍኑት መሆናቸውን ነው፣ በናሽናል ሄልዝ ሚሬጅ ሪሶርስ ባለቤትነት የተሰራው ጥናት የጠቆመው፡፡ በዚህ ረገድ አውቀውም ሆነ ሳያውቁት በላያቸው ላይ የተማገጠባቸው ሰዎች ትዳራቸውን ለዘለቄታው አቆይተዋል ወይም ወጋ ከፍለዋል፡፡

ለመማገጥ መጨመር የሚቀመጡ ምክንያቶች ምንድናቸው?
ከትዳር ውጪ ለመማገጥ ግፊት ከሚሆኑ ምክንያቶች መካከል በወጣትት ዕድሜ የሚደረጉ ጋብቻዎች በምክንያትነት ይጠቀሳሉ፡፡ በ16 ዓመት የዕድሜ ክልል ትዳር የሚመሰርቱ፣ 23 ዓመት ከሞላቸው አንፃር ለመማገጥና ድብቅ ግንኙነትን ለመመስረት ከፍተኛ ዕድል አላቸው፡፡ በዚህም በአንፃራዊነት በአራት እጥፍ ለትዳራቸው ታማኝ አይሆኑም ይላሉ ጥናቶች፡፡ የጥናቱ ባለቤቶች ደረስንበት ያሉት ሌላው ውጤት ከፍተኛ ገቢ ለውስልትና ያለው ድርሻ ከፍተኛ መሆኑ ነው፡፡ በአሜሪካ በአማካኝ በዓመት 75 ሺ ዶላር የሚያገኙ ግለሰቦች፣ በዓመት 30 ሺ ዶላር ከሚያገኙት በ1.5 በመቶ በበለጠ ይማግጣሉ፡፡ ከዚህ በቀር ምንም አይነት ሃይማኖት የሌላቸው ሰዎች ለመማገጥ የተጋለጡ ተብለው የተለዩ መሆናቸው ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች በ2.5 በመቶ በጨመረ ሁኔታ ለትዳራቸው ታማኝ አይደሉም ተብሏል፡፡

መማገጥ የጤና ችግር ነው?
መማገጥን የጤና ችግር አድርጎ ለመደምደም የሚያበቁ፣ በቂ ምክንያቶችን ማግኘት እንደማይቻል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የስነ ልቦና መምህር የሆኑት ዶ/ር አበባው ምናዬ ይናገራሉ፡፡ ድርጊቱ የጤና ችግር ከመሆኑ ይልቅ በማህበራዊ እንቅስቃሴያችን የሚቃኝ፣ በሰዎች ማንነት ልክ የሚመዘን ነው፡፡ በአንፃሩ በተጨናነቁ የህዝብ ማመላለሻዎች እርካታን ፍለጋ ከሚተሻሹት፣ ህፃናትን እደሚያባልጉትና ፆታዊ ጥቃቶች ላይ እንደሚገኙት ‹‹ከትዳር ውጪ መሄድ የጤና እክል ነው›› ብሎ መቁጠር አይቻልም፡፡ ከውስልትናው ተግባር በኋላ ሰዋዊ ባህሪያቸው ግድ ብሏቸው የፀፀትና የበዳይነት ስሜት ይጎዳቸዋል፡፡ ይሄ የሚያሳየን በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ወደ ቀደመው ማንነታቸው እንደሚመለሱ ማረጋገጫዎች መኖራቸውን ነው፡፡
ጥናቶቹ ሌሎች ሦስት መሰረታዊ ግፊቶችን ለትዳር መማገጥ በምክንያትነት ያስቀምጣሉ፡፡ የመጀመሪያው በወሲባዊ ግንኙነት ባለመጣጣም ሳይሆን በግጭት ሳቢያ ስሜታዊ በመሆን ድርጊቱን መፈፀም ነው፡፡ ይሄ በአምባ ጓሮው ምሽት ቤት ጥሎ መፈርጠጥና ሌላ ሰው አልጋና ደረት ላይ መገኘት፣ ሲነጋ ጠዋት ወደ ራሳችን ስንመለስም ለፀፀት መብቃትን የሚያስከትል ነው፡፡ ሁለተኛ ከፍተኛ የወሲብ ፍላጎት የሚያመጣው ነው፡፡ በሶስተኝነት የተቀመጠው ደግሞ የሁለቱ ጥምረት ማለትም ቀደም ሲል የነበረውን ፍላጎት ግጭቱ ሲደግፈው የሚፀም ይሆናል፡፡
ሴቶች በዋናነት በስሜታዊነት ሳቢያ፣ ከትዳራቸው ውጪ ለመሄድ የበለጠ እድል ሲኖራቸው ወንዶች ደግ ከፍተኛ የወሲብ ፍላጎት በሚያስከትለው ግፊት ለትዳራቸው ታማኝ እንዳይሆኑ ያደርጋቸዋል፡፡ ጥናቶች በሌላ መልኩ ለውስልትና መፈፀም ሂያጆቹ ያሉበትን የዕድሜና የትምህርት ደረጃ ምክንያት ያደርጋሉ፡፡
በትዳር ደስተኛ አለመሆን ቀዳሚው ነው፡፡ ትዳራቸው እንዳሰቡት ደስተኛ የማያደርጋቸው ሰዎች ከሂያጆቹ አንፃር በ4 እጥፍ የመማገጥ ዕድል አላቸው፡፡ ተፋትተው ወደ ትዳር የሚመጡት ደግሞ ምንም ፍቺ ካልፈፀሙት በሁለት እጥፍ ለትዳራቸው ታማኝ አይደሉም ይላል ጥናቱ፡፡ እንግዲህ በወጣትነት ዕድሜ ትዳር መያዝ መታሰር መስሎ የሚታያቸው፣ በስራ ምክንያት ከአካባቢያቸውና ከቤታቸው ርቀው የሚኖሩ፣ የገቢ ማደግ እና ምንም አይነት ሃይማኖት አለመከተል ሰዎች ታማኝነታቸውን እንዳያከብሩ የሚያደርጉ ፈተናዎች ተብለው ተለይተዋል፡፡
በትዳር ላይ መማገጥ፣ ከኢኮኖሚ፣ ከጤና እና ከቤተሰብ አንፃር የሚያስከትላቸው ቀውሶች አሉት፡፡ ከትዳር ውጪ የሚደረጉ ውስልትናዎች ፍቅር ፍለጋ ብሎ መለየት እንደማይቻል የሚናገሩ አሉ፡፡ ከዚያ ይልቅ የገንዘብ ትስስሮሽም ይኖሩታል፡፡ ቤትን በመበደል ለድብቁ ግንኙነት ጥሪትን ማሟጠጥም ይከተላል፡፡ ድርጊቱ ሲጋለጥ ከትዳር አጋር ጋር ከሚጀመረው ጭቅጭቅ አንስቶ ለልጆች መጥፎ አርአያነትን ያስተምራል፡፡ ማህበረሰቡም በግለሰቡ ላይ ገንብቶት የኖውን ክብር ይነጥቃል፡፡ በሌላ አገላለፅ መገለል ይፈጠራ ማለት ነው፡፡ እዚህ ጋ አንዳንድ ሴቶች አሁንም፣ መማገጥን ባሎቻቸውን ለመደብደብና ከፍ ሲልም ለመግደል ዋነኛ መነሻ ምክንያታቸው እንደሆነ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡
ያለንበት 21ኛው ክፍለ ዘመን ብዙ የአስተሳሰብ ውጥንቅጦችን አስፍቷቸዋል፡፡ ቀደም ሲል ከነበሩ አስተሳሰቦች በተለየ መልኩ፣ ማጋጣ ወይም ወስላታ ግለሰቦች ከመደበኛ ግንኙነታቸው ጋር በኢኮኖሚና ሌሎች ውለታዎች በመተሳሰራቸው ሳቢያ የሚደርስባቸው ጫና በእጅጉ ቀንሷል የሚሉ አልጠፉም፡፡ ድርጊቱ ድሮ ከሚታይበት አስተያይ ዛሬ ሁኔታዎች የተለየ መንገድ እንዲይዝ እያስገደዱ መሆኑን ነው የስነ ልቦና ባለሙያው ዶ/ር አበባው የሚናገሩት፡፡ ሞሉ ኢኮኖሚውና ማህበራዊ ዕድገቱ እየተዳከመ በመምጣቱ፣ ችግሩ ሲፈጠርም መደንገጡና መበሳጨቱ እንደወትሮ አይደለም፡፡ ዶ/ር አበባው እንደሚሉት፣ ከትዳር ይልቅ ተቋምነት አንፃር፣ ወሲብ ለዚህ ግንኙነት ዘለቄታዊነት ትልቅ ጉዳይ ቢሆንም ብዙ መሰረታዊ ጉዳይ ታሳቢ ያደርጋሉ፡፡ ሀብት፣ ልጅ ማሳደግ እንዲሁም የሁለቱም ትዳር ተጣማሪ ቤተሰቦች መካከል የሚፈጠረው ትስስር ሁሉ የትዳር ውጤት ነው፡፡ አንዱ ወገን ከትዳር ውጪ ቢሄድና ድርጊቱ በሌላኛው ቢደረስበት ከዚያም ወደ ፍቺ ሲኬድ፣ ብዙ ነገር ይበላሻል፡፡

በመማገጥ የተሰበሩ ልቦች በእርግጥ ይጠገናሉ?
ዶ/ር አበባው እንደሚሉት አዕምሮአችን ‹ኢድ፣ ኢጎ› እና ‹ሱፐር ኢጎ› በሚባሉ ክፍሎች ይከፈላል፡፡ ሰዎች ካገኙት ጋር ይሄዱ ዘንድ የሚገፋፋቸው ‹ኢድ› የሚባለው ክፍል ሲሆን ይሄ የእንስሳነት መገለጫችን ተደርጎ ይወሰዳል፡፡
‹ሱፐር ኢጎ› የምንለው ክፍል ደግ ሞራልን የሚያበዛና በወላጅ፣ በማህበረሰብና በሃይማኖት ጫና ስር ያለ ነው፡፡ ይሄ ከሁሉም ነገር የሚገደብ ሰብዕናን የሚያመጣ ነው፡፡ እንደ ዶ/ር አበባው ገለፃ ተመራጩ ‹ኢጎ› የሚባለው ነው፡፡
ነገሮችን መተውም እንደ እንስሳ መተግበርም እንደሌለብን የሚያዝን በመሆኑ፡፡ የአንዱ ክፍል በአንድ ሰው ላይ የበላይ መሆን ሌላውን ይጫነውና ነው ተግባሮችን የምንፈፅመው፡፡ የመማገጥ ታሪካቸው ከፍ ያለ ሰዎች በኢዳቸው ጫና ስር የመሆናቸው ማሳያ ሊሆን ይችላል ነው የሚሉት ዶ/ር አበባው፡፡
የጓደኛ ምክር፣ የሃይማኖት ትምህርቶችን መከታተል እንዲሁም ከትዳር አጋር ጋር በመመካከር ወደ ትክክለኛ መስመር ለመምጣት መጣር ያስፈልጋል ነው መልዕክቱ፡፡ ያም ቢሆን በደልን በመርዳትና ግንኙነትን በማሻሻል መኖር እንደሚቻል እምነት አላቸው፡፡ ከመማገጥ በኋላ ችግርና ልዩነቶቻቸውን አጥብበው ምሳሌ የሚሆን ቤተሰብ መፍጠር የቻሉ ሰዎች አሉ፡፡ እዚህ ደረጃ ላይ ለመገኘት ግን ብዙ ደረጃዎችን አልፈው ሊሆን ይችላል፡፡ ከትዳር ውጪ ለመሄድ ምክንያት የነበሩ ቀዳዳዎችን በመድፈን፣ የዘመድ ወዳጅ ተግሳፅ ምናልባትም የስነ ልቦና ባለሙያ ምክር ማግኘት ያስፈልጋል፡፡
በትዳር ውስጥ ያሉ ሁለቱ ሰዎች፣ በስምምነታቸው መሰረትና ተቋሙ በራሱ በሚያስገድደው ሁኔታ ሀብትና ንብረታቸውን በጋራ ያስተዳድራሉ፡፡ እንደ ግንኙነቱ ጥንካሬም የግ የሚባሉ ጉዳዮች እንዳይኖሩ ለማድረግ ይጥራሉ፡፡ ነገር ግን ያለንበት ዘመን የወል የሚባሉ አጠቃቀሞች ላይ ፈተና ጋርጧል፡፡ ባልም ሆነ ሚስት በፈለጉት ሁኔታ በግላቸው እንዲኖሯቸው የሚፈልጓቸውን ነገሮች ያለከልካይና ፈቃጅ ያሟላሉ፡፡ እነዚህ ነገሮች ከሀብትና ቁሳቁሶች ባሻገር አንዱ ወገን በማያውቀው ሁኔታ የተቃራኒም ሆነ የተመሳሳይ ፆታ ጓደኞችን ማፍራት ነው፡፡ በተለይ ማህበራዊ ድረገፆችን መጠቀም የዕለት ተዕለት ተግባር ሲሆን ከትዳር ውጪ መማገጥን ያመጣል፡፡ ለመፍትሄ የሚጨነቁት ባለሙያዎች፣ የትዳርን ምሰሶ ከማጠናከር ጋር የግል የሚባል ንብረት እንዳይጠናከር ማድረጉ ላይ መስራት እንደሚያስፈልግ ነው ምክረ ሐሳባቸው፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.