ትናንትና “ቫላንታይንስ ዴይ (የፍቅረኞች ቀን) ከባሕል ማንነታችን ጋር ምን ያህል ይቃረናል?” በሚል ርእስ ያስነበብኳቹህ ጽሑፍ ነበረ፡፡ በፌስብክ አካውንቴ (በመጽሐፈ ገጽ መዝገቤ) ከአንድ የመጽሐፈ ገጽ ጓደኛየ ለቀረበልኝ ጥያቄና አስተያየት የሰጠሁትን መልስ የተመለከተ ሌላ የመጽሐፈ ገጽ ጓደኛየ “አምሳሉ ከመልስህ ስለ ወሲብ አለመጣጣም ችግርና መፍትሔ ያልነበረኝን ግንዛቤ አግኝቻለሁ፡፡ በጽሑፍ መልክ አዘጋጅተህ ለንባብ ብታበቃውና ሌሎችም ግንዛቤ ቢወስዱበት ጥሩ ነበር፡፡ በተለይም ወሲብ ላልጀመሩት ያለውን ነገር በትክክል እንዲረዱት ያስችላቸዋል፡፡ ሌላውም ቢሆን ትክክለኛውን ነገር መረዳቱ ግንዛቤውን ወደጎንም ወደታችም (ለእኅት ወንድምና ልጅ) ችግሩ ውስጥ ከመግባታቸው በፊት እንዲያውቁትና እንዲጠነቀቁ ለማድረግ ይረዳልና እባክህ?” ሲለኝ የቫላንታይኑን ጽሑፍ አንብበው በመጽሐፈ ገጼ ላይ ጥያቄውን እንደጠየቀኝ የመጽሐፈ ገጽ ጓደኛየ ተመሳሳይ ጥያቄ ያላቸው ሊኖሩ ስለሚችሉ በሚል ሌላ ጽሑፍ ከምጽፍም ለምን እንዳለ በቀጥታ የመጽሐፈ ገጽ ጓደኛየ የጠየቀውን ጥያቄና የሰጠሁትን መልስ አላስነብባቸውም? ብየ እሱኑ ሳይነካካ አስፍሬላቹሀለሁ፦

የመጽሐፈ ገጽ ጓደኛየ ጥያቄዎች የሚከተሉት ነበሩ፦ “ጤና ይስጥልኝ?! በቅድሚያ ለዚህ አስተማሪ ፅሁፍኽ በጣም አመሰግናለሁ! ይሄን ዘመን አመጣሽ በዓል ከተለያዩ ነገሮች ዙሪያ ያየህበት መንገድም ደስ የሚል ነው! ምናልባት ሁለት ነገሮችን እንድታብራራልኝ እፈልጋለሁ፡፡ ፩) ወሲብን በተመለከተ፡ ከላይ እንደገለፅከው ወሲብ በቅድመ ጋብቻ ወቅት በባህላችን አይፈቀድም፡፡ በኔ እምነት ይሄ መቅረት ያለበት አስተሳሰብ ነው፡፡ ምክንያቱም ለአብዛኛው ትዳር በፍቺ መጠናቀቅ ዋነኛ ምክንያቱ በወሲብ አለመጣጣም ስለሆነ ነው፡፡ ለምሳሌ በ2011 በእንግሊዝ ሃገር በተደረገ ጥናት በሃገሪቱ ከተፈፀሙ ፍቺዎች 41% የሚሆነው ምክንያቱ ወሲብ ነበር፡፡ ስለዚህ ከትዳር በፊት ወሲብ ማድረግ በኋላ ለሚፈጠሩ አለመግባባቶች ሁነኛ መፍትሔ ይመስለኛል፡፡ ፪) አበባን በተመለከተ ያነሳኃቸው ነጥቦች ጥሩ ሆነው፡ ነገር ግን ባህላችን ለከንፈር ወዳጆቻችን አበባ መስጠትን ይደግፍ እንደሆነ ብታሳየን ደስ ይለኛል፡፡ ማለቴ አበባን ለመስቀል እና ለመሳሰሉት ሀይማኖታዊ በዓላት እንደምንጠቀመው ብቻ ነው እንጅ ለፍቅረኞች እንደስጦታ እንደሚሰጥ ፅሁፉ የጠቀሰ ስላልመሰለኝ ነው ሰላም!

የእኔ መልስ፦

@————– አየ አንተ ወንድሜ! ትዳር ላይ የወሲብ አለመጣጣም ከባድ ችግር ሆኖ ትዳር እስከማፍረስ የሚደርሰው ለምን ይመስልሀል? ሴቷም ሆነ ወንዱ ከእሷ ወይም ከሱ በፊት የወሲብ ተሞክሮ የያዙ መሆናቸው እኮነው፡፡ እሷና እሱ ከእሷና ከሱ በፊት ሌሎች ሰዎችን የማያውቁ ቢሆን ኖሮ ይሄ ችግር የሚፈጠር ይመስልሀል? በፍጹም አይፈጠርም! እሷና እሱ ሌሎችን ማወቃቸው እኮ ነው ማወዳደር ውስጥ እንዲገቡ የሚያደርጋቸውና እሷ እሱን እሱም እሷን ከሌሎቹ በወሲብ ከሚያውቋቸው ሰዎች ጋር እያነጻፀሩ እንዲናናቁ የሚያደርጋቸው፡፡ እሷና እሱ ሌላ የማያውቁ ከሆነ ግን እሷ ለሱ አንደኛ ናት እሱም ለእሷ አንደኛ ነው፡፡ የማታውቀው ሀገር አይናፍቅህማ! ሌላ የሚናፍቅህ የምታውቀው ጣዕም የለማ! አበባን ለፍቅረኛ ስለማበርከት በባሕላችን እንዴት ይታያል? ላልከው በቅድሚያ ጽሑፉ ላይ እንደገለጽኩት ባሕላችን ፍቅረኛነትን የሚያስተናግደው በምዕራባውያኑ ዓይነት እንዳልሆነ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ባሕላችን ያን ዓይነት ግንኙነት “መባለግ ነው!” ነው የሚለው፡፡ የከንፈር ወዳጅነት ወሲብ የሌለበት ወደ ትዳር የሚወስድ የመዋደጃ መንገድ እንጅ እንደ ምዕራባውያኑ በፍቅር ስም የወሲብ አምሮትን መወጫ አማራጭ አይደለም፡፡ ይሄን ካልኩ በኋላ ባሕላችን የአበባ ስጦታ ለከበረና ለተወደደ የሚበረከት ስጦታ መሆኑን ካስቀመጠ በቂውና አስፈላጊው ነገር እሱ ነው፡፡ ወደድኳት አከበርኳት የምትላት ፍቅረኛ ካለችህ ለወደድካትና ላከበርካት አበባን የማበርከቱን ውሳኔ ላንተ ትቷልና፡፡ በአዲስ ዓመት ለወላጅ፣ ለዘመድ ወዳጅ አበባን እንድናበረክት የደነገገ ባሕል ይልቁንም ለፍቅረኛ ወይም ለትዳር አጋር እንዴት አያዝ ወይም አይፈቅድ ጃል?
የመጽሐፈገጽ ጓደኛየ ተከታይ ጥያቄ፦ “በጣም አመሰግናለሁ! አሁንም ግን ስለ ቅድመ ትዳር ወሲብ አስፈላጊነት የሰጠኸኝ ምላሽ አላረካኝም፡፡ አንተ ካልኸው በተለየ መልኩ፡ በዚህ ዘመን ከባሏ ጋር ስለምታደርገው ወሲብ ለሴት ጓደኛዋ የማታወራ ሴት አለችን? ስንት ዓይነት ወሲብ ነክ ፊልሞችስ አስተዋጽኦ አይኖራቸውም? ስለዚህ በዚህ ዘመን ስለ ወሲብ ለማወቅ ግዴታ ከሌላ ወንድ ጋር ማድረግ አይጠበቅባትም፡፡ ሲጀመርስ በወሲብ አለመጣጣም ማለት necessarily relative ነው ብለህ ታስባለህ? ማለቴ ከባላቸው ጋር ብቻ ቢያደርጉም እኮ ወሲብ የሚሰጠው ደስታ ሲበዛ subjective ነው፡ ለባልና ለሚስት የሚኖረው ይለያያል፡፡ ስለዚህ በዚህም ምክንያት አለመግባባት ይመጣል ባይ ነኝ፡፡ ለጉራማይሌ የቃል አጠቃቀሜ ይቅርታ ይደረግልኝ!”

የእኔ መልስ፦

እንዴት ይሻላል ——-? ነገሩ እኮ ትንሽ በግልጽ ለማውራት ስለሚከብድ ነው፡፡ ግድ የለም እንዲህ አድርገን እንየው፡፡ ይቺ ከባሏ ጋር እንዴት እንደሆኑ (እንደተመቻት) ለጓደኛዋ ሄዳ የምታወራዋ ሴት ባሏን ጓደኛዋም ብታገኘው ውጤቱ ካወራችላት ተቃራኒ ሊሆንም እንደሚችል ይታወቃል:: ለምን ይመስልሀል? አንተ እንዳልከው ወሲባዊ እርካታ እንደየሰው ተፈጥሮ ግላዊ ስለሆነ ነው፡፡ ለአንደኛዋ በጣም የተመቻት ለሌላኛዋ የማይመቻት ምክንያት ይሄ ነው፡፡ እንግዲህ ወሲባዊ እርካታ ግላዊ ከሆነና ለጓደኛዋ የተመቻት ለእሷ ይመቻታል ማለት እንዳልሆነ ከታወቀ ችግሩ ከራሷም ሊሆን እንደሚችል ማሰብ ይኖርባታል እንጅ የእሷው የማይረባ እንደሆነና ሌላ መቀየር እንዳለባት እንዴት ልታስብ ይገባል? ይሄንን የምልህ ግን ይሄኛው ወንድ ወሲብን በተገቢው ብቃት ይፈጽማል ብለን እናስብና ነው፡፡ ይሄንን የምልህ ለምን መሰለህ እኛ በባሕላችን ስለ ወሲብ ነክ ነገር በግልጽ መወያየት አንወድም፡፡ በዚህ ምክንያት ከእኛ ወንዶች የሚበዛው ወሲብ ሲባል እሱ እስኪረካ ያለው ነገር ይመስለዋል እንጅ ሚስቱም የራሷ ስሜትና የእርካታ ፍላጎት እንዳላት ያንንም ማሟላት እንዳለበት ያለማወቅ ችግር በሰፊው አለ፡፡ እያልኩህ ያለሁት ከእሷ አና ከእሱ ውጭ ሌላ የማያውቁ ጥንዶች ወሲብን የተመለከተ ችግር ከገጠማቸው ችግሩ የሚሆነው ወሲብን በብቃት ያለመፈጸም ነው እንጅ ያለመጣጣም አይሆንም፡፡ ምክንያቱም እርካታ ሌላው ቀርቶ በመነካካት በማሻሸት ወይም በግለ ወሲብም ሊመጣ የሚችል ነገር ነውና፡፡ ባሏ ወሲብን በብቃት እየፈጸመ እርካታ ማግኘት ወይም መጣጣም ከጠፋ ችግሩ ሥነልቡናዊ እንጅ አካላዊ አይደለም፡፡ በዚህ ላይ የትኛውም ወንድ ቢሆን እርካታን የማይሰጣቸው ወይም የማይጥማቸው ሴቶች (Dormant) እንዳሉ ልብ በል፡፡ አንድ ነገር ግን በእርግጠኝነት ልነግርህ እችላለሁ እያንዳንዷ ሴትና እያንዳንዱ ወንድ ለእያንዳንዱ ወንድና ለእያንዳንዷ ሴት የሚሰጠው ጠዓም የተለያየ ነው፡፡ በተፈጥሮ ውስጥ አንድ ዓይነት የሚባል ነገር የለም፡፡

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
amsalugkidan@gmail.com

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here