ውጥረት በተሞላ ህይወት መነሻነት ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ በመላው ዓለም በተለምዶው በርካቶች ለእንቅልፍ እጦት መፍትሄ ሲሉ የእንቅልፍ ክኒኖችን ያለ ባለሞያ ምክር ይወስዳሉ፡፡ የዚህ ክኒን አደገኛነት ያሳሰባቸው ኤክስፐርቶች በርካታ ጥናቶችን አድርገው ማስጠንቀቂያዎችን መስጠት ከጀመሩ ሰንብተዋል፡፡ በእነዚህ የእንቅልፍ ክኒኖች የጤና አደጋ ላይ የመፍትሄ አቅጣጫን ያካተተ ሰፊ ዳሰሳን አድርገንልዎታል፡፡

የክኒኖቹ ባህሪ

ብዙ የዓለማችን ሰዎች የችግሩ ሰለባ ቢሆኑም ባለፈው ሰሞን ጮሆ የተሰማው የሆሊውድ ኮከቦች ታሪክ ብዙዎችን አስገርሟል፡፡ የሆሊውድና የእንቅልፍ ክኒኖች እጅግ አስገራሚ ቁርኝት የሜንስ ሄልዝ ድህረ ገፅ ፀሐፊ ጂም ቶርንተን ሲተነተን፣ ታይገር ውድስና ሊንዚ ሎሃንን ያነሳል፡፡ በሚስቱ ላይ ቆነጃጅትን ደርቦ ባልዣል በሚል በቅሌት ስሙ ገንኖ የነበረው የጎልፍ ኮከቡ ታይገር ውድስ ‹‹አምብየን›› የተባለውን የእንቅልፍ ክኒን ይወስድ እንደነበር ተዘግቧል፡፡ አስገራሚው ጉዳይ ግን ውድስ የመድሃኒቱ አምራቾች ያልተገነዘቡትን ጥቅም ከክኒኑ አግኝቻለሁ ማለቱ ነው፡፡ ‹‹ክኒኑ የወሲብ ብርታቴንና ፍላጎቴን በእጅጉ አሳድጎልኛል›› ብሏል ታይገር ውድስ፡፡

ከሱስ ማገገሚያ በመመላለስ የምትታወቀው ተዋናይ ሊንዚ ሎሃን በበኩሏ ‹‹በዕፅ መድሃኒቶች ሱስ የተለከፍኩት ለመጀመሪያ ጊዜ ስወስዳቸው በነበሩ የእንቅልፍ ክኒኖች መነሻነት ነው›› ማለቷም መነጋገሪያ ሆኖ ነበር፡፡ ከጥናቶቹም ከታዋቂዎቹ ሰዎች ንግግሮችም ሆነ ከአጠቃላይ ህዝቡ የእንቅልፍ ክኒኖች ጉዳይ አሳስቦናል ጥያቄ አላፈናፍን ያለው የአሜሪካ የመድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ነገሩን ከምር ወስዶ እርምጃዎችን ማጠናከር ከጀመረ ሰንብቷል፡፡ ባለስልጣኑ በተለይ አሳስቦኛል ያለው ‹‹አምቢያን›› የተሰኘው ክኒን ሰዎች ሌሊት በእንቅልፍ ልባቸው ተነስተው እንዲበሉ፤ መኪና እንዲያሽከርክሩ… የተለያዩ ለአደጋ የሚጋብዙ ተግባራትን እንዲከውኑ እንዲሁም ወሲብ እንዲፈፅሙ ጭምር አድርጓል መባል ነበር፡፡ እነዚህ ሰዎች ጠዋት ሲነቁ አንዱንም ነገር አያስታውሱም፡፡

ኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ያነጋገራቸው የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ ባለሞያ ‹‹እነዚህ የእንቅልፍ ክኒኖች እንቅልፍ መስጠት ብቻ ሳይሆን የባህሪ ቅየራ ድረስ የሚዘልቅ ጉዳትን ማስከተላቸው ስለታወቀ ቁጥጥሩንም ማስተማሩንም አጥብቀን ይዘናል›› ብለዋል፡፡ የቁጥጥር ባለስልጣኑ ለአስራ አንድ የመድሃኒት አምራቾች በሰጠው ማስጠንቀቂያም አምራቾቹ በመድሃኒቶቹ ማሸጊያዎች ላይ የመድሃኒቶቹ ያለባለሞያ ትዕዛዝ እንዳይሸጡ ትዕዛዝ አስተላልፏል፡፡ ይሁንና አሁንም ድረስ ቀለል ያለ ይዘት አሏቸው የተባሉ የእንቅልፍ ክኒኖች ያለ ትዕዛዝ በፋር ማሲዎች ውስጥ ይሸጣሉ፡፡ ይህ በአሜሪካ የሆነ ነው፡፡

መድሃኒቶች መዋዋስ ልምድ በሆነበት፣ ግንዛቤውም አናሳ በሆነባት እና መረጃዎችም ተጠናቅረው በማይገኙባት በኢትዮጵያ ‹‹ችግሩ የባሰ ሊሆን ይችላል›› የሚሉት ፋርማሲስቱ አቶ መስፍን አየለ ናቸው፡፡ የእኛ ሰው ከባለሞያ ይልቅ ለጎረቤቱ ምክር የበለጠ ጆሮውን ይሰጣል፡፡ ይህ ተባራሪ መረጃን ይዞ ህይወቱን አደጋ ላይ የመጣል አጋጣሚን ይፈጥራል፤ ይላሉ አቶ መስፍን፡፡ በተለያየ መንገድ መድሃኒቶች ያለ ትዕዛዝ የሚሸጡበት የመድሃኒቶች ህጋዊ ያልሆነ አገባብ እንዲሁም የላላው የመድሃኒት ቁጥጥርም ባለሞያውን ያሳስባቸዋል፡፡

ጥናቶቹ ያረጋገጡዋቸው ጠንቆች

‹‹የእንቅልፍ ክኒን ተብለው በሰዎች የሚወሰዱ ክኒኖች መዘዝ ብዙ ነው›› የሚሉት በካናዳው የላቫል ዩኒቨርሲቲ በ12 ሺህ ሰዎች ላይ ለአስራ ሶስት ዓመታት ጥናት የሰሩት ዶ/ር ጀነቪቭ ቤልቪል ናቸው፡፡ በካናዳ ጆርጅ ኦፍ ሳይኪያትሪ ላይ በሰፈረው የጥናት ውጤታቸው ባለሞያዋ እንዳሉት የእንቅልፍ ክኒን ተጠቃሚ ሰዎች ከሌሎች በበለጠ ከዕድሜያቸው ቀድመው የመሞት አጋጣሚያቸው በ36 በመቶ ከፍ ያለ ነው፡፡ ለጭንቀት ወይም ቀለል ላሉ የአዕምሮ ችግሮች የሚሰጡ መድሃኒቶችን ከሐኪም ትዕዛዝ ውጪ ለረጅም ጊዜ መውሰድ ሰዎች ለተለያዩ አደጋዎች የሚሰጡት ምላሽ እና ውሳኔ የዘገየ እንዲሆን ያደርጋል፡፡ ከአደጋ ለመሸሽ ይዘገያሉ፤ በአጉል ቦታዎች በመውደቅ ለአደጋ ይዳረጋሉ፤ በማዕከላዊ የነርቭ ስርዓት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ በማሳደር ራስን ወደ ማጥፋት ስለሚገፋፋም እነዚህ ሰዎች ሞታቸው የተፋጠነ ሊሆን እንደሚችን ባለሞያዋ ያብራራሉ፡፡

‹‹ዘ ዳርክ ሳይድ ኦፍ ስሊፕንግ ፒልስ›› በተሰኘ መፅሔታቸው ስለ እንቅልፍ ክኒን ጉዳቶች የሚያወሱት ዶ/ር ዳንኤል ክኒፕክ በበኩላቸው ክኒኖቹ የመተንፈሻ መስመር ጡንቻዎች ዘና ከማድረግ አልፈው እንዲዝሉ በማድረግ በእንቅልፍ ወቅት የመታፈን እና ትንታን በማምጣት በአልጋ ላይ እስከመሞት የሚዘልቅ አደጋን እንደሚኖራቸው ያወሳሉ፡፡ በተለይ እንደ ልብ ህመምና አስም ያለባቸው ሰዎች ያለ ሐኪም ትዕዛዝ የሚወስዱት የእንቅልፍ ክኒን መሰናበቻቸው ሊሆን ይችላል፤ ይላሉ ዶክተሩ፡፡ ዶ/ር ዳንኤል ክኒኖቹ የልብ በሽታ፣ ካንሰርንና ሌሎች የመተንፈሻ አካላት ህመም ስለማስከተላቸውም የሚጠቁሙ አንዳንድ ጥናቶች መኖራቸውን በመጽሐፋቸው ያነሳሳሉ፡፡ ከ20087 (እ.ኤ.አ) ጀምሮ ከስካንዶኖቪያን አገራት እስከ ጃፓን ከተሰሩ ጥናቶች መካከል በተለይ ሶስቱ የእንቅልፍ ክኒኖች ከካንሰር ጋር ጥብቅ ቁርኝት እንዳላቸው ማረጋገጣቸውን ዶ/ር ዳንኤል ፅፈዋል፡፡ የአሜሪካን ካንሰር ሶሳይቲ በሰራው ጥናት ደግሞ የእንቅልፍ ክኒን የሚወስዱ ሰዎች በአማካይ በተለያዩ ምክንያቶች ሲታመሙ ሞታቸው የመፋጠኑ አጋጣሚ በ55 በመቶው ከፍ ያለ መሆኑን አሳይቷል፡፡

አብዛኞቹ የእንቅልፍ ክኒኖች መፍዘዝ፣ የምግብ ፍላጎት ማጣት፣ የሆድ ድርቀት፣ ከባድ ራስ ምታት፣ ቅዠት እና የመሳሰሉት በማግስቱ የሚታዩ የጎንዮሽ ጉዳቶች ሆነው ይታያሉ፡፡ ነገር ግን ያለ እንቅልፍ ክኒን መተኛት ፈተና ሲሆንና ክኒኑም ወደ ሱስነት ሲያድግ ጉዳቶቹ ይገዝፋሉ፤ ክፋቱንም መቆጣጠር ያስቸግራል፡፡

የእንቅልፍ ክኒን የሚባል መድሃኒት አለ?

ለዚህ ጥያቄ ፋርማሲስቱ ራሳቸውን በአሉታ በመነቅነቅ መልሳቸውን ይጀምራሉ፡፡ እኒህ ሴዴቲቭ ወይም ደንዘዝ የሚያደርጉ መድሃኒቶች በቀደመው ዘመን ለከባድ የቀዶ ጥገና ለሚሰራላቸው ሰዎች ይሰጡ ነበር፡፡ ለተለያዩ የአዕምሮ ችግሮች ይሰጡ የነበሩትና እንቅልፍ የሚያስወስዱ መድሃኒቶችም የተለያዩ ጡንቻዎችንና የነርቭ ህዋሳትን ፈታ በማድረግ ከጭንቀት እና ከአዕምሮ መረበሽ እንዲያሽሉ ታስበው ይሰጡም ነበር፡፡ ከጊዜ በኋላም ለቀላል እንቅልፍ ማጣት ተብለው በሳምንት አንድ ወይም ሁለት ቀን በጥቂት ምጣኔ መስጠት ጀመሩ፡፡ አሁን ላይ የእንቅልፍ ክኒን የቢሊዮን ዶላሮች ኢንዱስትሪ ሆነዋል፡፡ ብዙ የዓለማችን ሰዎች ያለክኒን ይተኙም፡፡ የጤና ቀውሶቹን አስጨናቂ ሆነዋል፡፡

በገበያ ላይ ያሉት ለእንቅልፍ ተብለው የሚሰጡ መድሃኒቶች ሶስት ዋና ምድቦች ውስጥ ይቀመጣሉ፡፡ የመጀመሪያዎቹ ቤንዞዳያዜፒንስ የሚባሉት ሲሆኑ እንደ ቫልየም አይነቶቹ ክኒኖች በዚህ ስር ይጠቃለላሉ፡፡ በሌላው ስማቸው ደያዜፓም የሚባሉት እነዚህ መድሃኒቶች በኢትዮጵያ በብዙ ሰዎች አለአግባብ ጥቅም ላይ እየዋሉ ያሉ መሆናቸውን ያነጋገርናቸው ባለሞያዎች ይናገራሉ፡፡ ዋና ስራቸው ጭንቀትን ማስታገስ ሲሆን ሱስ የማስያዝ አቅማቸውም ከፍተኛ ነው፡፡ ያለ ሀኪም ትዕዛዝ ሊወሰዱ አይገባም፡፡ ከክኒኑ ሱስ መላቀቅም ሲጋራ ማጤስን ከማቆም የበለጠ ሊከብድ ይችላል፡፡

ሁለተኛው መደብ ውስጥ ያሉት እና ባርቢቱሬትስ የሚሰኙት በአብዛኛው በህክምናው ለቀዶ ጥገና ወቅት እና ሌሎች ህክምና ስራዎች ለማደንዘዣነት የሚውሉ ናቸው፡፡ በሶስተኛው ምድብ ውስጥ የሚቀመጡ እንደ ሉኔስታ አይነቶቹ መድሃኒቶች ከቀደሙት በፈጠነ መልክ እንቅልፍ ውስጥ የሚከትቱ ናቸው፡፡ ለአስም የሚታዘዙ አንቲሂስታሚንስ እንዲሁ መጠነኛ እንቅልፍ የማስያዝ ባህሪ ያላቸው ቅመሞች በውስጣቸው ይገኛል፡፡

በአንፃራዊነት የተሻለ የሚባለውና በቀጥታ የእንቅልፍ ክኒን ውስጥ የማይመደበው ሜላቶኒን በባለሞያዎች በበጎ ይነሳል፡፡ ሜላቶኒን በተፈጥሮ በሰውነት ውስጥ የሚሰራ ሆርሞን ሲሆን ሰውነት ቀንና ሌሊት መፈራረቂያ ሪትምን ለይቶ እንቅልፍን እንዲመራ ያግዛል፡፡ ሲጨልም እንድናቀላፋ ብርሃን ሲሆን እንድንነቃ ያደርጋል፡፡ ዕድሜያቸው የገፉ ሰዎች ዘንድ ቅመሙ እያነሰ ስለሚሄድ እንቅልፋቸው ይዛባል፡፡ ቀን እየተኙ ሌሊት አፍጥጦ ማደር እጣቸው ሊሆን ይችላል፡፡ ሜላቶኒን በክኒን ሲወሰድ ይህን ያስተካክላል፡፡

አልኮል መጠጥ+ጫት+እንቅልፍ+ ክኒን= ሞት

በተለይ በኢትዮጵያ ጫት ቃሚዎች በእንቅልፍ እጦት ችግር ከሚሰቃዩ ሰዎች መካከል በቀዳሚነት ይነሳሉ፡፡ ጫት በተፈጥሮው የማነቃቃት ጠባይ ስላለው ያንን የተነቃቃ አዕምሮ ማታ ላይ እርፍ ብሎ ማስተኛት በእጅጉ ያስቸግራል፡፡ የአባት ስም ይቅርባችሁ ብሎ የዚህ ችግር ሰለባ መሆኑን የነገረን እና በአንድ የግል ተቋም አይቲ ኤክስፐርትነት የሚሰራው ወጣት ሰለሞን ያለጨብሲ አልኮል መጠጥ ምርቃናውን መስበር እና መደንዘዝ ፈጽሞ እንዳይችል እና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ መጠጡ ጭራሽ አልሰማ እያለው በእንቅልፍ እጦት ላይ መሆኑን ይገልጣል፡፡ በጨብሲ መደንዘዝና እንቅልፍ መተኛት የማይችሉ ሰዎች ወደ እንቅልፍ ክኒን መዞራቸው የተለመደ ነው፡፡ ባለሞያው አቶ መስፍን ይህን ድርጊት በአንገት ላይ ሸምቀቆ አስገብቶ መጫወት ነው ይሉታል፡፡ አልኮል መጠጥ በተፈጥሮው ጡንቻዎችን የማዛል እና በእጅጉ የማዝናናት ጠባይ አለው፡፡ የእንቅልፍ ክኒኖች ደግሞ ይህን ተግባር ጠንከር አድርጎ መከወን ነው ስራቸው፡፡ በመሆኑም በአልኮል መጠጥ ላይ የእንቅልፍ ክኒን ሲታከልበት የሰውነትን ስራዎች የሚከውኑት የልብ፣ ሳንባ እና ሌሎች ጡንቻዎች ከመጠን ባለፈ ሁኔታ ይዝሉና መታጠፍ መዘርጋት መኮማተርና መፍታታት ያቆማሉ፡፡ ልብ ቀስ እያለች የመምታት ጉልበት ታጣለች፣ የመተንፈሻ መስመር ጡንቻዎችም አየር ለማስገባትና ለማስወጣት ፈተና ይሆንባቸዋል፡፡ ልብ መምታት ታቆማለች፣ መተንፈስ ያቆማል፡፡ ከዚህ የተሻለ የሞት ትርጉም የለም፡፡ ‹‹አልኮልና እንቅልፍ ክኒን ፈፅሞ ሊቀላቀሉ አይገባም፤ ውጤታቸው ሞት ነው…›› ይላሉ ዶ/ር ዳንኤል፡፡ ከቤት እስከ ክሊኒክ የመፍትሄ አቅጣጫዎች ለተለያዩ የአዕምሮ ችግሮች እንዲሁም እንደ አስም ላሉ የጤና ችግሮች ሲሉ እንቅልፍን የሚያበረታቱ መድሃኒቶችን ከሚወስዱ ሰዎች በስተቀር ለእንቅልፍ ብቻ መድሃኒት የሚጠቀሙ ሰዎች መነሻቸው እንቅልፍ ማጣት እንደመሆኑ የተለያዩ የመፍትሄ ሃሳቦችና እርምጃዎች ሲከተሉ ስር ነቀል መፍትሄ ላይ ማተኮርን ባለሞያዎቹ ያሳስባሉ፡፡

የእንቅልፍ እጦትን በክኒን ማስታመም የመጨረሻና የማይመከረው የመፍትሄ ሃሳብ ነው፤ ይላሉ ዶ/ር ዳንኤል፡፡ ባለሞያው የመፍትሄ አቅጣጫዎቹን በሶስት ከፍለው ይመለከታሉ፡፡ የመጀመሪያው የእንቅልፍ ችግር ላለባቸውና ክኒኖችን መጠቀም ላልጀመሩት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የእንቅልፍ ክኒን እያዘወተሩ ላሉትና አደጋውን ላልተገነዘቡት ነው፡፡ በመጨረሻም ደግሞ ወደፊት ችግሩ እንዳይከሰት ለማድረግ የሚያስችሉ የኑሮ ዘዬ ምክሮችን ያስከትላሉ፡፡

በቀን እስከ ስድስት ሰዓት ሰላማዊ እንቅልፍ ማግኘት ለሰውነት ቀልጣፋ አሰራር ወሳኝ ነው፡፡ ሰላማዊ እንቅልፍ ወሳኝ የጤናማ ህይወት ግብአት እንደመሆኑ፣ ሲከሰትም የሚፈጠረው ችግር በዕለት ተዕለት ስራ ላይ እና ጤና ላይ የሚያስከትለው ጫና ይከብዳል፡፡ ሰዎች ለጤና በእጅጉ አደጋ እንደሚፈጥር የሚታወቀውን የእንቅልፍ ክኒን ወደ መውሰድ የሚያዘነብሉትም ይህን ጫና ለማርገብ ነው፡፡ ወቅታዊ የእንቅልፍ ችግርያለባቸው ሰዎች ከእንቅልፍ ክኒን በፊት ሊወስዷቸው የሚገቡ እርምጃዎችን ዶ/ር ዳንኤል ሲዘረዝሩ ቀዳሚው ነገር የእንቅልፍ እጦቱ መንስኤ ምን እንደሆነ ለይቶ ማወቅ ነው ይላሉ፡፡ ችግሩ ሲባባስ ሐኪም ማማከር የግድ ቢሆንም በመጀመሪያ ደረጃ በራስ ጥረት ሊፈቱ የሚችሉ ችግሮችን ነቅሎ ማጥፋት ነው፡፡

ራስዎ ለእንቅልፍዎ በቤትዎ

– የትኛውም ሰው በየዕለቱ ሊያስጨንቁ የሚችሉ ጉዳዮች ሊገጥሙት ይችላሉ፡፡ ይሁንና እነዚህ ጉዳዮች እንቅልፍን አሳጥተው ጉዳት ላይ እስኪጥሉ መፍቀድ አይገባም፡፡ ሃሳብን ሙሉ በሙሉ ማጥፋት ባይቻልም ባለሞያዎቹ የሚሉት በቀኑ የስራ ክፍለጊዜ ያሳሰበዎትን ጉዳይ ወደ አልጋዎ ከመምጣትዎ በፊት ቢያንስ ጊዜያዊ መፍትሄ በአፋጣኝ መስጠት ልምድን እንዲያዳብሩ ነው፡፡ ‹‹የአልጋ እና የመኝታ ቤት ተግባራት እንቅልፍ እና ወሲብ ብቻ ናቸው›› ይላሉ ዶ/ር ዳንኤል፡፡ በተለይ መኝታ ቤታቸውን ሁለተኛ ቢሮ የሚያስመስሉ እና ሲሰሩ የሚያመሹበት ሰዎች በእንቅልፍ እጦት የመጠቃት እድላቸው ከፍ ማለቱን ጥናቶች አሳይተዋል፡፡ በመሆኑም ቢሮ እና መኝታ ቤትዎን ይለዩ ነው ምክራቸው፡፡

– ለአሁኑ ጤናማ እንቅልፍ የሚተኙ ሰዎችም ይሁኑ አልፎ አልፎ ችግሩ የሚገጥማቸው ነገር ግን ክኒን መውሰድ ያልጀመሩ ሰዎች ደግሞ ቢወስዷቸው የሚመክሩትን እርምጃዎች ባለሞያዎቹ ይነሳሳሉ፡፡

– ሞባይል፤ ፒዲኤ፤ ቲቪ፤ ኮምፒውተር እና መሰል ማሽኖችን ከአልጋዎ በቅርብ ርቀት እንዲኖሩ መፍቀድ የለብዎትም፡፡ – መጠነኛ የእንቅልፍ ችግር ያለብዎት ከሆነ ቀን ላይ አጭር እንቅልፍ መተኛትን ናፕ በፍፁም ሊያስወግዱ ይገባል፡፡ ምክንያቱም ይህ የምሽቱን እንቅልፍ ይሻማና ችግሩን ያባብሳል፡፡

– እንቅልፍ የሚተኙበትና ከመኝታ የሚነሱበት የተወሰነ ሰዓት ቢኖርዎትም የሰውነት ፊዚዮሎጂ ለዚህ ሳይክል እንዲላመድና መዛባትም እንዳይኖር ይረዳዋል፡፡

– የአካል እንቅስቃሴ በሚቻል መጠን ማድረግ የእንቅልፍ ሂደት ዘና አድርገው እያባበሉ ወደ እንቅልፍ የሚወስዱ ሆርሞኖች እንዲመረቱ ስለሚያግዝ መንቀሳቀስ ጥሩ መሆኑን ዶ/ር ዳንኤል ያወሳሉ፡፡

– ምሽት ላይ ከባድ ምግብን በጭራሽ አይውሰዱ፡፡ ምግብን የመፍጨትና የማሰራጨትንያህል ከባድ ስራ በሰውነት ውስጥ እየተካሄደ በቂ እረፍትን የሚሰጥ እንቅልፍ ማግኘት የማይታሰብ ነው፡፡ ምሽን ቀደም ብለው ቀለል ያለ እራት ይውሰዱ፡፡ ይመኑኝ በእንቅልፍዎ ላይ ለውጡን በፍጥነት ያዩታል… የሚለው በኦፕራ ዊንፍሬይ ኔትወርክ የቴሌቪዥን ፕሮግራሙን የሚያቀርበው ዶ/ር ፊል ማክጊል ነው፡፡

የእንቅልፍ እጦቱ የጀርባ ምክንያት ሲኖረው

በቀላል የቤት ውስጥና የኑሮ ዘዬ የማይሻሻል የእንቅልፍ ችግር የሐኪም እርዳታን ይፈልጋል፡፡ ባለሞያዎቹ እንደሚሉት እንቅልፍ እጦት ሌላ የጤና ችግር በሰውነት ውስጥ መኖሩን እየተናገረ ሊሆን ይችላል፡፡ ከፍተኛ ድብታ ዲፕሬሽን፣ የሪህ ህመም፣ አስም እንዲሁም ለተለያዩ የጤና እክሎች የሚወስዱ መድሃኒቶች የጎንዮሽ ጉዳቶች እንዲሁም ሌሎች በርካታ ምክንያቶች የእንቅልፍ እጦቱ መንስኤ ሊሆኑ እንደሚችሉ ዶ/ር ዳንኤል ያስረዳሉ፡፡ ዋናው መነሻ በሐኪም ከተለየ መፍትሄ መስጠቱ አይከብድም ባይ ናቸው፡፡

የእንቅልፍ ክኒን ቀለባቸው ለሆኑ

የእንቅልፍ ክኒኖች በአብዛኞቹ ሱስ የማስያዝ ጠባይ ስላላቸው ድንገት ተነስቶ ክኒኖቹን ማቆም ከፍተኛ ችግርን ይፈጥራል፡፡ የእንቅልፍ ክኒን በተከታታይ መውሰድ ከጀመሩ ከ6 እስከ 15 ቀናት ባለው ጊዜ ከሱሰኝነት ወጥመዱ ይከታል፡፡ ከማንኛውም ሱስ መውጣት ፈተና እንደሆነ ሁሉ የእንቅልፍ ክኒንም ይህ ፈተና አለበት፡፡ ድንገት ክኒኑን የሚያቋርጡ ሰዎች በከፍተኛ ሁኔታ መደንዘዝ፣ አካላቸውን አቀናጅቶ ማዘዝ ያለመቻል እና በዚህም ለተለያዩ አደጋዎች መጋለጥ፣ መንቀጥቀጥና፣ ራስን መሳት የመሳሰሉት መገለጫዎችን ያሳያሉ፡፡ ህይወታቸውም አደጋ ላይ ሊወድቅ ይችላል፡፡ እንዴት ከሱስ መላቀቅ ይቻላል? ለሚለው ጥያቄ መልስ የሚሰጡ ባለሞያዎች ሂደቱ ትንሽ የሚያስቸግር እንደሆነ ያወሳሉ፡፡ ማይንድ መጽሔት ‹‹ስሊፒንግ ፒልስ ከርስ ኦን ኪዩር?›› ሲል ባወጣው ፅሑፍ በጠቆመው የመፍትሄ ሃሳብ የመጀመሪያው እርምጃ በአንድ ጊዜ ለማቋረጥ አለመሞከር እንደሆነ ይጠቀሳል፡፡ የክኒኑን መጠን እየቀነሱ ቀስ እያሉ እያለማመዱ መተውና አማራጭ የእንቅልፍ ማግኛ አማራጮችን እየተኩ መሄድ ይመከራል፡፡ ከተቻለ በሂደቱ የባለሞያ እርዳታ ማካተት የበለጠ ውጤታማ ያደርጋል፡፡ ባለሞያም ከሌለ ቢያንስ የቅርብ ሰው እገዛን ማግኘት ያስፈልጋል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.