‹‹ለጋብቻ ሕይወትዎ ስምረት›› የባህሪ አለመጣጣምና የጋብቻ ግጭቶች

0

በክሪስቶፈር ዌልስ
(የስነ ልቦና ባለሙያ)

በአንድ ወቅት አንድ ‹‹ሚስቴ እጣ ክፍሌ አይደለችም›› ብሎ የሚያስብ ሰው እንዲህ ሲል ሰምቼው ነበር፡፡

‹‹ጋብቻዎች ሁሌም ቢሆን በደስታ የተሞሉ ናቸው፡፡ ችግሩ የሚመጣው አብሮ መኖር ሲጀመር ነው››
ይህ አባባል ትክክል ነው? አይደለም? የሚለውን ነገር ለአንባቢ ልተወውና ሁሉም የጋብቻ ውድቀቶች ወይም አለመስማማቶች የሚከሰቱት ግን በስሜት ባለመጣጣምና በባህሪ ባለመግባባት መሆኑን ግን ላስምርበት፡፡ በሁሉም የትዳር ህይወት ከባልና ከሚስት አንደኛው በባህሪ ባለመጣጣም ሳቢያ ለሚፈጠር ግጭት ምክንያት ይሆናል፡፡ የምናገባው ሰው በፆታ ተቃራኒያችን የሆነውንም፣ ከማናውቀው ቤተሰብ የተወለደና በማናውቀው አስተዳደግ ያደገውን ሰው ነው፡፡ ምንም ያህል በተጋቢዎች መካከል መመሳሰልና መጣጣም ቢኖርም የሆነ የኋላ ታሪክ ላይ ወይም አስተዳደግ ላይ ጥቂትም ቢሆን ልዩነት መኖሩ አይቀርም፡፡ በገቢ፣ በትምህርት፣ በስራና በህይወት ልምድ ልዩነት መኖሩ ግድ ነው፡፡ ተጋቢዎች በሁሉም ነገር ተመሳሳይ ናቸው ማለት ይከብዳል፡፡ ከዚህ በታች የማስነብባችሁ የሁለት ትዳሮችን ታሪኮች ሲሆን በጋብቻ ውስጥ የገጠማቸውን ችግር የሚዳስስ ነው… በዚሁ ያለመጣጣምና አንድ ያለመሆን ችግር ሳቢያ፡፡

አንድ ዕለት የቢሮዬን በር ያንኳኳ ደንበኛዬ ቁጭ ካለ በኋላ የሚከተለውን ነገረኝ፡፡ ይህ ሰው ሚስቴና እኔ ፍፁም ልንጣጣም አልቻልንም ነው የሚለው፡፡ ‹‹ከባለቤቴ ጋር ከተጋባን 12 ዓመታችን ነው፡፡ አንዲት ሴትና አንድ ወንድ ልጆችም አሉን፡፡ ከማውቃቸው ባለትዳሮች ሁሉ በተሻለ ሁኔታ የምንፋቀር ነበርን፡፡ በገንዘብም ረገድ ደህና የሚባል ገቢ ያለንና ጥሪት የቋጠርን ነን፡፡ የጋብቻ ግንኙነታችን ችግር የለበትም፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን በትዳራችን ላይ እንግዳ የሆነ ጉዳይ ብቅ ማለት ጀመረ፡፡ ሁለትና ሶስት ቀን ሳንጣላና ሳንኳረፍ የምናሳለፍው ጊዜ እየጠበበ መጣ፡፡ በተለይ በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናትና በበዓላት ጊዜ እኔ ቤት ውስጥ ስውል ደስ የማይል መንፈስ ተፈጥሮ ነው የሚጠብቀኝ፡፡ በዚያን ጊዜ ወደ ስራዬ ለመሄድ አስብና ነገሮች የበለጠ እንዳይወሳሰቡ በማሰብ እየደበረኝም ቢሆን ቤቴ ተቀምጬ እውላለሁ፡፡ ቤታችን ውስጥ እንግዳ ካለ ወይም ለሆነ ጉዳይ ወጣ ስንል ግን ሰላም እንሆናለን፡፡ ይህ ጉዳይ ከተጋባን ጊዜ ጀምሮ የተፈጠረ ነው፡፡ ነገር ግን ድግግሞሹ ቀስ በቀስ እየጨመረ መጥቷል፡፡ አሁን እንደማስበው እኔ በዚህ ጉዳይ ላይ ምርር ብሎኛል፡፡ ጤናዬንና የስራ ተነሳሽነቴን እየጎዳው ነው፡፡ የባሰ ነገር እንዳይመጣብኝ እየሰጋሁ ነው፡፡ እኔ በበኩሌ እሷን የሚያስከፋትን ነገር ላለማድረግ እጠነቃቀለሁ፡፡ የሚያስቆጣት ነገር አላደርግም፡፡ ነገር ግን ይህ ጥረቴ በኔ እንጂ በርሷ በኩል እውቅና አላገኘም፡፡

በርግጥ ቶሎ የሚከፋኝ ሰው መሆኔን አውቃለሁ፡፡ ትዕግስቴም ሙሉ አይደለም፡፡ ይህ ግን ብዙ አይቆይብኝም ምልስ ነኝ፡፡ ድርቅ አልልም፡፡ በቶሎ ፀባዬን አስተካክላለሁ፡፡ ራስ ወዳድም አይደለሁም፡፡ የባለቤቴን ባህሪ መናገር ልክ መስሎ ባይሰማኝም ለእርስዋ ግን መንገር አለብኝ፡፡ እጅግ እጅግ ቶሎ የሚከፋትና የምትበሳጭ ሴት ናት፡፡ ትዕግስት የሚባል ነገር የላትም፡፡ ቁጡ ናት፡፡ ራሷ የፈለገችውን ነገር ብቻ የምትጠብቅ ሴት ናት፡፡ ለማንኛውም አስተያየት ስፍራ የላትም፡፡ ልክም ይሁን ስህተት አትቀበለውም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሩህሩህ ልብ ያላት እና አፍቃሪ ሴት ናት፡፡ ጋብቻችን በዚህ ያለመጣጣም የተነሳ አሰልቺ እየሆነ ነው፡፡ ምን ላድርግ?›› ብሎ ጠየቀኝ፡፡
በተመሳሳይም አንዲት ሴት ደንበኛዬ ይህንኑ አይነት ርዕስ ይዛ ለምክር ወደ ቢሮዬ መጥታ ነበር፡፡

‹‹ዶክተር የ20 ዓመት ወጣት ነኝ፡፡ ካገባሁ አንድ ዓመት አልፎኛል፡፡ ባለቤቴ በጣም በስራ የተወጠረ ሰው ነው፡፡ ገንዘብና ስልጣን ሁሉንም ነገር ያሟላል ብሎ ያስባል፡፡ በባህሪያችንም ጭራሽ አንመሳሰልም፡፡ አንድ ቀን ጥሩ የሆነ ህይወት አሳልፈን አናውቅም፡፡ በርግጥ ያገባሁ የሚመስለኝ ከርሱ ጋር አንድ አልጋ ላይ ስንተኛ ብቻ ነው፡፡ ሁሌም ብቸኝነት የሚሰማኝና ራሴን ለማጥፋት የምመኝ ሰው ነኝ፡፡ የመጀመሪያ ልጄን በቅርቡ እወልዳለሁ፡፡ ከባሌ ጋር ለመታረቅ ብቸኛ መንገዴ ይህ ልጅ ብቻ ይሆናል፡፡ አንዳችም ቢሆን የግል ፍላጎታችንና ስሜታችን የማይጣጣም በመሆኑ ጋብቻ ሲኦል ሆኖብኛል፡፡ እባክዎ እርዱኝ›› አለችኝ፡፡

እንግዲህ የነዚህ ሁለት ሰዎች ጥያቄ ተመሳሳይ የሆነው ሁለቱም በጋብቻቸው ደስተኛ ያልሆኑት በመካከላቸው የባህሪ አለመጣጣምና አለመተዋወቅ በመኖሩ ነው፡፡ ጋብቻ የሁለት የተለያዩ ሰዎች አንድነት ነው፡፡ ጋብቻ የሚሰምረው አንዱ የሌላውን ልዩነትና የግል ባህሪ አውቆ ራሱን ከዚያ ጋር ለማጣጣም ጥረት ያደረገ እንደሆነ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የጋብቻ የመጀመሪያዎቹ ጊዜያት ውስጥ ያለመፋቀርና መዋደድ እንዲሁም መስማማት እየቆየ ከሚፈጠረው ባህሪ ጋር አይጣጣምም፡፡ ይለያያል፡፡ ወጣት ተጋቢዎች በዚህ ወቅት ‹‹የኔ ሰው አይደለም… የኔ እጣ ክፍል አይደለችም የሚል ድምዳሜ ላይ ይደርሳሉ፡፡››

ለሁለተኛዋ ደንበኛዬ ለችግሯ መፍትሄ የሚሆነው እሱን ከስራ ማስወጣት ወይም ከስልጣን ማውረድ አይደለም፡፡ በቤት ውስጥ ተቀምጣ ከምታስብ ጊዜዋን ሊይዘው የሚችል ሌላ ነገር በመስራት ጊዜዋን ማጣበብ ይገባታል፡፡ ምናልባት እሷን ለማራቅ ሳይሆን ኑሯቸውን የበለጠ ለማሻሻል ይሆናል ጊዜ እስኪያጥረው የሚሰራው፡፡ ስለዚህ በነገሮች ላይ ከርሱ ጋር መወያየት እና ከርሱ ህይወት ውስጥ የትኛውን በደስታ ተካፍላ መኖር እንደምትችል ለራሷ ጥናት ማድረግ አለባት፡፡

የመጀመሪያው ወጣት ደንበኛዬ ያለበት ችግር በቀላሉ ለመፍታት ይከብዳል፡፡ አንዳንዴ በየዕለቱ የሚፈጠር ግጭት ሰውን ወደ ጤና ችግር ይወስደዋል፡፡ ይህ ደግሞ ለእያንዳንዱ ነገር ትርጉም መስጠትና ለመስማማት መንገድ የማጥበብ ነገርን ይፈጥራል፡፡ በርግጥ ይህ ንጭንጭ ‹‹አፍቅረኝ… አስብልኝ›› ብሎ የመጠየቅ አንዱ መንገድ ነው፡፡ አንዳንዴ ችግራቸውን ለመፍታት የማይፈልጉ፣ መጎዳትና መጉዳትን የሚሹ ሰዎች አሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች በሳይንሱ አጠራር ሳዶ- ማሶሺስቲክ ይባላሉ፡፡ የሚመሩት ጋብቻም በኃይልና በቁጣ የተሞላ፣ ፀብ የማይጠፋው እንዲሆን ይፈልጋሉ፡፡

አንድ የማውቃት ሴት ባሏን ቤት ውስጥ የምታስተናግድበት መንገድ በጣም ፊት የመንሳትና የቁጣ ነገር የተቀላቀለበት በመሆኑ ጋብቻዋ ፈርሷል፡፡ በተለይ በቤት ውስጥ ስራ እንዲያግዛት የምትጠይቅበት መንገድ ጠባቂነት የተሞላበት ትዕዛዝ ስለሆነ ጋብቻዋን ንዶታል፡፡ በርግጥ በቤት ውስጥ የሚደረግ ስራና መተጋገዝ ለጋብቻና ለፍቅር ጥሩ ነገር ይፈጥራል፡፡ ትዕዛዝ ሲበዛ ግን የሚያመጣው ችግር ጥላቻን፣ ጭንቀትንና ከዚህ ጋብቻ የምወጣበት መንገድ… ብሎ መፈለግን ይፈጥራል፡፡ በየጊዜው የሚደረግ ትዕዛዝና ቁጥጥር ባልን ወይም ሚስትን አርቴፊሻል ባህሪ እንዲፈጥሩና ከጋብቻው ራሳቸውን በስሜት እንዲያርቁ ያደርጋቸዋል፡፡ አንድን ሰው በጣም ለመቆጣጠር መሞከር ትርፉ ያ ሰው የሚያመልጥበት ቀዳዳ እንዲፈለግ ማድረግ ነው፡፡

ሌላው ጋብቻን የሚያውከው ባልና ሚስት በተለያየ ሁኔታ የሚያድጉበትና የሚለወጡበት የተለያየ ደረጃና አቅጣጫ ነው፡፡ የአንድ ሰው ዕድገት ጤናማ ከሆነ ሁለቱም ተጋቢዎች ተፈላጊ የሆነውን መልዕክት በዕድገታቸው ውስጥ ይቀበላሉ፡፡ በስኬቶቻቸውም ይደሰታሉ፡፡ በለውጣቸው ይኮራሉ፡፡ በዕድገትና በስኬት ውስጥ አለመጣጣም መፍጠር ከባልና ከሚስት አንዳቸው ጋብቻቸውን ወደ ማይረባ ግዑዝ ነገር የሚለውጥ መንገድ ይከፍታሉ፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.