‹‹ዓይኗ ጎላ ያለ ጥርሰ በረዶ እና አፍንጫ ሰልካካ፣ ወገቧ የንብ አውራ የመሰለች›› እየተባለች በድምፃዊያኖቻችን የምትሞገሰዋ፤ በተለይ በአብዛኛው የሃገራችን ክፍል የውበት ምሳሌ ተደርጋ ስትወሰድ ነበር፤ ትወሰዳለችም፡፡

በተለይ ቀደም ባለው ጊዜያት፤ ሴት ልጅ ወደማጀት በምትባልበት በዚያን ዘመን፤ የሴት ልጅ የክብር ቦታ ትዳር ብቻ
እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡ ታዲያ ለቤተሰቦቿ የኩራት ተምሳሌት፤ ለአባቷ ክብር ለቤተሰቦቿ ኩራት
የምትሆን ሴት፤ ብረት መዝጊያ የሚሆን የትዳር አጋር የምታገኘው በውበቷ የተደነቀችዋ ናት ተብሎም ስለሚታሰብ፤
የተለየ ክብር እና እንክብካቤ ይደረግላት ነበር፡፡
ታዲያ በዚያን ጊዜም ቢሆን ለውጫዊ ውበት ብቻ ሳይሆን ለውስጣዊውም ውበት አባቶቻችን ይጠነቀቁ እንደነበር
እንሰማለን፡፡ አንብበናልም፡፡ የሃዲስ አለማየሁ ፍቅር እስከመቃብር ገፀ ባህሪ ሰብለ ወንጌልን ለአብነት ልንጠቅስ
እንችላለን፡፡
የሰብለ ወንጌል አስተዳደግ ራሱን የቻለ ግድፈት እንዳለ ሆኖ ነገር ግን በዛን ወቅት የነበረው ማህበረሰብ ሴት
ልጅ ውበቷ ብቻ ሳይሆን ምግባሯ እንዳያሳፍረው- በወቅቱ በነበረው ማህበረሰብ ዘንድ የተወደደች እና የተከበረች
እንድትሆን ምን ያህል ጥንቃቄ ያደርግ እንደነበር ማሳያ ነው፡፡
እንደ እኔ እይታ የዘመኑ ግድፈት የተለየ ክብር እና እንክብካቤ ተደርጎላቸው መልካም ኑሮ እንዲኖሩ ዝግጅት
የሚደረግላቸው ውጫዊ ውበት ያላቸው ላይ መሆኑ ነው፡፡
ዛሬም ላይ ቢሆን አሁን በእኛ ዘመን እንግዳ ተቀባይ፣ ፀሐፊ እና መስተንግዶ ላይ የሚሰሩ ሴቶችን እንኳን
ብንመለከት ለስራው ብቁ ናቸው ተብለው እንደ ቅድሚያ መስፈርት የሚያዝላቸው እንዲሁ ውጫዊ ውበታቸው ነው፡፡
እንዲህ ማድረጋቸው ስህተት ባይሆንም፤ በእርግጥ ውጫዊ ውበት ወይም በመግቢያ ላይ የጠቀስኩትን ዘመኑ ወይም
ማህበረሰቡ የውበት መገለጫ ብሎ ያስቀመጡት ውበት ብቻ ነው እንዴ ውበት? ውጫዊ ውበታቸው እምብዛም የሆኑትስ ውብ
ሊባሉ አይገባ ይሆን?
‹‹አምላክ ሲሰራት የዋለ›› ተብሎ የሚዘፈንላት ሆና ባህሪዋ አስደሳች ካልሆነ በተለይ በዚህ ዘመን፤ ደስተኛ እና
አሸናፊ ሆና ምለቅ ከባድ ይሆንባታል፡፡ ነገር ግን የውጫዊ ውበቷ ባያዘፍንላትም፤ ፈገግታዋ በራስ መተማመኗ/ለራሷ
በምትሰጠው ክብር እና በአለባበስ ምርጫዋ ውብ ናት የተባለች ደግሞ ብዙ ናት፡፡ ደስተኛ ብቻም ሳትን አሸናፊ ሆና
የታየች ለምሳሌ የምትጠቀስም በርካታ ናት፡፡
ወጣትነት ውበት ነው እንደሚባለው በተለያየ ማህበረሰብ እና ልማድ ‹‹የውበት መገለጫ›› ተብሎ የተቀመጠውን
ባታሟላም፣ በወጣትነት ውበቷ አማላይ ብቻ ሳይሆን ደስተኛም ሆና እንድትዘልቅ ግን ሁልጊዜ ራሷን መጠበቅ ማስታወስ
የማያሻው ሃቅ ነው፡፡
አንድ ቀን ድንገት በመስታወት ፊት ቆሞ የተጨማደደውን እና የደረቀውን ፊት ያስተዋለ ሰው መደንገጡ ይጠበቃል፡፡
ለምሳሌ ሴቶች በውበታቸው የሚመኩበት ጊዜ ማለፉን ተፈላጊነቱም ማብቃቱ ሊሰማቸው ይችል ይሆን? ወንዶችም
ይተማመኑበት የነበረውን ዓይናቸው ለስላሳ ቆቸው ወይም በጡንቻ የተገነባው ሰውነታቸው ዛሬ ከእርሱ ጋር አለመሆኑን
አስበው በራስ መተማመኑን ሊያጡት ይችሉ ይሆናል፡፡ በአብዛኛው ማህበረሰብ ውበት በአንድ የዕድሜ እርከን ላይ
የተገደበ ስለመሆኑ እምነት ተወስዷል፡፡ እናም አንድ የዕድሜ ክልልን ያለፈ ሰው ስለውበት ቢያስብ አያምርበትም
ተብሎም ታምኗል፡፡ ነገር ግን ውበት የወጣቱ ብቻ ነው?

ዕድሜን አለመፍራት /መጋፈጥ/

‹‹ወጣትነት ብቻ ውበት ነው›› የሚባለውን አባባል ብዙዎ ይስማሙበታል፡፡ እውነት ነው፡፡ በወጣትነት ዕድሜ
በተለይ በአፍላነት ወቅት ያለው ለጋ ሰውነት ያምራል፡፡ ‹‹ውብ›› ለመባል የሚያበቃ ተክለሰውነትን በፈጣሪ
ያልታደሉት ጭምር በለጋ ዕድሜያቸው ማማራቸው ማሳሳታቸው እሙን ነው፡፡
ነገር ግን ዕድሜ ሲጨምር ይህ ውበት እንደነበረ አይቆይም፡፡ ለዚህም ነው ከተወሰነ ዕድሜ ክልል በኋላ የተለየ
እንክብካቤ ለሰውነት ሊደረግለት ይገባል እየተባለ የሚመከረው፡፡ እውነታውን ተቀብሎ ለሰውነት የሚገባውን
እንክብካቤ ከማድረግ ይልቅ ይበልጥ በጉዳዩ ላይ መብሰልሰል ይበልጥ ውበት እንዲቀንስ ያደርጋል፡፡ የዕድሜ ባለፀጋ
የሆኑ ከፊታቸው ፈገግታ የማይለይ ሰዎች ይበልጥ ውብ ሆነው የመታየት ዕድላቸው ሰፊ ነው፡፡ ምክንያቱም ውበትን
ከሚያጎሉ ጉዳዮ ዋነኛው ደስተኝነት ነውና፡፡ ስለዚህ ዋናው ነገር በየትኛውም ዕድሜ እንዴት ው መሆን ይቻላል
የሚለውን መለየት ነው፡፡

ቆዳ እና የዕድሜ ተፅዕኖ

ቆዳ ዕድሜ እየገፋ ሲሄድ በተለያዩ ለውጦች ውስጥ ያልፋል ፀሐይ፣ ከባድ እና መጥፎ ባህሪያት ቆዳችንን
ይለዋውጡታል፡፡ የቆዳችን ዕድሜ በተለያዩ ተፅዕኖዎች ውስጥ ያልፋል የአኗኗር ዘይቤ፣ አመጋገብ፣ ዘር፣ ማጨስና
ሌሎች የግል ልማዶች በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ለቆዳ መሸብሸብ የሚዳርጉ ተጨማሪ ምክንያቶችን መጥቀስ እንዲሁ
ይቻላል፡፡ ተፈጥሯዊ እርጅና፣ ለፀሐይ ተጋላጭነት፣ የአካባቢ ብክለት በቆዳ እና በጡንቻ መካከል የሚከማች ስብ፣
ድብርት፣ ከልክ ያለፈ ውፍረት፣ የአተኛኘት ባህል፣ ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ በዕድሜ ሳቢያ የሚመጣ ለውጥ
በዋናነት በቆዳ ለይ ይገለፃል፡፡

ውበት ከአካላዊ ገፅታም በላይ መሆኑ ማሰብ

ውበት አካላዊ ገፅታ ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁንም ስነልቦናዊው ሁኔታ ሰፊውን ድርሻ ይይዛል፡፡ ውበት ከሚታየው ቆዳ
በላይ ጥልቅ ነው፡፡ ጥናቶች እንደሚነግሩን የቱ ቆንጆ ነው የቱስ ነው መስህብ የሌለው የሚለውን መለየት በቀላሉ
ሁሉንም ሰው አያስማማም፡፡ አንዳንዶች ቆንጆ መሆኔን አስቤውም አላውቅ ሲሉ ናገራቸው የውበት ሚዛን እንደ ግለሰቡ
የሚወሰን መሆኑን ሊያሳየን ይችላል፡፡ ውበት ዓይን ከሚደርስበት ደረጃም በታች እጅግ ጥልቅ ነው፡፡ እናም በዕድሜ
እየገፋችሁ ስትሄዱ ለዚህኛው ውበት ይበልጥ ተጨነቁ ያኔም የቆዳ መሸብሸብ፣ የፀጉር ቀለም መቀየር እና በጉልበትም
መድከም እንደወትሮው አለመሆን ላያስጨንቃችሁ ይችላል፤ ባለሙያዎች ማለታቸውም ከዚህ የመነጨ ነው፡፡

በዕድሜ ሳቢያ የሚመጣን ለውጥ መቀየርና መለማመድ

በዕድሜ ሳቢያ የሚመጣን አካላዊ ለውጥ ማስቆም የሚቻል አይደለም፡፡ ነገር ግን በእርግጠኝነት በዕድሜ ሳቢያ
የሚመጣን የለውጥ ልምድ መቀየር፣ መቀበል እና መልመድ ይቻላል፡፡
ዴርማቶሎጂስትና የቀዶ ህክምና ባለሙያዎች እና ሌሎች ዶክተሮች በዕድሜ ሳቢያ የሚመጣን ልዩነት ማስቀረት
አይችሉም፡፡ /በእርግጥ የቆዳን ጤንነት በመጠበቅ መልካም ገፅታን በህክምና በማላበስ እና በሌሎች መንገዶች
እርጅናን ማዘግየት በጊዜያዊነት ይቻላቸው ይሆናል/

‹‹የውጪውን ገፅታ ለመለወጥ የምንጥረውን ያህል ውስጣችንን ብንንከባከብ  የበለጠ እንስቃለን፡፡ ስንስቅ ደግሞ
ከመስታወት ምስል ውጪ ማሰብ፣ መስታወት ስር ስንቆም የምንመለከተው እኛነታችን የሚታየው ማንነታችን አይደለም፡፡
በእርግጥ የቆዳችንን ሁኔታ፣ የፀጉራችንን ደረጃ እና አቋማችን ልንገመግምበት ቢያስችለንም እንደ ሰው ያለንን
ነገር መስታወት አይነግረንም፡፡ ስለዚህ መስታወቱ ከሚሰጠን ምስልም በላይ ማሰብ ይኖርብናል፡፡

ለቆዳ ውበትና ጤንነት የሚጠቅሙ 16 የምግብ አይነቶች እነሆ፡

1. እስፒናች፡- የቫይታሚን ኤ እና ሲ ክምችት ያለው ሲሆን እነዚህ ቫይታሚኖች የአንቲኦክሲዳንት ባህሪ ስላላቸው
ቆዳችንንም ሆነ ሰውነታችንን ከፍሪ ራዲካሎች ይከላከላሉ፡፡ ማግኚዢየም፣ ሴሌኒየም፣ እና ዚንክን መያዙ ደግሞ
ለቆዳ መወጠር፣ ለደም ዝውውር፣ ለቆዳ ወዝ ቁጥጥር ወዘተ… ትልቅ ጥቅም ይሰጣሉ፡፡
2. ኪያር፡- ለቆዳ ውበት እና ጤንነት የሚጠቅም ሲሊካ የሚባል ማዕድን ይዟል፡፡ ኪያርን አዘውትሮ መመገብ እና
የኪያር የፊት ማስክ መቀባት ቆዳን ብሩህ እና አንፀባራቂ የሆነ ውበት ያላብሰዋል፡፡ የቆዳን እርጅናም
ያዘገያል፡፡
3. ቀዩ፣ ቢጫውና ብርቱካናማው የፈረንጅ ቃሪያ፡- የፈረንጅ ቃሪያ ቤታ ካሮቲን የሚባለው የአንታይኦክሲዳንት
አይነት ባህሪ ያለው ቫይታሚንን የያዘ ሲሆን ይህም በቆችን ስባማ ክፍል ውስጥ ሟሙቶ ቦታ በመያዝ ይቀመጣል፡፡
በዚህም ምክንያት የቆዳን ህዋሳት ከፍሪ ራዲካል ለመከላከል ይረዳል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የቆዳን የመለወጥ ባህሪ
የመጠበቅ እና ሞላ ያለ እና ውብ እንዲሆን ያደርጋል፡፡
4. አቮካዶ፡- የቫይታሚን ኢ ይዞታው ከፍተኛ በመሆኑ የቆዳን ህዋሶች ከፍሪ ራዲካሎች ጥቃት ይከላከላል፡፡
5. ፐርስሊ፡- በውስጡ የያዘው ጠቃሚ ዘይት የማሸናት ባህሪ ያለው በመሆኑ፣ በውሃ ውስጥ የሚሟሙ ቆሻሻዎች
እንዲወገዱ ያደርጋል፡፡ የኩላሊት ስራንም ቀልጣፋ ያደርጋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ሌሎች እንደ ሊቲዮለን የመሳሰሉ
የአንታይኦክሲዳንት አይነቶችን በውስጡ ይዟል፡፡
6. ሽንኩርት፡- ሽንኩርቶች አንድ የጋራ የሆነ የማዕድን ይዘት አላቸው፡፡ እርሱም ሰልፈር ነው፡፡ ሰልፈር
የተባለው ማዕድን ደግሞ ቆዳ እንዳይሸበሸብ እና እንዲወጠር ያደርጋል፡፡
7. እንስላል፡- ለምግብ መፈጨት ትልቅ አስተዋፅኦ የሚያደርግ ሲሆን ዘሩ፣ ቅጠሉ፣ ሥሩም ጠቀሜታ ላይ መዋል
የሚችል የአትክልት አይነት ነው፡፡ እንስላል ልክ እንደ ፐርስሊ ሁሉ የማሸናት ባህሪ አለው፡፡ ይህ ደግሞ
ከሰውነታችን መውጣት ያለባቸውን በውሃ ውስጥ የሚሟሙ ቆሻሻዎችን በብዛት እና ቶሎ ቶሎ እንዲወገዱ ያደርጋል፡፡
ቆሻሻ ከሰውነታችን በበቂ ሁኔታ ተወገደ ማለት ደግሞ የቆዳ ጥራት እና ፍካት ይጨምራል ማለት ነው፡፡
8. ቲማቲም፡- ቲማቲም የተለያዩ አንቲኦክሲዳንት አይነቶችን የያዘ የምግብ አይነት ነው፡፡ ስለዚህ ቲማቲም
ህዋሶቻችንን ከፍሪ ራዲካል ጥቃት ሊታደግ የሚችል በቀላሉ የሚገኝ አትክልት ነው፡፡ በመሆኑም ቲማቲም ባለው
አንታይኦክሲዳንት ብዛት እና አይነት ሳቢያ የቆዳን እርጅና ፍጥነትን የመቀነስ ችሎታ አለው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ
የኮላጂንን ጥንካሬ እና የመለጠጥ ችሎታ የመጨመር ኃይል ስላለው የቆዳ መሸብሸብን ፍጥነት ይቀንሳል፡፡
9. ቀይ ስር፡- ቀይ ስር በውስጡ ቤታ ሳያኒን የተባለ ቅመም የያዘ ሲሆን ይህ ቅመም ለቀይ ስር ደማቅ ሀምራዊ
ቀለም መያዝ ምክንያትም ነው፡፡ ይህ ቅመም በዋነኛነት ከሚያከናውናቸው ሥራዎች ውስጥ የጉበትን ቆሻሻ የማስወገድ
ሥራ ማገዝ ነው፡፡ ይህም ማለት በሰውነት ውስጥ የሚገኙ መርዛማ የሆኑ ቆሻሻዎችን ለማስወገድ የሚጠቅም ሲሆን
መርዛማ ቆሻሻዎችን በመሰባበር ከሰውነት እንዲወገዱ ይረዳል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ዚያክሳቲን የተባለ
አንታይኦክሲዳንት በመያዙ ህዋሶቻችንን ከፍሪ ራዲካሎች ሊታደግልን ይችላል፡፡ ይህ በአንፃሩ ቆዳ ቶሎ
እንዳይሸበሸብ፣ ውብ እና ህይወት ያለው እንዲሆን ያደርጋል፡፡

10. ስኳር ድንች፡- በውስጡ ቆዳ አፍቃሪ የሆነውን የአንቲኦክሲዳንት አይነት ቤታ ካሮቲንን በብዛት የያዘ
ነው፡፡ ቤታ ካሮቲን ደግሞ በተደጋጋሚ በብዛት እንደተመለከትነው በቆዳችን ስባማ ክፍል ውስጥ በመጠራቀም የቆችንን
ኮላጂንን እና ኢላስቲን የተባሉ ቆዳን የመለጠጥ እና የመወጣጠር ባህሪን የሚያላብሱ ክፍሎችን ከፍሪ ራዲካሎች
ጥቃት ይከላከላል፡፡ በዚህም ሳቢያ ቆዳ ቶሎ እንዳይሸበሸብ እና እንዳያረጅ ያግዛል፡፡ ሌላው ቤታ ካሮቲን
በ‹‹አንቲ ኢንፍላማቶሪ›› ባህሪው ምክንያት የቆዳን መቅላት፣ ማበጥ እና ህመም የማከም ችሎታ አለው፡፡
11. አጃ፡- የቫይታሚን ቢ ቤተሰቦችን አሰባስቦ የያዘ የምግብ አይነት ነው፡፡ ስለዚህም በቆዳ ውስጥ ለሚከናወኑ
ሥራዎች ለምሳሌ፣ ለቀልጣፋ የደም ዝውውር፣ ለቆዳ ውበት እና ለቁስል መዳን እንዲሁም የወዝ መጠን ቁጥጥር ወዘተ…
በተጠናከረ መልኩ እንዲከናወን ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋል፡፡
12. ተልባ፡- ኦሜጋ ስሪ ፋቲ አሲድ በውስጡ የያዘ በመሆኑ ቆዳን የማለስለስ፣ የቆዳ መቅላትና ማበጥ እንዲሁም
ህመምን መከላከል ይችላል፡፡
13. የዱባ ፍሬ፡- የዱባ ፍሬ ለቆዳ ጤንነት እና ውበት ከሚጠቅሙ ማዕድናት ውስጥ ዚንክን የያዘ ሲሆን የበሽታ
መከላል አቅምን ከፍ ያደርጋል፡፡ በመሆኑም እንደ ብጉርና በኢንፌክሽን አማካኝነት የሚፈጠሩ የቆዳ ችግሮችን
ይዋጋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የኦሜጋ 3 እና 6 ፋቲ አሲድን በውስጡ ይይዛል፡፡
14. የሾርባ ቅጠል ግንድ
የሾርባ ቅጠል በውስጡ የተለያዩ አይነት ማዕድናትን የያዘ ሲሆን ለመጠቀስ ያህል ፖታሲየም፣ ሶዲየም ማግኒዥየም
ወዘተ… ይገኙበታል፡፡ እነዚህ ማዕድናት ሰውነታችን የሚያስፈልገውን መጠን ያህል ፈሳሽ ለቆዳ ውበት መጠበቅ
አስተዋፅኦ የሚያደርግ ነገር የለም ማለት ይቻላል፡፡ የቆዳ እርጥበት መጠን ሲጠበቅ ወዙ፣ ውጥረቱ፣ ሙሉነቱ፣
አንጸባራቂነቱ፣ ፍካቱ ሁሉ ጎልቶ የቆዳውን ውበት ያሳያል፡፡
15. ሽንብራ፡-
ሽንብራ በውስጡ ዚንክ የሚባል ንጥረ ነገር የያዘ ሲሆን የቆዳን ወዝ መጠን ለመቆጣጠር እና ሚዛኑን እንዲጠብቅ
ለማድረግ ይረዳል፡፡ ዚንክ የቆዳ ወዝ ሲበዛም ሆነ ሲያንስ ሚዛኑን የጠበቀ የወዝ መጠን የወዝ ዕጢዎች
እንዲያመነጩ ለማድረግ ይጠቅማል፡፡ ሌላው በሽንብራ ውስጥ የሚገኝ ጠቃሚ ነገር ደግሞ ፋይበር ነው፡፡ ፋይበር
ደግሞ እንደሚታወቀው አንጀትን ለማፅዳት ይጠቅማል፡፡ ይህም ማለት የሆድ ድርቀትን ለመከላከል ቆሻሻ ቶሎ ቶሎ
እንዲወገድ ያደርጋ፡፡ ስለዚህ ይህ ቆሻሻ በአንጀት ውስጥ በቆየ ቁጥር እነዚህ መርዞች በደም ስር ውስጥ ተመልሰው
ሰርገው በመግባት ወደ ሰውነታችን ይሰራጫሉ፡፡ የዚህ ሁኔታ ውጤት ደግሞ ጤንነታችንን ከማወኩ በተጨማሪ ቆዳችንን
ህይወት የሌለው እና አመዳም፣ ድካም የተላበሰ አይነት ፊት እንዲኖረው ያደርጋል፡፡ ስለዚህ ይህ የሚያመለክተው
ቆሻሻ ለሰውነታችን በፍጥነት በተወገደ ቁጥር የተሻለ የቆዳ ጤንነት እና ጥራት ይኖረናል፡፡
16. ጥቁር ቦለቄ
የቦለቄ ዘሮች ብዙ አይነት ናቸው፡፡ ቀይ፣ ነጭ፣ ጥቁር፣ ዥንጉርጉር የመሳሰሉት ሲሆኑ ሁሉም የየራሳቸው ጥቅም
አላቸው፡፡ ጥቁሩ ቦለቄ ለብቻው መነሳቱ ከቆዳ አንፃር ያለውን ጥቅም ለማስረዳት ነው እንጂ ሁሉም አይነት
ቦለቄዎች የሚሰጡት ጥቅም ይህ ነው የሚባል አይደለም፡፡
በእኛ በኢትዮጵያዊያን ዘንድ ግን እንደውም ጭራሹኑ ዞር ብሎ የሚያያቸው ያን ያህል ነው፡፡ በእርግጥ የሸክላ
ማሰሮዎችን ለማስጌጥ ተጠቅመውበት አይቻለሁኝ፡፡ እጅግ በጣም ነው የገረመኝ፡፡ ፈጠራውን በጣም ባደንቅም እውነቱን
ለመናገር የተሰማኝ ስሜት ግን አንድ ትንሽ ልጅ ሳያውቅ በጣም በውድ ዋጋ የገዛችሁትን አንድ ንብረት አግኝቶ
በሌላችሁበት ሲጫወትበት ብታገኙት የሚሰማችሁን አይነት ነው፡፡
ጥቁር ቦለቄ በአንደኛ ደረጃ የቫይታሚን ቢ ቤተሰቦችን በውስጡ አጭቆ የያዘ ነው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ቆዳን
በተለያየ መልኩ መርዳት ይቻላል ማለት ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ዚንክ የተባለውን ማዕድን በውስጡ ይዟል፡፡
ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት ዚንክ ደግሞ የቆዳ ወዝ ሚዛኑ እንዲጠበቅ ያደርጋል፡፡ በተጨማሪም የቆዳን ኢንፌክሽን
የሚያስከትሉ የቆዳ ችግሮችን ለመከላከልም ይጠቅማል፡፡

ጥቁር ቦለቄ ሽፋኑ ጥቁር እንዲሆን ያደረገው በውስጡ የያዘው አንቶሳያሊን የተሰኘ የአንቲኦክሲዳንት አይነት
ነው፡፡ ይህ አንቲ ኦክሲዳናት ደግሞ በቀዩ ወይን ውስጥ ከሚገኘው አንቲኦክሲዳንት ጋር አንድ አይነት ሲሆን
በዋናነት የቆዳን መቅላትና ማበጥ ብሎም ህመም የሚያስከትሉ የቆዳ ችግሮችን ለመከላከል እና ለማከም ይረዳል፡፡
ሌላው ጥቅሙ ደግሞ የማይሟሟ የፋይበር አይነት መያዙ ነው፡፡ ይህ ፋይበር በሌሎች ጥራጥሬዎች ውስጥ የሚገኝ
ቢሆንም በጥቁር ቦለቄ ውስጥ የሚገኘው ግን ለየት ያለ ነው፡፡ በአንጀታችን ውስጥ የሚገኙ ባክቴሪያዎች ይህንን
ፋይበር ሲያገኙት በቀላሉ እንዲብላላ በማድረግ ቡትሪክ አሲድ እንዲፈጠር ያደርጋሉ፡፡ ቡትሪክ አሲድ ደግሞ
የአንጀትን ግድግዳ የማደስ ችሎታ አለው፡፡ በተጨማሪም ቆሻሻ ከአንጀታችን ውስጥ በፍጥነት እንዲወገድ የማድረግና
ጠቃሚ ንጥረ ነገሮች በቀላሉ በአንጀት ግድግዳ እንዲመጠጡ የማድረግ ችሎታ አለው፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች ተደጋግፈው
ውጤቱ ቆዳችን ላይ ፍንትው ብሎ ይታያል፡፡ ይኸውም ጥርት፣ ፍክት፣ ውጥር ያለ፣ ውብና ጤናማ ቆዳ ነው፡፡

ዕድሜ ሲገፋ ውበትዎን መጠበቂያ 4 መንገዶች

የዕድሜ መግፋት የውበት መርገፊያ ምክንያት ሊሆን አይገባም፡፡ ይሄን መመሪያ ትክክል መሆኑን ያሳዩንና ዕድሜ
ዘመናቸውን የነበራቸውን ውበት አስጠብቀው የዘለቁ ሰዎች አሉ፡፡ አሁኑኑ ታዲያ በሰውነት ላይ እርምጃ መውሰድ
በመጀመር ዕድሜ እየገፋ ሲሄድ ማቆየት ይቻላል፡፡

1. የፀሐይ ቃጠሎን መከላከል
ሰውነት ለፀሐይ ሲጋለጥ ለቆዳ ካንሰር እንደሚያመጣ እንዲሁም ቆዳንም እንደሚያበላሽ ይታመናል፡፡ ቆዳ በፀሐይ
ሲጠቃ የቆዳ መበሳሳት፣ መጨማደድ፣ ለመፍታታት መቸገር ሁሉ ይከሰታል፡፡
ከፀሐይ የሚወጣን ጉዳት ታዲያ
– በዋናነት ከ4-8 ሰዓት ድረስ የሚኖረውን ጉልበተኛ ፀሐይ ውስጥ በተቻለ መጠን አለመንቀሳቀስ
– የፀሐይ መከላከያ ቅባቶችን መጠቀም
– ጥላ ወይም መከላከያ ልብሶችን መጠቀም ናቸው

2. አለማጨስ
ማጨስ በህይወት የመኖር ዕድል ብቻ አይደለም የሚቀንሰው መጥፎ ገጽታ እና መጥፎ ሽታንም ያላብሳል፡፡ እንዲሁም
ቆዳንም በተለያዩ ደረጃዎች ይጎዳል፡፡
3. ብዙ ውሃ መጠጣት
ብዙ ውሃ መጠጣት ቆዳ እንደለሰለሰ እና እንደተፍታታ እንዲቆይ ይረዳዋል፡፡ ገፅታም የተሻለ እንዲሆን ያደርጋል፡፡
በቀን ውስጥ ታዲያ 2 ሊትር ፈሳሽ ነገር መጠቀማችን መዘንጋት የለብንም፡፡
4. የጥሩ ቅርጽ ባለቤት መሆን
የጥሩ ቅርፅ ባለቤትነትን የአካል ብቃትን እንቅስቃሴን አዘውትሮ በመስራት፣ ዮጋን እና መሰል የትኩረት መሰብሰቢያ
እንቅስቃሴዎችን በማድረግ የእራስ መተማመኑን ብሎም አካላዊ መስህቡን ማቆየት ይቻላል፡፡
5. በቂ ካልሲየም መውሰድ
ብዙ የካልስየም ንጥረ ነገር ያላቸውን ምግቦችና ፈሳሽ ነገሮች በመውሰድ እንዲሁ ውበትንና ጥንካሬ ማቆየት ይቻላል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.