መውለድ አለመቻል (መሀንነትን) ከማከም አስቀድሞ መከላከሉ ይቀላል(ይመረጣልም)፡፡ በትዳር መሀል ለሚከሰት መፀነስ አለመቻል ችግር በእርግዝናና ወሊድ እንዲሁም መሃንነት ተጠያቂዋ ሴቷ ወገን ብቻ ልትሆን አይገባም፡፡ በወንድ(ባል) ምክንያት መፀነስ የማይቻልባቸው አጋጣሚዎችም አሉ፡፡ እንዲሁም አንዳንዴ በሁለቱ የትዳር ጓደኞች ጥምረት ችግር ምክንያት መውለድ አለመቻል ሊከሰት ይችላል፡፡ ለዛሬ ግን በሴቷ ምክንያት የሚከሰተውን መሃንነት እንዴት መከላከል ይቻላል ወደሚለው ጉዳይ አመራለሁ፡፡
ሴቶችን ለመሀንነት በመዳረግ ግንባር ቀደሙን ሚና የሚጫወቱት የአባላዘር ህመሞች ናቸው፡፡ በተለይም ጨብጥ፣ ቂጥኝ እና ክላሚዲያ የተባሉት ይጠቀሳሉ፡፡ የአባላዘር ህመሞች መሃንነት የሚያስከትሉት የማህፀንን ቱቦ አንዳንዴም የማህፀንን በር በማጥበብና በመድፈን ነው፡፡ ይህ መሳይ ችግርም በወንዱ ላይ በመጫን(የወንዴ ስፐርም ዘር መተላለፊያ ቱቦን በመዝጋት) የወንድ መሃንነትን ሊያመጡ ይችላሉ፡፡

በመሆኑም መሃንነትን ለመከላከል የአባላዘር ህመሞችን መከላከል ይኖርብሻል፡፡ መከላከል ብቻም አይደለም ድንገት ቢከሰት እንኳ አፋጣኝና የተሟላ ህክምና ያስፈልጋል፡፡ በጥቅሉ በአባላዘር ህመሞች ዙሪያ ማንኛዋም ሴት ልታውቃቸው የሚገቡ ነጥቦች አሉ፡፡ የሚከተሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

– ስለ አባላዘር ህመሞች ምንነት፣ መተላለፊያ መንገድ፣ ምልክቶችና የሚያስከትሉትን የጤና ጠንቅ መለየት፡፡
– ጥንቃቄ ከጎደለው ወሲብ መታቀብ፣ በተለይም የወሲብ ጓደኛን ከማብዛት መታቀብ፣ ቢቻል እስከ ጋብቻ ቀን መታቀብ ወይም ለፍቅረኛ ታምኖ መወሰን፡፡ ይህ በማይሆንበት አጋጣሚ ሁሉ ግን ኮንዶም መጠቀም፡፡

– ለአባላዘር ህመም የመጋለጡ ዕድል በተከሰተ ቁጥር ምልክት ታየም አልታየም ምርመራ ማድረግ፡፡
– የአባላዘር ህመም ከተከሰተም በፍጥነት የተሟላ ህክምናን መውሰድ፡፡ እነዚህን ቁም ነገሮች ተግባራዊ የምታደርግ ሴት በአባላዘር ህመም ምክንያት ከሚመጣ የመሃንነት ችግር ተጠበቀች ማለት ነው፡፡

የመሃንነት መንስኤ የአባላዘር ህመሞች ብቻ አይደሉምና ከአባላዘር ህመሞች መጠበቅ ብቻውን ዋስትና አይሆንም፡፡ ከመሃንነት ምክንያቶች አንዱ የሆነውና እንደ አባላዘር ህመሞች ሁሉ አስቀድሞ መከላከል የሚችሉት ሌላው ጉዳይ ደግሞ የወሊድ መቆጣጠሪያ ዘዴ ነው፡፡ አቅምን ባገናዘበ መልኩ መጥኖ መውለድ ወይም ጭራሽ ያልተፈለገ እርግዝናን ለመከላከል ከሆርሞን የሚዘጋጁ የወሊድ መቆታጠሪያዎች አንዳንዴ ከመስመር አልፈው ለአጭር ጊዜም ቢሆን መውለድን ሊከላከሉ ይችላሉ፡፡ የወሊድ መከላከያ ዘዴዎችን በተመለከተ ሊያውቁ የሚገባቸው ነጥቦች የሚከተሉትን ይመስላሉ፡፡

ከሆርሞን ከሚዘጋጁ የወሊድ መቆጣጠሪያዎች የወንዱ ዘር ከሴቷ እንቁላል እንዳይገናኝ የሚያግዱ መቆጣጠሪያ ዘዴዎች (ለምሳሌ የወንድ ወይም የሴት ኮንዶም) በበለጠ ለአጭር ጊዜም ቢሆን መውለድን ሊከላከሉ ይችላሉ፡፡ የዚህ ምክንያት ደግሞ ከሆርሞን የሚዘጋጁ የወሊድ መቆጣጠሪያ ዘዴዎች የሴቷ ኦቫሪ እንቁላል እንዳያመርት የሚያግድ በመሆኑ አንዲት ሴት ከሆርሞን የተዘጋጁ ወሊድ መቆጣጠሪያዎችን ባቆመችበት(እርግዝና በፈለገችበት ጊዜ) እንዳታረግዝ ሊያግዳት ይችላል፡፡ ይህ ችግር ደግሞ ከአንዱ የሆርሞን የመከላከያ ዘዴ ከሌላው ይለያያል፡፡

ማህፀን የማስቋጠር የእርግዝና መቆጣጠሪያ ዘዴን ከመጠቀም በፊት የመፀነስ ፍላጎት ተመልሶ እንደማይመጣ ሙሉ ለሙሉ እርግጠኛ እስከሚሆን ድረስ አለመወሰን፡፡

የማህፀን ህመም ያለባቸው ወይም የአባላዘር ህመም ያለባቸው ሴቶች በማህፀን የሚቀበረውን የእርግዝና መከላከያ ዘዴ (ሉፕ) መጠቀም የለባቸውም፡፡ ምክንያቱም ኢንፌክሽኑን ወደ ማህፀን ግድግዳ በማድረስ ማህፀንን ፅንስን ደግፎ ለማቆየት የማይመች ስፍራ ሊያደርገው ይችላልና፡፡ በሌላ አነጋገር የመሃንነት ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡

ከአባላዘር ህመሞችና ከወሊድ መቆጣጠሪያ ዘዴዎች ባለፈ ሌሎችን የመሀንነት ችግሮች እምብዛም አስቀድሞ መገመትና መከላከልም አይቻልም፡፡ የወንዱ ምክንያትነት መኖሩም ሳይረሳ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ወንዱም ከሲጋራ ሱስ በመራቅ መሀን የመሆን አጋጣሚን መቀነስ እንደሚቻል ማወቅ አለበት፡፡ ወይም ልታስተምሪው ይገባል፡፡

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.