‹‹አጠቃላይ ሽንት የምሸናበት ቦታ አልቀረኝም፡፡ ምላጩ ሁሉንም ቦታ ነው የነካው፡፡ ሦስት ቀን ሽንቴን ሳልሸና ከቆየሁ በኋላ ሰውነቴ አበጠ፡፡ ወደ አረንጓዴ ከለርም ተቀየረ፡፡ ስቃዬ የገባት እናቴ ገራዥዋን ጠራቻት፡፡ ‹የሶማሌ ጫማ› የሚባል አለ፡፡ ሰንደል የሚሉት ዓይነት፡፡ ጠንካራ ቆዳ ነው፡፡ ያልለፋ፡፡ እና ገራዥዋ ከቆዳው በስለት ቆርጣ አሾለችው፡፡ ከዚያ በዚያ በሾለው ቆዳ በግርዛቱ የተደፈነውን ቦታ በሳችው፡፡ ቆዳው የሚተወው እዚያው ብልቴ ውስጥ ነው፡፡ ስሸና አወጣዋለሁ፡፡ . . . ከአራት ወር በላይ በዚህ ዓይነት ሁኔታ ቆይቻለሁ፡፡ ግርዛት በልጅነቴ ከቁስልነቱ ጥዝጣዜ ባሻገር ዛሬም ድረስ በሴትነቴ ከምፈጽማቸው ድርጊቶች ጋር ሁሌ እያደረሰብኝ ያለው ስቃይ በቃላት የሚገለጽ አይደለም፡፡ አሁን በሚታየው ለውጥ ከማንም በላይ እደሰታለሁ፡፡ ለውጡ ብዙ ላይመስል ይችላል፡፡ ግን ከትናንት ዛሬ በጣም ብዙ ለውጥ አለ፡፡ . . . ከዛሬ ደግሞ ነገ የተሻለ እንደሚሆን ተስፋ አለኝ፡፡››

በ2003 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ሱማሌ ክልላዊ መንግሥት የጅግጅጋ ከተማ አስተዳደር ሴቶችና ማኅበራት ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ፋጡማ መሐመድ፣ በፖፑሌሽን ሚዲያ ሴንተር ለሚዘጋጀው አለኝታ ቡክሌት፣ እሳቸው በግርዛት ተሰቃይተው ቢያሳልፉም ሁኔታዎች እየተቀየሩ፣ ወንዶችም ያልተገረዘች ማግባት እየጀመሩ መምጣታቸውን፣ ወደፊት የተሻለ ለውጥ እንደሚመጣ ተስፋ እንዳላቸው ከተናገሩት ላይ የተወሰደ ነው፡፡

ለውጡ በተለይ ከ15 እስከ 49 ዕድሜ ክልል ባሉት ላይ ጉልህ ባይሆንም፣ ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ከነበረችበት በሴት ልጅ ላይ የሚፈጸም ግርዛትን መቀነሷ ነሐሴ 9 ቀን 2009 ዓ.ም. የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ አራተኛው የሥነ ሕዝብና ጤና ዳሰሳ አሳይቷል፡፡ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ግን በ2005 ከነበረው 97.3 በመቶ ወደ በ2016ቱ ዳሰሳ 99 በመቶ አድጓል፡፡

በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2000 80 በመቶ፣ በ2005 74 በመቶ ከነበረው የሴቶች ግርዛት መጠን በ2016 ወደ 65 በመቶ ዝቅ ብሏል፡፡ ግርዛቱም በዓይነቱና በመጠኑ ይለያይ እንጂ በሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች የሚተገበር ነው፡፡ በ2005 የተደረገው የኢትዮጵያ የሥነ ሕዝብና ጤና ዳሰሳ የሚያሳየውም በትግራይ 29.3 በመቶ፣ በአፋር 91.6 በመቶ፣ በአማራ 68.5 በመቶ፣ በኦሮሚያ 87.2 በመቶ፣ ሶማሌ 97.3 በመቶ፣ ቤንሻንጉል ጉምዝ 67.6 በመቶ፣ ደቡብ ሕዝቦች 71 በመቶ፣ ጋምቤላ 27.1 በመቶ፣ ሐረሪ 85.1 በመቶ፣ አዲስ አበባ 65.7 በመቶ፣ እንዲሁም ድሬዳዋ 92.3 በመቶ እንደነበር ነው፡፡

ከ15 እስከ 49 ዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሴቶችን አካቶ የተሠራው የ2016ቱ ዳሰሳ፣ ግርዛት በትግራይ ወደ 24 በመቶ፣ በአፋር ወደ 91 በመቶ፣ አማራ ወደ 62 በመቶ፣ ኦሮሚያ ወደ 76 በመቶ ሲቀንስ በሶማሌ ደግሞ ወደ 99 በመቶ አሻቅቧል፡፡ የቤንሻንጉል ጉምዝ ወደ 63 በመቶ፣ የደቡብ ሕዝቦች ወደ 62 በመቶ ሲቀንስ የጋምቤላ ደግሞ ከነበረበት 27.1 ወደ 33 በመቶ አድጓል፡፡ የሐረሪ ወደ 82 በመቶ፣ አዲስ አበባ ወደ 54 በመቶ እንዲሁም ድሬዳዋ ወደ 75 በመቶ በመቀነስ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ደረጃ በ2005 ከነበረው 74 በመቶ የሴት ልጅ ግርዛት ወደ 65 በመቶ መቀነስ ተችሏል፡፡

በኢትዮጵያ የሴት ልጅ ግርዛት በተለያዩ የዕድሜ ክልሎች የሚፈጸም ሲሆን፣ የ2016ቱ ዳሰሳ እንዳሰፈረው፣ 49 በመቶው ከአምስት 22 በመቶው ከአምስት ዓመታቸው በፊት ተገርዘዋል፡፡ እስከ ዘጠኝ፣ 18 በመቶው ከ10 እስከ እንዲሁም 14 ስድስት በመቶው 15 ዓመትና ከዚህ በላይ ዕድሜ ክልል ውስጥ የተገረዙ ናቸው፡፡

የሥነ ሕዝብና ጤና ዳሰሳው ይፋ በሆነበት ወቅት የተገኙት የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ይፍሩ ብርሃኔ (ፕሮፌሰር)፣ በሥነ ሕዝብ ጤና ላይ በአገሪቱ ለውጥ እየታየ መሆኑን በተለይ ግርዛት ላይ ያለው ሁኔታ እየቀነሰ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡ በተለይ ከ15 ዓመት ዕድሜ በታች ያሉ ሴቶች ግርዛት በመላ ኢትዮጵያ 16 በመቶ ብቻ መሆኑ፣ አገሪቷ የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስቀረት የምታደርገው ጥረት ውጤት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ከ15 ዓመት በታች ካሉ ሴቶች 84 በመቶው አልተገረዙም ማለት ከፍተኛ ውጤት መሆኑን፣ ለዚህም ከመንግሥት ጎን ለጎን መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች አስተዋጽኦ እንዳላቸው በማስታወስ፣ የሴት ልጅ ግርዛትን ዜሮ ማውረድ አለብን ብለዋል፡፡

የሴት ልጅ ግርዛትን ሳይንሱና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ቢያጣጥሉትም፣  ከወንዶች የበላይነትና ከሰብዓዊ መብት ረገጣ ቢያያይዙትም በኢትዮጵያ ሴት ልጆችን ለመግረዝ የተለያዩ ምክንያቶች ሲደረደሩ ይሰማሉ፡፡ እስካሁንም እንደ ምክንያት እየተቀመጡ አገሪቱ እ.ኤ.አ. በ2030 ግርዛትን ሙሉ ለሙሉ ለማቆም እየሄደችበት ያለውን መንገድ ይፈታተናሉ፡፡

በኢትዮጵያ የሴት ልጅ ግርዛት የሴትን ልጅ የጋለ ወሲባዊ ስሜት ይቀንሳል፣ ረጋ እንድትል ያደርጋል፣ ድንግልናን ጠብቆ ያቆያል እንዲሁም ውበቷን የጠበቀች እንድትሆን ይረዳል በሚል ምክንያት የሚፈጸም ሲሆን፣ በሦስት ዓይነት መንገድም ይፈጸማል፡፡

ይህም በግርዛቱ ወቅት ሴቶች ከሚገጥማቸው የአጭር ጊዜ አደጋ በተጨማሪ በቀላሉ ለኢንፌክሽን እንዲጋለጡ፣ በወሲብና በወሊድ ጊዜ ለሕመም እንዲጋለጡ ያደርጋቸዋል፡፡ ይህም ሆኖ ግን የሴት ልጅ ግርዛትን ለጊዜው መግታት አልተቻለም፡፡ ፈልገውና ተገደው የሚፈጸሙም አሉ፡፡ በታኅሣሥ 2009 ዓ.ም. ጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ጽንስና ማህፀን ሐኪሞች ማኅበር አዘጋጅተው በነበረው መድረክ፣ ኢትዮጵያ የሴት ልጅ ግርዛትን በ2030 በማስቀረት ዓለም አቀፍ ግብን ለማሳካት እየሠራች ቢሆንም፣ ግቡን ለማሳካት የማኅበረሰቡን ግንዛቤ ማሻሻል፣ የሕክምና ዕርዳታን ማጠናከርና ማዳረስ በተለይም የመከላከል ሥራዎችን መሥራት እንደሚጠበቅባት ተነግሮ ነበር፡፡

በተደረጉ ጥረቶች በተለይ ፕሮፌሰር ይፍሩ እንዳሉት ከ15 ዓመት በታች ካሉ ሕፃናት ያልተገረዙት 84 በመቶ መሆናቸው ትልቅ ለውጥ ቢሆንም፣ በአገሪቱ ካሉት የታዳጊ ሴት ሕፃናት ቁጥር አንፃር 16 በመቶ ተገርዘዋል ማለት ትንሽ ቁጥር አይደለም፡፡ በመሆኑም የተገኘውን ለውጥ ለማስመዝገብ ላለፉት 20 ዓመታት የተተገበረው የጤናው ዘርፍ ልማት ዕቅድ እንዲሁም የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም መስፋፋት፣ ከሃይማኖት ተቋማትና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች አጋርነት ጎን ለጎን ‹‹አንገረዝም›› ‹‹አናስገርዝም›› የሚሉ ሴተቶች፣ ወላጆች ማኅበረሰብ እንዲፈጠር የሚያስችል የግንዛቤ ሥራን ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡

የሴት ልጅ ግርዛት መቅረት ያለበት ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ስለመሆኑ እ.ኤ.አ. በ1993 በቪየና በተካሄደው የዓለም ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ፣ በ1994 በካይሮ በተካሄደው የሕዝብና ልማት ዓለም አቀፍ ኮንፍረስ እንዲሁም በ1995 በቤጂንግ በተካሄደው ዓለም አቀፍ የሴቶች ኮንፈረንስ ከስምምነት ተደርሷል፡፡ ኢትዮጵያም የሴቶችና ሕፃናት መብት የተመለከቱ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን የተቀበለች ሲሆን፣ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 35/4 ሴቶችን የሚጨቁኑ ወይም በአካላቸው ወይም በአዕምሯቸው ላይ ጉዳት የሚያስከትሉ ሕጎች፣ ወጎችና ልማዶችን ይከለክላል፡፡ በወንጀል ሕጉም የሴት ልጅ ግርዛት የወንጀል ቅጣት እንደሚያስቀጣ ተካቷል፡፡ ሆኖም የሴት ልጅ ግርዛት ዛሬም ይስተዋላል፡፡ የልማድ ውርስ ሆኖም ቀጥሏል፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት በ2015 እንዳሰፈረው የሴት ልጅ ግርዛት በአብዛኛው የሚፈጸመው በምዕራብ፣ በምሥራቅና በሰሜን ምሥራቅ አፍሪካ፣ እስያና መካከለኛው ምሥራቅ ባሉ አገሮች ነው፡፡

የእንግሊዝ ጤናና ማኅበራዊ አገልግሎት ማዕከል በ2015 ባደረገው ጥናትም በእንግሊዝ በአንድ ዓመት ብቻ ከአራት ሺሕ በላይ ሴቶች መገረዛቸውን ደርሶበታል፡፡ በሠለጠኑት አገሮች ይፈጸማል ለሚባለው የሴት ልጅ ግርዛት ከአፍሪካና የሴት ልጅ ግርዛት ከተንሰራፋባቸው አገሮች በስደት በሚገቡ ዜጎች አማካይነት ነው፡፡

የአፍሪካ ሲታይ ደግሞ በየዓመቱ ከሦስት ሚሊዮን ሴቶች በላይ የግርዛት ሰለባ ይሆናሉ፡፡ ይኼንን ለማስቀረተ የፀረ ሴት ልጅ ግርዛት ቀን በየዓመቱ የሚከበር ሲሆን፣ በ2030 የሴት ልጅ ግርዛትን ፈጽሞ ለማጥፋት በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተሠራ ይገኛል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.