• osteoporosis (1)በዓለም ዕድሜያቸው ከ45 ዓመት በላይ ከሆናቸው አራት ሴቶች ሶስቱ የአጥንት መሳሳት ችግር አለባቸው
  • በተለይ በከተሞች አካባቢ ችግሩ ተባብሷል
  • ፎስፈሪክ አሲድ ያለባቸውን ለስላሳ መጠጦች ማዘውተር ለችግሩ መነሻ ሊሆን ይችላል
  • በሽታው ከነመኖሩም ሣያስታውቅ በድንገት ለሞት የሚዳርግ ችግር ሊፈጥር ይችላል

ቀደም ባሉት ዘመናት በአገራችን ለዘርና ለትውልድ ማንነት መገለጫ፣ ለጋብቻና ለዝምድና መፈላለጊያ ግንባር ቀደሙ ተጠቃሽና ተፈላጊ ጉዳይ የአጥንት ብርቱነት ወይንም የአጥንት ስሱነት ጉዳይ ነበር፡፡ “እከሌ አጥንተ ብርቱ ነው” ከተባለ ከጥሩ ቤተሰብ የተገኘ፣ የባላባትና የሀብታሞች ዘር ነው ማለት ሲሆን አጥንተ ስሱ ነው ማለት ደግሞ ድሃ ነው ወይም የሚያኮራና የሚጠቅም ቤተሰብ የሌለው ሰው ነው እንደማለት ነበር፡፡ ዘመን ተለውጦ የሰው ልጅ በራሱ ማንነትና በስራው መለካት ሲጀምር፣ አጥንተ ብርቱነትም ሆነ አጥንተ ስሱነት የሰው ልጅ ማንነት መገለጫ የመሆን ጠቀሜታቸውን እያጡ ሄዱ፡፡

ዘመንና ቴክኖሎጂ ምስጋና ይግባቸውና ዛሬ ደግሞ አጥንተ ስሱነት ለከፍተኛ የጤና ችግር ብሎም ለሞት ሊዳርግ የሚችል የጤና ችግር እንደሆነ ይፋ ሆነ፡፡ ችግሩ በአብዛኛው የዕድሜ መግፋትን ተከትሎ የሚከሰትና ለከፍተኛ የጤና ችግር እና ለሞት ሊያደርስ እንደሚችልም ባለሙያዎቹ ይገልፃሉ፡፡

የአጥንት መሳሳት ችግር (ኦስቲዮፓረሲስ) በአጥንት ሕብረህዋሳት መሳሳት አማካይነት የሚከሰትና አጥንት ደካማና ልፍስፍስ እንዲሆን በማድረግ በቀላሉ እንዲሰበርና ከፍተኛ የጤና ችግር እንዲፈጠር የሚዳርግ በሽታ ነው፡፡ አጥንት ከሚጠቃባቸው በሽታዎች መካከል ማለትም የአጥንት ቲቢ፣ የአጥንት ካንሰርና የአጥንት መመርቀዝ ችግሮች በበለጠ በአሁኑ ወቅት በአገራችን በስፋት የሚታየውና የአብዛኛዎች ችግር የሆነው የአጥንት መሳሳት በሽታ ወይንም በሳይንሳዊ አጠራሩ (ኦስቲዮፓሪሲስ) ምንም አይነት የህመም ስሜት ሳይኖር ወይንም የትኛውንም አይነት የበሽታ ምልክት ሳያሳይ በድንገት የአጥንቶች መሰበር፣ የመጉበጥና ቀደም ሲል የነበረንን አካላዊ ቁመና የማሳጠር ችግር ከማስከተሉም በላይ የተሰበረው አጥንት በመተንፈሻ አካሎቻችን፣ በልባችንና በውስጣዊ የሰውነታችን ክፍሎች ላይ ጉዳት በማድረሱ ሳቢያ ለሞት ሊዳርገን ይችላል፡፡

አጥንት ሳሳ የሚባለው ለጠንካራ አጥንት አስፈላጊ የሆኑ ንጥረ ነገሮችን በበቂ ሁኔታ በውስጡ ሳይዝ ሲቀርና አጥንቱ የሚያጋጥሙትን ነገሮች ለመቋቋም የሚስችል ጥንካሬና ብቃት ሲያጣ ነው። በሰውነታችን ውስጥ የሚገኙትና ለአጥንት ጥንካሬ እጅግ ወሣኝ የሆኑት የካልሺየምና የፎስፌት ንጥረ ነገሮች በሰውነታችን ውስጥ በበቂ ሁኔታ አለመኖር የአጥንት መሳሳት ችግርን ያስከትላል፡፡ እነዚህ ንጥረ ነገራት ከሰውነታችን ውስጥ በተለያዩ ምክንቶች ሊቀንሱ ይችላሉ፡፡ ከእነዚህ ምክንያቶች ዋንኞቹ ግን ከዕድሜ መግፋት ጋር ተያይዘው የሚከሰቱና ለሴቶች የወር አበባ ማየት ማቆም ወይንም ማረጥ ናቸው፡፡ የአጥንት መሳሳት ችግር ዕድሜያቸው በገፋና የወር አበባ ማየት ባቆሙ (ባረጡ) ሴቶች ላይ በስፋት የሚታይ የጤና ችግር ነው፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት በ2012 ዓ.ም ያወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕድሜያቸው ከ45 ዓመት በላይ ከሆኑ አራት ሴቶች መካከል አንዷ የአጥንት መሳሳት ችግር ይኖርባታል። ዕድሜ እየገፋ በሄደ ቁጥር ችግሩ እየተባባሰ እንደሚሄድ ያመለከተው ይኸው መረጃ፤ ከ70 ዓመት በላይ ዕድሜ ካላቸው 10 ሴቶች መካከል ዘጠኝ ያህሉ የዚህ ችግር ተጠቂ እንደሚሆኑ አመልክቷል፡፡ ችግሩ ከገጠራማ አካባቢዎች በበለጠ በከተሞች ውስጥ በስፋት እንደሚስተዋል የጠቆመው መረጃው፤ ይህም በሰዎች የአኗኗር ዘይቤና የአመጋገብ ሥርዓት ላይ ተመርኩዞ እንደሆነ አመላክቷል፡፡

የአጥንት መሳሳት ችግር በአሁኑ ወቅት በአገራችን በስፋት እየታየ መሆኑን የገለፁት የነርቭ ስፔሻሊስቱ (ኒውሮሎጂስት) ዶ/ር ታረቀኝ አክሊሉ፤ በሽታው ወይንም ችግሩ በሰውነታችን ውስጥ ተከስቶ እያለ መኖሩን ሳናውቅና ምንም አይነት ምልክቶችን ሳያሳየን ለረጅም ጊዜ ልንቆይ እንደምንችል ገልፀዋል፡፡ ችግሩ የሚታወቀው ሰዎች ስብራት ወይንም የአጥንት መሰንጠቅ ደርሶባቸው ወደ ህክምና ቦታ ሲመጡ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

የአጥንት መሳሳት ችግር ያለበት ሰው ማንኛውም ጤናማ ሰው የሚያከናውናቸውን ተራ እንቅስቃሴዎች ለማድረግ በእጅጉ ይቸገራል ያሉት ዶክተሩ፤ እነዚህ ተራ እንቅስቃሴዎች (መነሳትና መቀመጥን) የመሳሰሉ በየዕለቱና በየጊዜው የምናከናውናቸው እንቅስቃሴዎች አጥንቱ እንዲሰበር ያደርጉታል፡፡ የአጥንት መሳሳት ችግር የአጥንት መሰበር፣ የአጥንት መጉበጥና የቁመት ማጠር ችግርን ሊያስከትሉ እንደሚችሉ የሚናገሩት ዶ/ር ታረቀኝ፤ በብዛት የችግሩ ተጠቂ ከሚሆኑት የሰውነታችን ክፍሎች መካከል የዳሌና የጎድን አጥንቶታችን፣ የጀርባችን አካባቢ አጥንቶችና የእጅና የእግር አንጓዎችን ዋንኞቹ እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡ የአጥንት መሳሳት ችግር በህክምና መስተካከል የሚችል ቢሆንም በአብዛኛው በሽታው መኖሩ የማይታወቅ በመሆኑና ምንም አይነት ጠቋሚ ምልክቶችን ስለማያሳይ አብዛኛዎቻችን ችግሩ እንዳለብን የምናውቀው የመሰበር አደጋ ሲደርስብንና ወደ ህክምና ተቋም ስንሄድ ብቻ መሆኑንም ዶ/ሩ ገልፀዋል፡፡

የአጥንት መሳሳት ችግር መኖሩን ለማወቅ በሚደረግ ቅድመ ምርመራ፣ ችግሩ በሰውነታችን ውስጥ መኖሩን የሚያሳይ የጨረር ምርራ መኖሩን የጠቆሙት ዶ/ሩ፤ ይህ ምርመራ በአገራችን በስፋት እየተሰራበት አለመሆኑንና በዋጋውም አንፃር እጅግ ውድ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ለአጥንት መሳሳት በሽታ መከሰትና መባባስ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋሉ ከሚባሉት ነገሮች መካከል ዋንኛው የዕድሜ መግፋት ሲሆን ችግሩ በተለይ የወር አበባ ማየት ባቆሙ (ባረጡ) ሴቶች ላይ በስፋት ይታያል፡፡ የአጥንት መሳሳት ችግር በዘር የሚወረስ ሊሆን እንደሚችል የሚገልፁት ዶ/ር ታረቀኝ፤ አልኮል አዘውትሮ መጠጣት፣ ሲጋራ ማጨስ፣ ፎስፈሪክ አሲድ በብዛት ያለባቸውን ለስላሳ መጠጦች ማዘውተር፣ የቫይታሚን ዲ እጥረት፣ በካልሺየምና ፎስፌት የበለፀጉ ምግቦች እጥረት፣ በመርዛማ የብረት ኬሚካሎች አካባቢ ረዘም ላለ ጊዜ መስራት፣ ከፍተኛ ውፍረት፣ ስትሮይድ በውስጣቸው የያዙ መድኀኒቶችን መጠቀምና ከበድ ያሉ የስፖርት እንቅስቃሴዎችን ማዘውተር ለችግሩ መባባስ አይነተኛ ምክንያቶች ናቸው ብለዋል፡፡

የአጥንት መሳሳት ችግር ከተከሰተ በኋላ ከሚደረገው ህክምና በበለጠ ችግሩ ከመከሰቱ በፊት የሚደረገው ጥንቃቄ ውጤታማ ነው የሚሉት ዶ/ር ታረቀኝ፤ ከእነዚህ የመከላከያ እርምጃዎች መካከል ለሰውነታችንና ለአጥንቶቻችን ጥንካሬ እጅግ ወሳኝ የሆኑትን የካልሺየምና ፎስፌት ንጥረ ነገሮች በበቂ ሁኔታ በየቀኑ መመገብ ዋንኛው እንደሆነ ጠቁመዋል። በተለይ የወር አበባ ማየት ያቆሙ (ያረጡ) ሴቶች በቀን ቢያንስ ከ1200-1400 ሚሊግራም የሚደርስ የካልሺየም ንጥረ ነገሮችን መውሰድ ይገባቸዋልም ብለዋል፡፡ የቫይታሚን ዲ እጥረት ለችግሩ መባባስ ምክንያት ስለሚሆን ቫይታሚን ዲን ከፀሐይ ብርሃንና ከሌሎች የተለያዩ መንገዶች ለማግኘት መሞከሩ ወሳኝነት አለው ሲሉም ተናግረዋል፡፡

መርዛማ የብረት ወይም የኒኬል ኬሚካሎች ባሉባቸው አካባቢዎች የሚሰሩ ሰዎች ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው የተናገሩት ዶ/ሩ፤ ኬሚካሎቹ የአጥንት መሳሳት ችግርን የመከሰት ወይም የማባባስ አቅማቸው ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡ ሌላው ለአጥንት መሳሳት ችግር ዋንኛው መንስኤ ተብሎ የተገለፀው ፎስፈሪክ አሲድ በብዛት ያለባቸውን ለስላሳ መጠጦች አዘውትሮ አለመጠጣት፣ ለሌሎች በሽታዎች ታዘውልን የምንወስዳቸው መድኀኒቶች ስትሮይድ በውስጣቸው መያዝ አለመያዛቸውን በማረጋገጥ ጥንቃቄ ማድረግ ችግሩ ከመከሰቱ በፊት ለመከላከል እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡ የአልኮል መጠጥ አለማዘውተርና ሲጋራ አለማጨስ ችግሩን ለመከላከል ከሚያስችሉ ጉዳዮች መካከል እንደሚጠቀሱም ዶ/ሩ ጨምረው ገልፀዋል፡፡ ምንም አይነት የህመም ስሜት ሳይኖረው ወይንም ምልክቶችን ሳያሳይ ለከፍተኛ የጤና ችግር ብሎም ለሞት ሊዳርገን የሚችለውን የአጥንት መሳሳት ችግር ለመከላከል የአመጋገብ ስርዓታችንን ማስተካከል፣ ቀላል የአካል እንቅስቃሴዎችን ማዘውተርና ከአልኮልና ከሲጋራ ሱስ ነፃ መሆን ተገቢ ነው ብለዋል – ባለሙያው፡፡

ምንጭ፥   addisadmassnews.com

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.