ከፍተኛ የደም ግፊት መከላከያውና መቆጣጠሪያው

0

ብራዚል የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

ማርያን ደንግጣለች! በድንገት ኃይለኛ ነስር ነሰራት። “የምሞት መስሎኝ ነበር” በማለት የደረሰባትን ታስታወሳለች። ዶክተሯ የነሰራት በከፍተኛ የደም ግፊት ምክንያት እንደሆነ ነገረቻት። “ግን ምንም የሚያመኝ ነገር አልነበረም” በማለት ማርያን መለሰች። ዶክተሯም መልሳ “ብዙ ሰዎች ምንም ዓይነት የሕመም ምልክት ስለማይኖራቸው ከፍተኛ የደም ግፊት እንዳለባቸው አያውቁም” አለቻት።

ያንተስ የደም ግፊት እንዴት ነው? አሁን ያለህ አኗኗር ወደፊት ከፍተኛ የደም ግፊት ያስከትልብህ ይሆን? የደም ግፊትህን ለመቆጣጠር ምን ልታደርግ ትችላለህ?*

የደም ግፊት የሚባለው ደም በደም ሥር ግድግዳዎች ላይ የሚያሳርፈው ኃይል ነው። የደም ግፊት መጠን የሚለካው ግፊት ሊመዘግብ ከሚችል መሣሪያ ጋር በተገናኘና ክንድ ላይ ተጠምጥሞ በነፋስ በሚሞላ መሣሪያ አማካኝነት ነው። ሁለት ንባቦች ይወሰዳሉ። ለምሳሌ ያህል 120/80 ይባላል። የላይኛው ቁጥር ልብ ደም ለመግፋት በሚኮማተርበት ጊዜ የሚኖረውን የግፊት መጠን የሚያመለክት በመሆኑሲስቶሊክ የደም ግፊት ሲባል የታችኛው ቁጥር ደግሞ ልብ ዘና በሚልበት ጊዜ የሚኖረውን ግፊት ስለሚያመለክት ዳያስቶሊክ ግፊት ይባላል። የደም ግፊት የሚለካው በሚሊ ሜትር ሜርኩሪ ሲሆን ሐኪሞች የደም ግፊታቸው ከ140/90 የሆኑትን ሰዎች ከፍተኛ የደም ግፊት አለባቸው ይላሉ።

የደም ግፊት ከፍ እንዲል የሚያደርጉ ምክንያቶች ምንድን ናቸው? አትክልትህን ውኃ በማጠጣት ላይ እንዳለህ አድርገህ አስብ። የቧንቧውን መክፈቻ በጣም በከፈትክ ወይም የቧንቧውን አፍ ባጠበብክ መጠን የውኃውን ግፊት መጨመር ትችላለህ። የደም ግፊት ከፍ የሚልበት ምክንያትም ይኸው ነው። የደሙ የፍሰት መጠን ሲጨምር ወይም የደም ሥሮች ሲጠቡ የደም ግፊት ከፍ ይላል። ታዲያ ከፍተኛ የደም ግፊት የሚከሰተው እንዴት ነው? ብዙ ምክንያቶች አሉ።

ልትቆጣጠራቸው የማትችላቸው መንስኤዎች

ተመራማሪዎች አንድ ሰው ከፍተኛ የደም ግፊት ያለባቸው ዘመዶች ካሉት በዚህ በሽታ የመያዙ አጋጣሚ ከፍተኛ እንደሚሆን ደርሰውበታል። ተመሳሳይ የሆኑ መንትዮች ከማይመሳሰሉ መንትዮች ይበልጥ በከፍተኛ የደም ግፊት እንደሚጠቁ ስታቲስቲካዊ ማስረጃዎች ያመለክታሉ። አንድ ጥናት “የደም ግፊት የሚያስከትሉትን ጂኖች ለይቶ በማውጣት” ጠቅሟል። ይህ ሁሉ ከፍተኛ የደም ግፊት በዘር ሊወረስ እንደሚችል ያረጋግጣሉ። በተጨማሪም በከፍተኛ የደም ግፊት የመያዝ ዕድል ከዕድሜ ጋር እየጨመረ እንደሚሄድና በጥቁር ወንዶች ላይ እንደሚያይል ታውቋል።

ልትቆጣጠራቸው የምትችላቸው መንስዔዎች

አመጋገብህን ተቆጣጠር! ጨው በአንዳንድ ሰዎች ላይ በተለይ ደግሞ በስኳር ህሙማን፣ ከባድ የደም ግፊት ባላቸው፣ በዕድሜ በገፉና በአንዳንድ ጥቁር ሰዎች ላይ የደም ግፊት ከፍ እንዲል ያደርጋል። በደም ውስጥ ብዙ ስብ በሚኖርበት ጊዜ በደም ሥሮች ውስጠኛ ግድግዳ ላይ ኮሌስትሮል ይጋገርና የደም ሥሮቹ ስፋት ስለሚጠብ (አቴሮስክለሮሲስ ይባላል) የደም ገፊት መጠን ይጨምራል። የሰውነት ክብደታቸው ከትክክለኛው ክብደት 30 በመቶ ከፍ ያለባቸው ሰዎች በከፍተኛ የደም ግፊት የመያዝ ዕድላቸው በጣም ከፍተኛ ነው። ጥናቶች እንዳረጋገጡት ፖታሲየምና ካልሲየም በብዛት መውሰድ የደም ግፊት ይቀንሳል።

ማጨስ ከአቴሮስክለሮሲስ፣ ከስኳር በሽታ፣ ከልብ ድካምና በአንጎል ውስጥ ደም ከመፍሰስ ጋር ከፍተኛ ተዛማጅነት አለው። ስለሆነም ማጨስ ከደም ግፊት መጨመር ጋር በሚጣመርበት ጊዜ ለሥርዓተ ልብ ወቧንቧ በሽታ ያጋልጣል። ማስረጃዎቹ እርስ በርሳቸው የሚጋጩ ቢሆኑም በቡና፣ በሻይና በኮላ መጠጦች ውስጥ የሚገኘው ካፊን የተባለ ንጥረ ነገርና በስሜትና በአካል ላይ የሚደርስ ውጥረት ከፍተኛ የደም ግፊትን ሊያባብስ ይችላል። በተጨማሪም ሳይንቲስቶች የአልኮል መጠጦችን በብዛት ወይም ለረዥም ጊዜ መጠጣት እንዲሁም በቂ የአካል እንቅስቃሴ አለማድረግ የደም ግፊትን ከፍ ሊያደርግ እንደሚችል ተገንዝበዋል።

ጤናማ አኗኗር

አዎንታዊ እርምጃዎችን ከመውሰድ በመታቀብ ከፍተኛ የደም ግፊት እስኪከሰት ድረስ መቆየት ስህተት ነው። ከልጅነት ዕድሜ አንስቶ ጤናማ አኗኗር መከተል ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ ነው። አሁኑኑ ጠንቃቃ መሆን ወደፊት የተሻለ ጣዕም ያለው ኑሮ ለመምራት ያስችላል።

ሦስተኛው የብራዚል ከፍተኛ የደም ግፊት ስምምነት ለደም ግፊት መቀነስ አስተዋጽኦ የሚያደርጉትን የአኗኗር ለውጦች ዘርዝሯል። ከፍተኛም ሆነ ልከኛ የደም ግፊት ላለባቸው ሰዎች ሊጠቅሙ የሚችሉ መመሪያዎች ናቸው።

ወፍራም ለሆኑ ሰዎች ተመራማሪዎቹ ዝቅተኛ የካሎሪ መጠን ያለው የተመጣጠነ አመጋገብ መከተል፣ ተዘጋጅተው የሚሸጡ ምግቦችንና በአጭር ጊዜ ክብደት ይቀንሳሉ የሚባሉትን “ተአምራዊ” ምግቦች ማስወገድ፣ መጠነኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ጥሩ እንደሚሆን ይመክራሉ። በጨው ረገድ ደግሞ በቀን ከስድስት ግራም ወይም ከአንድ የሻይ ማንኪያ ያልበለጠ ጨው መውሰድን ይመክራሉ።*ይህ ማለት በምግብ ዝግጅት ወቅት የሚጨመረውን ጨው በእጅጉ መቀነስ፣ የታሸጉ ምግቦችን፣ እንደ ሳላሜና ሞርቶዴላ የመሰሉትን ምግቦች መቀነስ ያስፈልጋል ማለት ነው። በተጨማሪም በገበታ ላይ ጨው ከመነስነስ በመታቀብና በተዘጋጁ ምግቦች ውስጥ የሚገኘውን የጨው መጠን በመጠቅለያቸው ላይ ከተጻፈው ተመልክቶ በመቆጣጠር ወደ ሰውነት የሚገባውን የጨው መጠን መቀነስ ይቻላል።

በተጨማሪም የብራዚሉ ስምምነት ፖታሲየም “የደም ግፊት እንዲቀንስ የማድረግ ባሕርይ” ሊኖረው ስለሚችል ተጨማሪ ፖታሲየም መውሰድ ጥሩ እንደሚሆን ይመክራል። በመሆኑም ጤናማ የሆነ አመጋገብ እንደ ባቄላ፣ አረንጓዴ አትክልት፣ ሙዝ፣ ከርቡሽ፣ ካሮት፣ ቀይ ሥር፣ ቲማቲምና ብርቱካን የመሰሉት “አነስተኛ ሶዲየምና ብዙ ፖታሲየም ያላቸው” ምግቦች የሚያካትት መሆን ይገባዋል። በተጨማሪም በአልኮል አወሳሰድ ረገድ ልከኛ መሆን ያስፈልጋል። ከፍተኛ የደም ግፊት ያለባቸው ወንዶች በቀን የሚወስዱት የአልኮል መጠን ከ30 ሚሊ ሊትር መብለጥ እንደማይኖርበትና ሴቶች ወይም ክብደታቸው አነስተኛ የሆኑ ሰዎች በቀን ከ15 ሚሊ ሊትር የበለጠ አልኮል መውሰድ እንደማይኖርባቸው ተመራማሪዎች ያመለክታሉ።*

የብራዚሉ ስምምነት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማዘውተር የደም ግፊት እንደሚቀንስና ከፍተኛ የደም ግፊት እንዳይመጣባቸው እንደሚከላከል ደምድሟል። በሳምንት ከሦስት እስከ አምስት ጊዜ ከ30 እስከ 45 ደቂቃ ለሚደርስ ጊዜ በእግር እንደመሄድ፣ ብስክሌት እንደመንዳትና እንደ መዋኘት ያሉትን በጣም ጠንካራ ያልሆኑ ኤሮቢክ የአካል እንቅስቃሴዎች ማድረግ ጠቃሚ ነው።* በጤናማ አኗኗር ውስጥ ሊካተቱ ከሚችሉት ተጨማሪ እርምጃዎች መካከል ማጨስ ማቆም፣ በደም ውስጥ የሚገኘውን የስብ መጠንና (ኮሌስትሮልና ትራይግሊሰራይድ) ስኳር መቆጣጠር፣ በቂ ካልስየምና ማግኒዝየም መውሰድ፣ አካላዊና ስሜታዊ ውጥረቶችን መቀነስ ይገኛሉ። አፍንጫ የሚከፍቱ መድኃኒቶች፣ ከፍተኛ የሶዲየም መጠን ያላቸው ፀረ አሲድ መድኃኒቶች፣ የምግብ ፍላጎት መቆጣጠሪያ መድኃኒቶች፣ የማይግሬይን ራስ ምታት የሚያስታግሱ ካፊን ያለባቸው መድኃኒቶች የደም ግፊት ከፍ እንዲል ሊያደርጉ ይችላሉ።

ከፍተኛ የደም ግፊት ካለብህ ሐኪምህ ላንተ ሁኔታ የሚያስፈልገውን አመጋገብና የአኗኗር ልማድ ሊመክርህ እንደሚችል የተረጋገጠ ነው። ይሁን እንጂ በየትኛውም ዓይነት ሁኔታ የምትገኝ ብትሆን ከልጅነት ጀምሮ ጤናማ አኗኗር መከተል ከፍተኛ የደም ግፊት ችግር ላለባቸው ብቻ ሳይሆን ለመላ የቤተሰብ አባሎችም ጠቃሚ ነው። በመግቢያው ላይ የተጠቀሰችው ማርያን በአኗኗሯ ላይ ለውጥ ማድረግ ነበረባት። በአሁኑ ጊዜ ሕክምናዋን እየተከታተለች ሕመም ቢኖርባትም እንደ ጤነኞች ኑሮዋን ትመራለች። አንተስ? ሰዎች ሁሉ የተሟላ ጤና አግኝተው የሚኖሩበትንና “በዚያም የሚቀመጥ:- ታምሜአለሁ አይልም” የሚለው ትንቢት ፍጻሜውን የሚያገኝበትን ጊዜ በተስፋ እየተጠባበቅህ የደም ግፊትህን ተቆጣጠር።—ኢሳይያስ 33:24

[የግርጌ ማስታወሻ]

ንቁ! ማንኛውም ዓይነት የሕክምና ምርጫ የግል ጉዳይ እንደሆነ ስለሚገነዘብ የትኛውንም የሕክምና ዓይነት ደግፎ አይናገርም።

ከፍተኛ የደም ግፊት ወይም የልብ፣ የጉበት ወይም የኩላሊት ሕመም ካለብህና መድኃኒት የምትወስድ ከሆነ በየቀኑ ምን ያህል ሶዲየምና ፖታሲየም መውሰድ እንዳለብህ ሐኪምህን አማክር።

ሠላሳ ሚሊ ሊትር አልኮል 60 ሚሊ ሊትር ከሚያክል እንደ ዊስኪና አረቄ ከመሰሉት ጠንካራ መጠጦች፣ 240 ሚሊ ሊትር ከሚያክል የወይን ጠጅ ወይም 720 ሚሊ ሊትር ከሚያክል ቢራ ጋር እኩል ነው።

በግልህ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ያስፈልግህ እንደሆነ ሐኪምህን አማክር።

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ከፍተኛ የደም ግፊትን መከላከል

1. ከፍተኛ የደም ግፊትን ለመቆጣጠር ሊወሰዱ የሚችሉ እርምጃዎች

• የሰውነት ክብደትን መቀነስ

• የጨው ፍጆታን መቀነስ

• በፖታሲየም የበለጸጉ ምግቦችን አብዝቶ መመገብ

• የአልኮል መጠጦችን ፍጆታ መቀነስ

• የአካል እንቅስቃሴ ማዘውተር

2. የደም ግፊት ለመቆጣጠር ሊረዱ የሚችሉ ሌሎች እርምጃዎች

• ተጨማሪ ካልሲየምና ማግኒዝየም መውሰድ

• ብዙ አሰር ያላቸውን አትክልቶች አብዝቶ መመገብ

• ውጥረት መቀነስ

3. ተዛማጅ እርምጃዎች

• ማጨስ ማቆም

• የኮሌስትሮል መጠን መቆጣጠር

• የስኳር ሕመምን መቆጣጠር

• የደም ግፊትን ከፍ ሊያደርጉ የሚችሉ መድኃኒቶችን አለመውሰድ

[ምንጭ]

ሰርድ ብራዚሊያን ኮንሴሰስ ኦን አርተሪያል ሃይፐርቴንሽን—ብራዚሊያን ጆርናል ኦቭ ክሊኒክ ኤንድቴራፒውቲክስ ከተባለው የተወሰደ

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማዘውተርና ጤናማ አመጋገብ መከተል ከፍተኛ የደም ግፊትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ይረዳል

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.