ምግብ በፍጥነት የምንበላ ከሆነ ብዙ ምግብ ወደ ሰውነታችን ልናስገባ እንደምንችል ተመራማሪዎች ይገልፃሉ።
በዝግታ መመገብ ለውፍረት፣ ለስኳር እና ለልብ ህመሞች የመጋለጥ እድላችንንን እንደሚቀነስ አንድ ጥናት አሳይቷል።
በአንፃሩ በፍጥነት መመገብ በደማችን ውስጥ ያለው የስኳር መጠን የተለያየ እንዲሆን በማድረግ የኢንሱሊንን ስራ እንደሚያስተጓጉል ነው ጥናቱ የገለፀው።

ቶሎ ቶሎ መመገብ በሰውነታችን ላይ ጨ የሚያስከትለው ከመጠን ያለፈ ውፍረትን እና ቦርጫምነት ለልብ ህመም፣ ለስኳር እና በጭንቅላት ውስጥ የደም መፍሰስን ያመጣል ተብሏል።
ይህ ሊከሰት የሚችለው በሆድ አካባቢ ውፍረት ሲፈጠር፣ በደም ውስጥ ያለው የግሉኮስ መጠን ከመደበኛው በከፍተኛ ሁኔታ ከጨመረ፣ ከፍተኛ የደም ግፍት ሲከሰት እና ደማችን በጣም ሲወፍር ነው።

በአሜሪካ የልብ ማህበር ጉባኤ ላይ የቀረበ አንድ ጥናት እንደሚያሳየው፥ በዝግታ ምግብን መመገብ ሰውነታችን እና ጤናችን እንዲጠበቅ ያደርጋል።
በጃፓን የሂሮሺማ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች በፈረንጆቹ 2008 ምንም ዓይነት የሆድ አካባቢ ውፍረት ያልነበረባቸውን ሰዎች መሰረት አድርገው ጥናት አካሂደዋል።
በጥናቱ የተሳተፉት እድሜያቸው በአማካይ 51 ዓመት የሚሆናቸው 642 ወንዶች እና 441 ሴቶች ናቸው።

የጥናቱ ተሳታፊዎች በዘወትር አመጋገባቸው መሰረት ፈጣን፣ በቀስታ ወይም በመደበኛ መሆን ላይ ተመስርቶ በሶስት ቡድኖች ተከፍለዋል።
ከአምስት ዓመታት በኋላም ተመራማሪዎቹ የጥናቱን ተሳታፊዎች አሁናዊ ሁኔታ እንደገና ማጥናት ጀመሩ።
በዚህም መሰረት በጣም በፍጥነት የሚመገቡት የጥናቱ ተሳታፊዎች 11 ነጥብ 6 በመቶ ያልተገባ የሆድ አካባቢ ውፍረት ጨምረው ተገኝተዋል።

በአንፃሩ በመደበኛ ሁኔታ የሚመገቡት 6 ነጥብ 5 በዝግታ የሚመገቡተ ደግሞ 2 ነጥብ 3 በመቶ ሆኖ ተገኝቷል።
በዚህም በፍጥነት መመገብ የክብደት መጠን እንዲጨምር፣ የሆድና የወገብ አካባቢ ውፍረት ከፍ እንዲል እና በደማችን ውስጥ ያለው የግሉኮስ መጠን እንዲበዛ እንደሚያደርግ ደርሰንበታል ነው ያሉት የሂሮሺማ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች።
በመሆኑም ምግብን በቀስታ አላምጦ ለመዋጥ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ፣ በዝግታ መጉረስ ወይም ቶሎ ቶሎ ምግብ ወደ አፍ አለመላክ ተገቢ ነው ተብሏል።
ምግብን በዝግታ መመገብ ያልተገባ እና የተለያዩ የጤና ጠንቆችን የሚያመጣ የአካላዊ ውፍረት እንዳያጋጥመን ፋይዳው የላቀ ነው።

ይህ ደግሞ ለስኳር፣ ለልብ ህመሞች እና ለጭንቅላት ውስጥ የደም መፍሰስ የመጋለጥ እድላችንን እንደሚቀንሰው ነው የተመላከተው።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.